የመጋቢት 24/2011 ዓ.ም. የቀበላ ጾም እለተ ሰንበት ምንባባት እና አስተንትኖ የመጋቢት 24/2011 ዓ.ም. የቀበላ ጾም እለተ ሰንበት ምንባባት እና አስተንትኖ 

የመጋቢት 24/2011 ዓ.ም. የቀበላ ጾም እለተ ሰንበት ምንባባት እና አስተንትኖ

“በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአልና”

 

የእለቱ ምንባባት

1.     ዕብ13፡7-16

2.     ያዕቆብ 4፡6-17

3.     የሐዋ. ሥራ 25፡13-27

4.     ዮሐንስ 3፡10-24

የእለቱ ቅዱስ ወንጌ

ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “አንተ የእስራኤል መምህር ሆነህ ሳለ እነዚህን ነገሮች አታውቅምን? እውነት እልሃለሁ፤ የምናውቀውን እንናገራለን፤ ያየነውንም እንመሰክራለን፤ እናንተ ግን ምስክርነታችንን አትቀበሉም። ስለ ምድራዊው ነገር ነግሬአችሁ ያላመናችሁ፣ ስለ ሰማያዊው ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ? ከሰማይ ከወረደው ከሰው ልጅ በቀር፣ ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም።ሙሴ በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ፣ የሰው ልጅም እንዲሁ ሊሰቀል ይገባዋል፤ይኸውም በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው ነው።

“በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአልና፤ እግዚአብሔር ልጁን ወደ ዓለም የላከው በዓለም ለመፍረድ ሳይሆን፣ ዓለምን በእርሱ ለማዳን ነው። በእርሱ የሚያምን ሁሉ አይፈረድበትም፤ በእርሱ የማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ፣ አሁኑኑ ተፈርዶበታል። ፍርዱም ይህ ነው፤ ብርሃን ወደ ዓለም መጣ፤ ሰዎች ግን ሥራቸው ክፉ ስለ ነበረ፣ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ወደዱ፤ ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላል፤ አድራጎቱም እንዳይገለጥበት ወደ ብርሃን አይመጣም። በእውነት የሚመላለስ ግን ሥራው በእግዚአብሔር የተሠራ መሆኑ በግልጽ ይታይ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል።”

ከዚህ በኋላ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ይሁዳ አገር ሄዱ፤ እዚያም ከእነርሱ ጋር ጥቂት ተቀመጠ፤ አጠመቀም። በዚህ ጊዜ ዮሐንስም በሳሌም አቅራቢያ ሄኖን በተባለ ስፍራ ብዙ ውሃ ስለ ነበረ፣ ያጠምቅ ነበር፤ ሰዎችም ለመጠመቅ ይመጡ ነበር። ይህም የሆነው ዮሐንስ ከመታሰሩ በፊት ነበር

የእለት ቃለ እግዚኣብሔር አስተንትኖ

በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም መልካም ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ ዛሬ እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት አቆጣጠር ዘቅበላ የተሰኘውን ሰንበት እናከብራለን፡፡ ዛሬም እንደ ወትሮው ሁሉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቀደም ሲሉ በተነበቡት ንባባት አማካኝነት እያንዳንዳችንን ይጐበኘናል፣ ያስተምረናልም፡፡

በመጀመሪያው ምንባብ ቅዱስ ሕዋርያዋ ጳውሎስ ለዕብራዊያን በጻፈው መልእክቱ እንዲህ ይላል “የእግዚአብሔርን ቃል ያስተማሯችሁን የቀድሞ አባቶቻችሁን አስቡ የኑሮአቸውንም ፍሮ እየተመለከታችሁ በእምነታችሁ ምሰሉዋቸው” ይላል። የእግዚአብሔርን ቃል ያስተማሩን ማናቸው? ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በምድር ላይ ቅን በነበሩ ሰዎች አማካኝነት በነ ሙሴ በነ አሮን እንዲሁም ከዛም በኃላ በተለያዩ ነቢያት አማካኝነት ሕዝቡን ያስተምር ነበር፡፡

