ፈልግ

ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን የኢትዮጵያ ካቶሊካዊያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን የኢትዮጵያ ካቶሊካዊያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት 

ብፁዕ ካ. ብርሃነየሱስ ለ2011ዓ.ም የትንሣኤ በዓል ያስተላለፉት መልእክት

“የጌታ ትንሣኤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ለሚኖሩት ራሳቸውን ላስገዙ ልዩ ደስታ የሚሰጥ ነውና በፊቱ ለመቆም የሚያስችለንን በጎ ሥራውንና መልካሙን ሥራ እንሥራ። ሁላችንም ለአገራችን እርቀ ሰላም በጸሎትና በጾም እንትጋ”

ብፁዕ ካርዲናል  ብርሃነየሱስ  

የኢትዮጵያ  ካቶሊካዊት  ቤተክርስቲያን  ሊቀጳጳሳት

ለመላው የአገራችን ምዕመናን የ2011ዓ.ም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የትንሳኤ በዓል በማስመልከት ያስተላለፉት መልዕክት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

“አይዞአችሁ አትደንግጡ፤ እናንተ የምትፈልጉት ተሰቅሎ የነበረውን የናዝሬቱን ኢየሱስ እንደሆነ አውቃለሁ፤ እርሱ ተነሥቷል እዚህ የለም የተቀበረበትም ቦታ ይኸውላችሁ፤ ተመልከቱ"። (ማርቆስ 16፡6)

      

ብፁዐን ጳጳሳት

ክቡራን ካህናት፤

ገዳማውያን/ዊያት

ክቡራትና ክቡራን ምዕመናን

መላው ሕዝበ እግዚአብሔር

በጎ ፍቃድ ላላቸው ሰዎች በሙሉ

ከሁሉ አስቀድሜ ለመላው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ምዕመናንና ምዕመናት እንኳን ለ2011 ዓ.ም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞቴን በእኔና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ስም አቀርብላችኋለሁ።

    “በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ምክንያት ህያው የሆነውን ተስፋ የሰጠን በታላቅ ምህረቱ በአዲስ ልደት ልጆቹ ያደረገን ይመስገን”  (1ጴ 1፡3 )

 እግዚአብሔር አባታችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ከሞት በማስነሣት እኛን ሁለተኛ እንደወለደንና አዲስ ሕይወት እንደሰጠን ከዚህ ከሚያልፈው ርስት ይልቅ በሰማይ ቤት የማያልፍ ርስትን አዘጋጅቶልናል። እኛም ክርስቲያኖች ትናንትም ዛሬና ነገም በእግዚአብሔር ኃይልና ምህረት በመታመን የዘለዓለምን ርስት ለማግኘት ሙሉ ተስፋ አለን። ለዚህ ደግሞ በህያው ተስፋው አማካይነት ምህረት ስላደረገልን ለእግዚአብሔር ክብርና ምስጋና ይገባዋል።

ጌታችን ሞትን ድል አድርጎ ከሞት እንደተነሣ እኛም በአሁኑ ጊዜ ከሃጢያት ተላቀን ከክፋት ሃሳብና ሥራ ወጥተን አዲስ ሕይወትን መጀመር ይኖርብናል። የጾም ውጤት በሥጋ ተጋድሎ የነፍሳችንን በረከት ማብዛት ነውና ይህን የተቀበልነውን ጸጋና በረከት  ተመልሰን ወደ ኃጢያት ውስጥ ሳንከት የሰላምና የመግባባት መንፈስ በመላው የአገራችን ዜጎች ውስጥ እንዲኖር ያስፈልጋል። ይህ ዓይነት መንፈስ በእኛ ውስጥ ሲገኝ እኛም የትንሣኤውን ጸጋና ብርሃን መቀበላችንን እርግጠኛ ይሆናል።

የተወደዳችሁ ምዕመናን

ሐዋርያው ጳውሎስ በቆላስያስ መልዕክቱ “ጌታችን ከሞት ተነሥቶ በአብ ቀኝ ተቀመጠ፤ መንፈሱን ሰጠን” ይላል። በዚህም እኛ ዛሬ ይህን መንፈስ ተቀብለን በክርስቶስ ሕይወት ሆነን በሕይወት እንገኛለን የክርስትና ሕይወት ደግሞ አካሄዳችንን ወደ መልካምነትና በጎነት መምራት እንጂ ወደ ጥላቻና ጥፋት መውሰድ አይገባም። ሁላችንም በምድር እስካለን ድረስ የአምላካችንን ፈቃድ ማድረግ መፈጸም ይጠበቅብናል። ሁላችንም መጣጣር ያለብን እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት ነው ። መልካም ክርስቲያን ክፋትን አሸንፎ መልካም ሥራ የሚሠራ ነውና።

በአሁኑ ጊዜ እኛ ሰዎች በአርዓያ ሥላሴ አምሳል ከተፈጠረው ሰው ጋር ሰላምን ፈጥረን ሊያገኘን ሲገባ በየአካባቢው ተቃርኖ ውስጥ እየገባን መሄዳችን እጅግ የሚያስፈራና የሚያሳዝን ነገር ነው ። ማንኛውም ሰው በሚያደርገው ያልተገባ ሥራና አካሄድ እንዲሁም ኃጢያት ክርስቶስ ለሰው ልጆች ኃጢያት ሞቶ የተነሣለትን የእግዚአብሔር ህዝብ ማፈናቀልና ማሳደድ ከእምነት ውጪ የሆነ ነገር በመሆኑ ሁሉም በየእምነቱ መጀመሪያ ላይ እንደሚያስተምረው ከፈጣሪ ቀጥሎ ሰውን ሁሉ እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ የሚለውን መሪ ቃል በመከተል፣ እርስ በእርሳችን ይቅር ተባብለን ካልተዋደድንና ካልተዛዘንን የትንሣኤው ክብር ዋጋ ያጣልና ከእግዚአብሔርና ከሰዎች ጋር ሰላምን በግድ ልንፈጥር ይገባናል።

