ፈልግ

የዱቦ ሉርድ እመቤታችን ማርያም ቤተመቅደስ የዱቦ ሉርድ እመቤታችን ማርያም ቤተመቅደስ  

የዱቦ ሉርድ እመቤታችን ማርያም ቤተመቅደስ - በኢትዮጵያ

የዱቦ ሉርድ ማርያም የመጀመሪያው ቤተክርስቲያን ሥራ የተጀመረው እ.አ.አ. በየካቲት 27 ቀን 1933 ዓ.ም. ነበር፡፡

የዱቦ ሉርድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተክርስቲያን መሥራች አባ ፓስካል (1874-1950) የሚባሉ የቱሉዝ ካፒቺን አውራጃ አባል የነበሩ ፈረንሳዊ ካፑቺን ነበሩ፡፡ አባ ፓስካል ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ዱቦ ጉብኝት ያደረጉት በከምባታ ጣምባሮ ዞን ከሚገኘው ከጡንጦ ተነሥተው እ.አ.አ. በነሐሴ 15 ቀን 1930 ዓ.ም. ነበር፡፡ እ.አ.አ. በየካቲት 11 ቀን 1931 ዓ.ም. አቡነ እንድርያስ ጃሮሶ በአዲስ አበባ ቤታቸው አባ ፓስካልን ባነጋገሩበት አጋጣሚ የወላይታ ካቶሊክ ሚሲዮን ባልደረባ የሉርድ ማርያም እንድትሆን እንደ ወሰኑም ከአባ ፓስካል ጽሑፍ ለመረዳት ይቻላል፡፡ አባ ፓስካል ራሳቸው ጉዳዩን በማስመልከት እ.አ.አ. በመጋቢት 27 ቀን 1931 ዓ.ም. በጻፉት መልእክታቸው እንዲህ ብለው ነበር፡- “በብፅዕት እመቤታችን ማርያም አማካይነት ጌታችን ኢየሱስ ወደ ዓለም ሊገባ ችሏል፤ በልጇም በመድኃኔዓለም አማካይነት ወደ ወላይታ ገብቷል፡፡”

የዱቦ ሉርድ ማርያም የመጀመሪያው ቤተክርስቲያን ሥራ የተጀመረው እ.አ.አ. በየካቲት 27 ቀን 1933 ዓ.ም. ነበር፡፡ በአጋጣሚውም በጻፉት መልእክታቸው አባ ፓስካል እንዲህ ብለው ነበር፤ “ዛሬ ዱቦ ቅድስት ከተማ ሆናለች፤ ለወላይታም ሕዝብ የእምነት ምንጭ ሆናለች፡፡” የመጀመሪያው የዱቦ ቤተክርስቲያን የተመረቀው እ.አ.አ. በሰኔ 13 ቀን 1933 ዓ.ም. ነበር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከመጀመሪያው ቤተክርስቲያን ተለቅ ያለ ሁለተኛው ቤተክርስቲያን እ.አ.አ. በሚያዝያ 1 ቀን 1934 ዓ.ም. በፋሲካ እሑድ ዕለት እንደ ተመረቀ ከአባ ፓስካል መልእክት ለመረዳት እንችላለን፡፡ እስካሁን በዱቦ ቤተክርስቲያን ውስጥ የሚገኘው ትንሹ የሉርድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሐውልት በአባ ፖስካል አማካይነት ወደ ዱቦ የደረሰው እ.አ.አ. በየካቲት 26 ቀን 1936 ዓ.ም. ነበር፡፡ ከጣልያን ወረራ በኋላ እ.አ.አ. በ1942 ዓ.ም. በዱቦ ቤተክርስቲያን ላይ የቃጠሎ አደጋም ቢደርስ የሉርድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሐውልት ምንም ጉዳት አልደረሰበትም ነበር፡፡

እስካሁን ድረስ በዱቦ የሚገኘው የዱቦ ሉርድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተክርስቲያን የተመረቀው እ.አ.አ. በጥር 13 ቀን 1985 ዓ.ም. በብፁዕ አቡነ ዶሜኒኮ ማሪኖሲ በቀድሞው በሶዶ ሆሣዕና ሀገረስብከት ጳጳስ እጅ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ባሁኑ ጊዜ በቤተክርስቲያኑ ዓመታዊ ክብረ በዓል ዕለት ለሚመጡት በብዙ ሺ ለሚቆጠሩ መንፈሳውያን ተጓዦች ቤተከርስቲያኑ ስለማይበቃ የቅዳሴ ሥነ ሥርዓት የሚካሄደው በድንኳን ውስጥ በቤተክርስቲያን ፊት ለፊት ባለው ሰፊ ቦታ ላይ ነው፡፡ በዱቦ ሉርድ ማርያም ዓመታዊ ክብረ በዓል ላይ ለመሳተፍ ከመላዋ ኢትዮጵያ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሀገረ ስብከቶች እጅግ ብዙ ምእመናን ወደ ዱቦ እንደሚሄዱ ግልጽ ነው፡፡

በተጨማሪም ካለፉት 25 ዓመታት ጀምሮ የመንፈሳውያን ተጓዦች ቁጥር እጅግ እየጨመረ በመሄዱ የዱቦ ሉርድ ማርያም ቤተክርስቲያን የሀገረስብከቱ ዋና ቤተመቅደስ እንዲሆን ብፅዕ አቡነ ዶሜኒኮ ማሪኖሲ በመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በተከበረው የእመቤታችን ማርያም ዓመት (እ.አ.አ. ከሰኔ 7 ቀን 1987 ዓ.ም. እስከ ነሐሴ 15 ቀን 1988 ዓ.ም. ድረስ ተከብሮ የነበረው) መጨረሻ ላይ በይፋ አውጀዋል፡፡ በአጋጣሚውም የሀገረ ስብከቱ ሁለተኛው ቤተመቅደስ በዋሠራ የሚገኘው የቅድስት ተሬዛ ቤተክርስቲያን እንደ ሆነም እንደ ወሰኑ ይነገራል፡፡ ይሁን እንጂ የዱቦ ሉርድ ማርያም ቤተክርስቲያን የሀገረ ስብከቱ ቤተመቅደስ እንዲሆን በሀገረስብከቱ ጳጳስ ቢወሰንም በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ወደ ዱቦ ሉርድ ማርያም ቤተክርስቲያን ለዓመታዊ ክብረ በዓል የሚሄድ የተቀናጀ የመንፈሳውያን ተጓዦች ቡድን አልነበረም፡፡

ለቤተክርስቲያኑ ዓመታዊ ክብረ በዓል ወደ ዱቦ የመንፈሳውያን ተጓዦች ጉዞ የማቀናጀት ሐሳብ የመጣው ከአባ ዮሐንስ ተክለማርያም እንደ ነበረም ይነገራል፡፡ ይኸውም እ.አ.አ. በኀዳር 1998 ዓ.ም. አባ ዮሐንስ ተክለማርያም አባ ተክለሃይማኖት ሙንኤን፣ ወ/ሮ ማሪያ ወልደ ትንሣኤንና ወ/ሮ ቴሬዛ ማሞን በመጥራት  ለዱቦ ሉርድ ማርያም ዓመታዊ ክብረ በዓል የመንፈሳውያን ተጓዦችን ቡድን እንዴት ማጠናከር እንደሚቻል እንደ ተወያዩም ይነገራል፡፡

በዚህ ዐይነት እ.አ.አ. በየካቲት 8 ቀን 1999 ዓ.ም. በአዲስ አበባና በአካባቢው ከተሞች የሚኖሩ የዱቦ ተወላጆች የመጀመሪያውን መንፈሳዊ ጉዞ በአንድነት ወደ ዱቦ ሉርድ ማርያም እንዳደረጉም ይታወሳል፡፡ ይህ ቡድን ነው ለዱቦ ሉርድ ማርያም ዓመታዊ ክብረ በዓል አከባበር ወደ ዱቦ ለሚሄዱት መንፈሳውያን ተጓዦች ከፍተኛ ቅስቀሳ ያደረገው፡፡ የእግዚአብሔርም ዓላማ ከዚህ ቡድን ጀርባ እንደ ሆነም ይታመናል፡፡ ባሁኑ ጊዜ የዱቦ ሉርድ ማርያምን ቤተክርስቲያን በትልቁ የመሥራት ፕሮግራም ተወጥኗል፡፡ የቤተክርስቲያኑም አገልጋዮች የካፑቺን ወንድሞች ስለ ሆኑ የኢትዮጵያ ካፑቺን ማኀበር አለቃ የዱቦ ሉርድ ማርያም አዲስ ቤተመቅደስ ሥራ አስተባባሪ ኮሚሽን እ.አ.አ. በኀዳር 16 ቀን 2016 ዓ.ም. አቋቁሟል፡፡ የሶዶ ሀገረስብከት ጳጳስም ውሳኔውን በሙሉ ልብ አጽድቀዋል፡፡ በርግጥ ብፁዕ አቡነ ፀጋዬ ቀኔኒ፣ የሶዶ ሀገረስብከት ጳጳስ፣ ከብፁዕ አቡነ ወልደጊዮርጊስ ማቴዎስ፣ የሆሣዕና ሀገረስብከት  ጳጳስ ጋር ሆነው እ.አ.አ. በየካቲት 12 ቀን 2017 ዓ.ም. በቤተክርስቲያኑ ዓመታዊ ክብረ በዓል ዕለት በብዙ ሺ ምእመናን ታጅበው የአዲሱን የዱቦ ሉርድ ማርያም ቤተመቅደስ የመሠረት ድንጋይ አስቀምጠዋል፡፡ የዱቦ ሉርድ ማርያም ቤተመቅደስ ከፈረንሳይ ታዋቂው የሉርድ ማርያም ