ፈልግ

ወጣቶች የመዝናኛ ትርዒታቸውን ሲያቀርቡ ወጣቶች የመዝናኛ ትርዒታቸውን ሲያቀርቡ 

ለወጣቶች የሚመደብ የመዝናኛ ጊዜ

በሁሉም ማሕበረሰብ ዘንድ ወጣቶች ጤናማ የሆነ የአካል እና የአእምሮ እድገትን ለማምጣት ከሌሎች የጤና እንክብካቤዎች በተጨማሪ የመዝናኛ ጊዜ መኖር አስፈላጊ ነው። ይህን እቅድ ለማሳካት በተግባር የሚውሉ መርሃ ግብሮችን በማውጣት የተለያዩ ጨዋታዎችን፣ የስፖርት እንቅስቃሴዎችን እና ባሕላዊ በአላትን አዘጋጅቶ ወጣቶችን ማሳተፍ፣ ዓመታዊ ትርፍ ጊዜያቸውን በመዝናናት እንዲያሳልፉ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ይታመናል።

አዘጋጅ እና አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የወጣችን ማህበራዊ፣ ኤኮኖሚያዊ ፖለቲካዊ እና ማሕላዊ ሕይወትንም ጭምር ወደ ተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስ በርካታ አገሮች የተለያዩ እቅዶችን በማውጣት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ። የወጣቶች ችግር እንደ የአገሮቻቸው ሊለያይ ይችላል። በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ወጣቶች ዘንድ የሚታዩ ችግሮች ባደጉት አገሮች ዘንድ ሙሉ በሙሉ ተወግደዋል ለማለት ያስቸግራል። ወጣቶች እንዲወገድላቸው ከሚፈልጉት ማሕበራዊ ችግሮች መካከል ጥራቱን የጠበቀ የትምህርት እና የስልጠና ዕድልን በበቂ ሁኔታ አለመዳረስ፣ ሥራ አጥነት፣ በቂ የሆነ የጤና እንክብካቤን አለማግኘት እና የጎጂ ሱሶች ተገዢነት የሚሉት ከሚጠቀሱ ችግሮች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።

በሁሉም ማሕበረሰብ ዘንድ ወጣቶች ጤናማ የሆነ የአካል እና የአእምሮ እድገትን ለማምጣት ከሌሎች የጤና እንክብካቤዎች በተጨማሪ የመዝናኛ ጊዜ መኖር አስፈላጊ ነው ይህን እቅድ ለማሳካት በተግባር የሚውሉ መርሃ ግብሮችን በማውጣት የተለያዩ ጨዋታዎችን፣ የስፖርት እንቅስቃሴዎችን እና ባሕላዊ በአላትን አዘጋጅቶ ወጣቶችን ማሳተፍ፣ ዓመታዊ ትርፍ ጊዜ ያቸውን በመዝናናት እንዲያሳልፉ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ይታመናል። ወጣቶች ትርፍ ጊዜያቸውን በዚህ መልክ በሚያሳልፉበት ጊዜ አካልን እና አእምሮን ሊጎዱ ከሚችሉ ተግባራት፣ ከእነዚህም መካከል ከአደንዛዥ ዕጽ፣ ከወንጀል፣ ከአመጽ እና ከሌሎችም እኩይ ተግባራት ራሳቸውን ሊያገልሉ ይችላሉ። በአንድ አገር ውስጥ ለወጣቶች ሊኖር የሚገባውን የመዝናኛ ጊዜ አስፈላጊነት በተመለከተ የሚቀርቡ ጠቃሚ አስተያየቶች ብዙ ቢሆኑም ከዚህ ቀጥሎ ያሉትን እንደ ምሳሌ መውሰድ ይቻላል ብለን እንገምታለን።

በአንድ አገር ወይም አካባቢ ለወጣቶች ተብሎ የሚዘጋጅ የመዝናኛ ጊዜ እቅድ ያለ እንደሆነ፣ ለሌሎች አጠቃላይ ማሕበራዊ ፖሊሲዎች እና መርሃ ግብሮች የሚሰጠውን እውቅና እና ትኩረት በመስጠት፣ እውቅና እና ትኩረት መስጠት ብቻ ሳይሆን የሚዘጋጀው የመዝናኛ ጊዜ አዝናኝ እና አስተማሪ እንዲሆን ለማድረግ ከመንግሥስት ሆነ በወጣቶች ማሕበራዊ ሕይወት ዙሪያ የሚሰሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም ሳይቀሩ በቂ ገንዘብ፣ ጉልበት እና ጊዜን በመመደብ ዕቅዳቸውን ፍሬያማ ማድረግ ያስፈልጋል። መንግሥት ከልዩ ልዩ በሀገር ውስጥ እና ከሃገር ውጭ ከሚገኙ ድርጅቶች እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር ለምሳሌ ሙዜሞችን፣ የንባብ ቤቶችን እና ባሕላዊ የመዝናኛ ስፍራዎችን ማመቻቸት ወይም ማዘጋጀት ያስፈልጋል። ከዚህም በተጨማሪ ወጣቶች በድራማ፣ በሙዚቃ፣ በቱሪዝም እና በሌሎችም ባሕላዊ እና ዘመናዊ በሆኑ መዝናኛዎች እንዲሳተፉ ማድረግ ያስፈልጋል።

የወጥቶች የመዝናኛ ጊዜ ወጣቶች ተገናኝተው አንዱ ከሌላው ጠቃሚ እውቀቶችን፣ ሃሳቦችን እና ምክሮችን የሚለዋወጡበት ጥሩ አጋጣሚ ስለሚሆን የወጣቶችን የእውቀት አድማስን ለማስፋት መንግሥታት ለትምህርት ተቋማት የገንዘብ ድጋፍን በማድረግ ወጣቶች ከመደበኛው የትምህርት ጊዜ በተጨማሪ ለመዝናኛ ጊዜም ዕድል እንዲሰጣቸው ማድረግ ያስፈልጋል።

ለወጣቶች የሚዘጋጅ የመዝናኛ ጊዜ እቅድ በዋና ዋና ከተሞች ውስጥ ያሉትን ወጣቶች ብቻ የሚመለከት ሳይሆን በተለያዩ የገጠር ከተሞች እንደዚሁም በገጠራማው አካባቢ የሚኖሩ ወጣቶችን ያካተተ መሆን ያስፈልጋል። የወጣቶችን የመዝናኛ ጊዜ እቅድ ከሌሎች ማሕበራዊ የእድገት እቅዶች መካከል አንዱ በማድረግ ወጣቶች በሚኖሩበት አካባቢ የተነሳ ልዩነት ሳይደረግባቸው በሁሉም አካባቢዎች ለሚኖር የወጣቱ ክፍል ተመሳሳይ እድል እንዲዳረስ ማድረግ ያስፈልጋል።

በወጣቶች የመዝናኛ ጊዜ እቅድ ውስጥ የብዙሃን መገናኛ መንገዶች ሚና የጎላ ስለሚሆን፣ በተለይም ወጣቶች ከተለያዩ ወንጀሎች እንዲታቀቡ በማድረግ፣ በማሕበራዊ ኑሮ ምርታማ እንዲሆኑ በማድረግ፣ እያዝናኑ በማስተማር ትልቅ እገዛን ማድረግ እንደሚችሉ መዘንጋት የለበትም።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
01 March 2019, 17:43