በመሆኑም ወደ ጥላቻና ከእግዚአብሔር ክንድ ውጪ ለመውጣት የምንገሠግሥ ከሆነ ብዙ የምንሠራበትን ጊዜ በከንቱ እናሳልፈዋለን። እኛ በአንድ በፈጣሪ እርሾ ውስጥ ያለን እንጂ የዚህን የዚያን ተባብለን አንዳችን ለአንዳችን እንቅፋት በመሆን ብዙ ሥራዎችን ልንሠራ የምንችልበትን ጊዜያችንን ማባከን፣ ተስፋችንን ማጨለም የለብንም ።

 “ክርስቶስ ከሙታን ተነሣ ሞቶ ሞትን ረገጠ፤ በመቃብር ውስጥ ላሉትም የዘላዓለም ዕረፍት ሕይወት ሰጣቸው።”

በይቅርታና በፍቅር እንዲሁም በሰላም ሁልጊዜ የተሰጠንን የሕይወት ጊዜ በደስታ ለመኖር እንድንችል በምህረት የተሞላ ልብ እንዲኖረንና እንዲሁም በሰዎችም ሆነ በእግዚአብሔር ፊት ልዩ ጸጋን የሚያሰጠንን የይቅርታ ፣ መንፈስ በሕይወት ልንኖረው ይጠበቅብናል። ብፁዕ ወቅዱስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቼስኮስ የትሕትናን ትልቅነቱንና አስፈላጊነቱን ለደቡብ ሱዳን መሪዎችና ለደቡብ ሱዳን ሕዝብ በሙሉ በግልጽ ጐንበስ በማለት ጫማ ስመው አሳይተውናል።

በሀገራችን በኢትዮጵያም በተቋቋመው የእርቅና የሰላም ኮሚሽን በኩል ለሁላችንም የተሰጠንን ትላቅ ኃላፊነት በሚገባ እንድንወጣና ዕርቀ ሰላሙን ተግባራዊ እንድናደርገው ፈጣሪ እንዲረዳን በየቤተእመነቱ ጸሎት እንዲደረግ አደራ እላለሁ፡፡  

ሁላችንም መረዳት ያለብን አገራችን ከተፈጠረችበት ጊዜ አንስቶ እስከ ፍጻሜዋ የሚመራት አልፋና ኦሜጋ የሆነው እግዚአብሔር እንደሆነ ነው። ስለዚህ ትንሣኤን በአዲስ ህሊና ለማክበር ለሰው ልጆች ደኅንነት የማይጠቅሙ ነገሮችን በማስወገድ በእምነት በተስፋና በፍቅር ጸንተን በመቆም ሃይማኖታችንን ጠብቀን መጓዝ ይኖርብናል።

   የጌታ ትንሣኤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ለሚኖሩት ራሳቸውን ላስገዙ ልዩ ደስታ የሚሰጥ ነውና በፊቱ ለመቆም የሚያስችለንን በጎ ሥራውንና መልካሙን ሥራ እንሥራ። ሁላችንም ለአገራችን እርቀ ሰላም በጸሎትና በጾም እንትጋ፡፤

ደቀመዛሙርቱና ተከታዮቹ የኢየሱስን ትንሣኤ እንደሰበኩ ክርስቲያኖችም ፍቅር በጥላቻ ላይ ዕርቅ በኩሪፊያ ላይ ወንድማማችነትና እህትማማችነት በመለያየት ላይ፣ ልክ እንደትንሣኤው አሸናፊ መሆናቸውን መገናኛ ብዙኃንንና ማሕበራዊ ሚዲያዎችን ተጠቅመን ማብሠር ይጠበቅብናል።

   

የተወደዳችሁ ምዕመናን

ይህን የጌታችን የትንሣኤ በዓል ስናከብር ልክ እንደ መጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች አንድ ሆነን በተለይ በአገራችን በተለያዩ ክፍሎች ተፈናቅለው ላሉ ወገኖቻችን፣ ከችግረኞችና ከአቅመደካሞች፣ ረዳትና አስታዋሽ ከሌላቸው ጋር በመሆን ገንዘባችንን እንደ አቅማችን ያለንን በመስጠትና በማካፈል እነዚህን ወገኖቻችንን በመርዳትና በማስደሰት በዓሉን በማሳለፍ ፍፁም ሰላምና ደስታ ያለው በዓል በጋራ አብረን እንድናከብር አደራ ማለት እወዳለሁ።

በመጨረሻም በህመም ምክንያት በየሆስፒታሉ፣ ጤና ጣብያዎችና እንዲሁም በቤታችሁ ያላችሁ ህሙማን እግዚአብሔር ምህረቱን እንዲልክላችሁ፣ በማረሚያ ቤቶች የምትገኙ የህግ ታራሚዎች እግዚአብሔር መፈታትን እንዲሰጣችሁ የአገርን ደህንነት ለማስከበር የተሰማራችሁ የፌዴራልና የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ በአገር ውስጥና ከአገር ውጪ በሥራና በተለያዩ ምክንያቶች ከአገርና ከቤተሰብ ርቃችሁ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሁላችሁ እንኳን ለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ።

                  የትንሣኤው የጸጋ ብርሃን ከሁላችን ጋር ይሁን!

                 እግዚአብሔር አገራችን ኢትዮጵያን አብዝቶ ይባርካት!

ካርዲናል ብርሃነየሱስ

ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
27 April 2019, 10:40