ነገር ግን ይህ ሁሉ ትምህርትና ተግሳጽ የሰውን ልብ ሙሉ በሙሉ ሊገዛው ባለመቻሉ በስተመጨረሻ አምላክ ራሱ ሰው በመሆን አስተማረ ከሱም በኃላ እንዲያስተምሩ ሐዋርያቶችን አዘጋጀ በዓለምም ሁሉ እየተዘዋወሩ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እንዲያጠምቁ ላካቸው፡፡ ዛሬ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ እነዚህን አስተማሪዎች አስቡ የደረሱበትንም ቦታ በማሰብ የሚላችሁን ስሙ መንገዳቸውንም ተከተሉ በእምነታችሁም ምሰሉአቸው ይለናል፡፡ እነዚህ የቀድሞ አባቶቻችን ለእግዚአብሔር ፍጹም ታዛዦች ነበሩ ከሁሉ በፊት ቅድሚያ ለአምላካቸው ለፈጣሪያቸው ይሰጡ ነበር በመሆኑም እግዚአብሔርን አከበሩ እርሱም አከበራቸው፡፡

እግዚአበሔር ስለ እነርሱ መሰከረ “እኔ የአብርሃም፣የይስሐቅ፣ የያዕቆብ የሕያዋን አምላክ ነኝ አለ፡፡ ስለዚህ እነዚህ አባቶቸችን የደረሱበትን ቦታ በማሰብ እናንተም በእምነታችሁ የእነርሱን አብነት ተከተሉ ይለናል፡፡ እነርሱ እግዚአበሔር ባመላከታቸው መንገድ ስለተጓዙ እምነታቸውን ጠብቀው ስለኖሩ ስማቸው በሰማይም ሆነ በምድር ሕያው ሆኖ ይኖራል፡፡ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ለዚህ ነው እነርሱን ምሰሉ የሚለን እኛም እንደነሱ በሰማይም ሆነ በምድር ሕያው ሆነን እንድንኖር ነው፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እነዚህ አባቶች ከመፈጠራቸው በፊት ነበር ዛሬም ከኛ ጋር አለ ወደፊትም ይኖራል፡፡ በዕብራውያን መልእክት ቁ8 ላይ ሲነበብ እንደሰማነው “ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ዘለዓለም ያው ነው ይለናል፡፡ እንግዲህ ይህ ጥንትም የነበረ ዛሬም ያለ አምላክ እምነታችን ጠንካራ እንዲሆን  በሰው አምሳል ተፈጥሮ አስተማረን፡፡ የእርሱንም ትምህርት ይዘው እንዲቀጥሉ ሐዋርያቶችን ወደ ዓለም ሁሉ ላከ የእነርሱንም ትምህርትና እምነት እንድንከተል እኛንም በጸጋው ሞላን፡፡

ታዲያ ዛሬ እኛ ይህንን ትምሕርት፣ የእነዚህን ቅዱሳኖች አብነት በመከተል ላይ እንገኛለን ወይስ ደግሞ በራሳችን ስሜትና ፍላጎት ብቻ በመመራት በዓለም ላይ እየተቅበዘበዝን እንገኛለን? ልባችን በእግዚአበሔር ላይ ካልፀና በምንም መልኩ የተረጋጋ ሕይወት ሊኖረን አይችልም እውነተኛ ውስጣዊና ውጫዊ ሰላምሊኖረን አይችልም  “በዚሁ ተመሳሳይ መልዕክት ቁ.9 ላይ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ምን ይላል “ ልዩ ልዩ ዓይነት በሆነ እንግዳ ትምህርት አትወሰዱ ልባችሁ በጸጋ ቢፀና መልካም ነው ይለናል፡፡

ይህንን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረውን ሐዋርያቶችና አባቶች በደማቸው የመሰከሩለትን በአንድ ዓለት ላይ የተመሰረተን እምነት ቅድስት ቤተክርስቲያን ዘወትር ለልጆቿ ታስተምራለች፡፡ ይሕ እምነታችን እንዳያድግ ብሎም ፍሬ እንዳያፈራ በመንገዳችን ላይ ብዙ መሰናክል ይኖራል፡፡ ቅዱስ ሐዋርያው ያዕቆብ ሰይጣን እምነታችን ጽኑ እንዳይሆን በብዙ መልኩ ይፈትነናል ይላል፡፡

