የመጋቢት 01/2011 ዓ.ም ሰንበት ዘቅድስት ምንባባት እና የእግዚኣብሔር ቃል አስተንትኖ የመጋቢት 01/2011 ዓ.ም ሰንበት ዘቅድስት ምንባባት እና የእግዚኣብሔር ቃል አስተንትኖ 

የመጋቢት 01/2011 ዓ.ም ሰንበት ዘቅድስት ምንባባት እና የእግዚኣብሔር ቃል አስተንትኖ

“በምትጾሙበት ጊዜ ግብዞች እንደ ሚያደርጉት የሐዘን ምልክት አታሳዩ”

የእለቱ ምንባባት
1. 1ተሰ. 4፡1-12
2. 1ጴጥ. 1፡13-25
3. ሐዋ.ሥ. 10፡17-29
4. ማቴ 6፡16-24

 

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ “በምትጾሙበት ጊዜ ግብዞች እንደ ሚያደርጉት የሐዘን ምልክት አታሳዩ፣ እነርሱ ጾመኞች መሆናቸውን ሰው እንዲያውቅላቸው የሐዘን ምልክት ያሳያሉ፣ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል። አንተ ግን በምትጾምበት ጊዜ ፊትህን ታጠብ ቅባትም ተቀባ። በዚህ አኳኋን መጾምህን በስውር ካለው አባትህ በቀር ሌላ ማንም አያየውም። በስውር የሚያይ አባትህም ዋጋህን በግልጽ ይከፍልሃል።
ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፣ “ለራሳችሁ በዚህ ምድር ላይ ሐብት አታከማችሁ፣ ምክንያቱም በዚህ ምድር ላይ ብልና ዝገት ያጠፋዋል፣ ሌቦችም ሰብረው ይሰርቁታል። ይልቁንም ለራሳችሁ ሐብት በሰማይ አከማቹ፣ በዚያ ያለውን ሐብት ብል እና ዝገት ሊያጠፋው አይችልም፣ ሌቦች ቆፍረው ሊሰርቁት አይችሉም። ሐብትህ ባለበት ልብህ በእዚያው ይገኛልና።
ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ “ዐይን የሰውነት መብራት ነው፣ ስለዚህ ዐይንህ ጤናማ ከሆነ ሰውነትህ ሁሉ ብሩህ ይሆናል፤ ዓይንህ ግን ታማሚ ከሆነ፥ ሰውነትህ ሁሉ የጨለመ ይሆናል። እንግዲህ በአንተ ያለው ብርሃን ጨለማ ከሆነ፥ ጨለማውስ እንዴት ይበረታ! ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም።

የእለቱ ቃለ እግዚኣብሔር አስተንትኖ


በክርሰቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!
ዛሬ እንደ በቤተክርስቲያናችን ሥርዓት አቆጣጠር ዘቅድስት የተሰኘውን ሰንበትን እናከብራለን ፡፡በዚሁም ዕለት ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ የሚያሳስበን ነገር አለ። ይኸውም “እግዚአብሔር ዘወትር በቅድስና እንድንመላለስ ስለሚፈልግ ምክሩንና ተግሣጹን ጥንትም በተለያየ ዓይነት መንገድ ለልጆቹ ይሰጥ እንደነበረው” ያስተምራቸው እንደነበር ዛሬም ይህን ምክሩንና ተግሣጹን ለኛ ለልጆቹ ይሰጠናል ያስተምረናል፡፡
እርሱ እንደሚነግረን እግዚአበሔርን የሚያስደስተው ምን ዓይነት ሕይወት ነው? እያለ እያንዳዳችንን ይጠይቀናል። እግዚአብሔርን የሚያስደስተው ሕይወት የቅድስና ሕይወት ብቻ ነው። እግዚአብሔር ዘወትር በቅድስና እንድንኖር ይፈልጋል፣ ዘወትርም ነቀፋ የሌለብን ሆነን እንድንገኝ ይፈልጋል። እኛ ሰዎች ሆነን ሳለ፣ ደካሞች ሆነን ሳለ፣ እንዴት ዘወትር በቅድስና መኖርና ዘወትር ነቀፋ የሌለብን ሆነን መገኘት እንችላለን? ይህ ግን የሰው ሐሳብ ነው። እግዚአብሔር ከተጨመረበት የማይቻል ነገር የለም እግዚአብሔር ከተጨመረበት የማንሻገረው ባሕር የለም። እግዚአብሔር ከተጨመረበት የማይፈርስ ግንብ የማይፈነቀል ቋጥኝ የለም፡፡
እግዚአብሔር ስለ እኛ ቅድስና በማሰብ ምሥጢረ ንሰሀን ከሚሥጢራት ውስጥ አንዱ አድርጐ ሰጥቶናል።
ስለዚህ ምሥጢር ንሰሀን በማዘውተር ሁልጊዜ ከኃጢያት ርቀን በቅድስናና ነቀፋ የሌለብን ሆነን መገኘት እንችላለን። ይህንን ካላደረግን ግን በ1ኛ ተሰሎንቄ 3፡12 ላይ እንደተጻፈው “በመንፈሳዊ ሕይወታችን እንጫጫለን በስተመጨረሻም ሞትን እንሞታለን”። ዛሬ በተጨማሪ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በተሰሎንቄ መልእክቱ ሁላችንም የገዛ ሰውነታችንን እንድንቆጣጠር ምክሩን ይለግሰናል። ሁልጊዜ በስሜታችን ብቻ የምንገዛ ከሆነ ስህተት ውስጥ እንወደቃለን።
እግዚአብሔር እንድናስብ ጠለቅ ብለን ነገሮችን እንድንመረምር ሕሊናን ማስተዋልን አእምሮን ሰጥቶናልና ስለዚህ ነገሮች ምን መሆናቸውን እያስተዋልን ክፉውን ከበጎ በመለየት በንጹሕ ሕሊና ፍትሐዊ በሆነ መልኩ ልንጓዝ ያስፈልገናል። በ1ኛ ቆሮ 6፣19 ላይ እንደተፃፈው ሁል ጊዜ የክርስቶስ እንጂ የራሳችን አለመሆናችንን መዘንጋት የለብንም የህም ማለት ነገሮችን ሁሉ ከእርሱ በሚመጣ መንፈስ እንጂ በራሳችን ስሜት ብቻ መፈፀም የለብንም ፡፡
እኛ ክርስቲያኖች አማኞች የሆነን እግዚአብሔርን የምናውቅና በእርሱም ጸጋ የምንመላለስ ሕይወታችን እግዚአብሔርን ከማያውቁ በሥጋዊ አስተሳሰብ ብቻ ከሚመሩ እውነት ከሌላቸው ሰዎች የተለየ በቅድስና የተሞላ ሁል ጊዜም ፍቅርን የሚያንፀባርቅ ሊሆን ይገባዋል። ልክ እምነት እንደሌለው ሠው የምንገድል፣ የምናመነዝር፣ የምንሰርቅ፣ የምንደባደብ፣ የምንዘርፍ ከሆንን፣ የእኛ እምነት ምን ዓይነት እምነት ነው? የኛ ክርስትናስ ምን ዓይነት ክርስትና ነው? የእኛ ቅድስናስ ምን ዓይነት ቅድስና ነው?።
ይልቁንም እግዚአብሔር በሰጠን ጸጋ እየተመላለስን በሥራችን እየተጋን በቅድስና እንድንኖር ያስፈልገናል ምክንያቱም ዕብ 12፣14 ላይ እንደምናገኘው ሁላችን እግዚአብሔር ቅዱስ እንደሆነ እኛም ለቅድስና ተጠርተናልና ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአናጢነት ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ደግሞ በድንኳን ሰፊነት የዕለት ምግቦቸውን ያገኙ እንደነበር፣ እኛም እግዚአብሔር በሰጠን ጸጋ ሥራችንን እያከበርን፣ በእጃችን እየሰራን ዘወትር እየተጋን በቅድስና ልንጓዝ ያስፈልገናል፡፡
በዚሁ በዛሬው 2ኛ ንባብ 1ጴጥ.1፡13-25 ቅዱስ ሐዋርያው ጴጥሮስም ይህንኑ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ የሰጠንን ምክር ይደግምልናል፡፡ በተለይም ለቅድስና መጠራታችንንና ራሳችንን በመግዛት ሰውነታችንን መቆጣጠር እንደሚያስፈልግ ይናገራል፡፡
ራስን መግዛት ከመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች ውስጥ አንዱ መሆንኑ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ለገላትያ በፃፈው መልእክቱ ይናገራል፡፡ ስለዚህ ራሳችንን በመግዛት በቅድስና ለመኖር የሚያስችለንን ነገር ማለትም ቅዱስ ያልሆነውን ነገር ከውስጣችን በማስወገድና ቅዱስ የሆነን ነገር ብቻ በመልበስ በቅድስና እንደንኖር ይጋብዘናል፡፡
እኛ የእግዚአብሔር ልጆች ለመሆን ተጠርተናል ስለዚህም በተጠራንበት ጥሪ መሠረት ልቦናችንን በማዘጋጀት አእምሮአችንን በመንፈስ በማደስና ውስጣችንን ለመልካምነት በማነሳሳት በቅድስና መኖር ያስፈልገናል፡፡ የቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ መልዕክት ወደ ኤፌሶን 4፣1 ላይ በተጠራንበት ጥሪ መሠረት በሚገባ እንድንኖርና እንድንመላለስ ይነግረናል።
በዛሬው ወንጌል ማለትም ማቴ. 6፡16-24 ወንጌላዊው ማቴዎስ እንዴት መጾም እንደሚገባና የጾምን አስፈላጊነት ያስተምረናል። አይሁዳውያን መልካም ሥራን የሚሰሩትና የሚጾሙት _ ለእግዚአበሔር ክብር ሳይሆን በሰዎች ዘንድ ክብርንና ዝናን ለማግኘት ነበር። መጾማቸውም እንዲታወቅ በፊታቸው ላይ ዐመድን ይነሰነሱ ነበር። እኛ ግን መጾም የሚገባን በእግዚአበሔርም ሆነ በሰው ፊት ትሑት ሆኖ ለመገኘት፣ ሥጋችንን ለመቆጣጠርና፣ ከመንፈስ ቅዱስ በሚገኘው ኃይልና ጸጋ አማካኝነት የክርስትናን ሕይወት በቅድስና ለመኖር እንድንችል ነው ፡፡
ትንቢተ ኢሳያስ ኢሳ.58፡1-7 ላይ እንደሚናገረው ጾም ትህትናና የፍቅር ሥራ የተሞላበት ሊሆን እንደሚገባ ይናገራል። ያለ ትህትና ያለ ፍቅር ሥራ የሚደረግ ጾም ከንቱና ግብዝነት ነው ይላል። እኛም የጾምን ዓላማ በመረዳት እውነተኛውን ጾም በመጾም ብልና ዝገት በማያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በማይሰርቁት ቦታ በሰማይ ሃብታችንን ልናከማች ይገባናል፡፡
ሀብትን በምድር ላይ ማከማቸት ለዚህ ምድርም ሆነ ለዘለዓለማዊ ሕይወት ምንም ዋጋ የለውም የሀብታሙን ገበሬ ምሳሌ ለዚህ ዓይነተኛ ማስረጃችን ነው። ሃብታችን ባለበት ልባችንም በዛው ይቀራልና እንዳንዴ ከእግዚአብሔር መንገድም እንድንርቅ ምክንያትም ሊሆን ይችላልና ሀብትን በምድር ላይ ከማከማቸት እንቆጠብ። እግዚአብሔር በሰጠን ፀጋ በመጠን እየኖርን በቅድስና በመመላለስ ዘለዓለማዊ ሀብት በሰማይ ለማከማቸት እንደንችል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጇ ይህንን ጸጋና ብርታት ታሰጠን በልጇ ፊት ዘወትር ጠበቃ ሁና ትቁምልን።
ምንጭ፡ በቫቲካን ሬዲዮ የአማርኛው የስርጭት ክፍል የተዘጋጀ

 

09 March 2019, 10:43