እኛም እግዚአብሔርን በተከፈለ ልብ የምንቀርብና በተከፈለ ልብ የምንታዘዝ ከሆነ በሰይጣን ፈተናዎች በቀላሉ እንታለላለን በፈተናውም እንወድቃለን፡፡  እነዚህ አባቶቻችን እንዳስተማሩን በትሕትና በሙሉ ልብ ወደ እግዚአብሔር ከቀረብን እምነታችንም ደጸና ከሆነ በጸጋው ይሞላናል፡፡ ጸጋውም በእግዚአብሔር መንገድ ውስጥ እንድንመላለስ ያደርገናል፡፡  የሰይጣንን ሥራ እንድንክድና በእምነታቸንም ጠንክረን እንድንቆም ያግዘናል  ፡፡

ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ እንዲህ ይለናል “መዝ. 51 ትሑት የሆነውንና ለንሰሐ የተዘጋጀውን ልብ እግዚአብሔር አይንቅም” ይላል፡፡ ወንጌላዊው ዩሐንስም በወንጌሉ እንደሚያስተምረን በእግዘአብሔር ያመነ፣ የእርሱንም መንገድ የተከተለ፣ ፈቃዱንም የፈጸመ ለዘለዓለም እንደሚኖር፤ ይነግረናል። ይህንን ያልፈፀመ ግን በተቃራኒው እግዚአብሔር የሰጠውን ጸጋ ወደ ጐን በመተው በራሱ ፈቃድ ከዘለዓለማዊ ሕይወት ራሱን እንዳገለለ ይናገራል፡፡

ከእግዚአብሔር ጋር የሚጓዝ ሰው በብርሃን ውስጥ እንደሚጓዝ ይናገራል በብርሃን ውስጥ የሚጓዝ መሰናክል ቢያጋጥመው እንኳ ይህ ብርሃን ስለሚመራው ወደ ጉድጓድ አይወድቅም፡፡  በብርሃን ውስጥ የማይመላለስ ሰው  ብርሃንን የሚፈራ ሰው ነው የሚፈራበትም ምክንያት ውስጡ በኃጢአት ጨለማ ስለተዋጠ ነው ወደ ብርሃን ቢወጣ ስራው የሚታወቅበት ስለሚመስለው ነው፡፡ በዚሁ በዮሐንስ ወንጌል 3፥20 ላይ እንዲህ ይላል ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላል አድራጎቱም እንዳይጋለጥበት ወደ ብርሃን አይመጣም ይላል፡፡   እኛም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠንን እውነተኛ እምነት በጽናት ይዘን ዘወትር በብርሃን ውስጥ መጓዝ እንድንችል ራሳችንን የምንመረምርበት ወቅት ነው፡፡ ስለ ሰው ፍቅር ብሎ ራሱን አሳልፎ የሰጠውን ክርስቶስን በማሰብ   እኛም  ለሌሎች ያለንን የምናካፍልበት ወቅት ነው፡፡ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ ተሳታፊ ለመሆን ራሳችንን በጾም ጸሎት የምንዘጋጅበት ወቅት ነው፡፡ ይህንን የምናደርግ ከሆንን በእርግጥም በብርሃን ውስጥ እየተመላለስን እንገኛለን ማለት ነው ካልሆነም ደግሞ ንስሃ በመግባት ራሳችንን ከጨለማ ወደ ብርሃን እንድናወጣና የብርሃን ጉዞ እንድንጀምር ያስፈልጋል ለዚህም ዘወትር አብራን የምትጓዝ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ታግዘን ጾማችንንም ከእግዚአብሔር ልዩ ጸጋና በረከት የምናገኝበት መንፈሳዊ ሕይወታችንን የምናድስበት ይሁንልን ፡፡

01 March 2019, 15:38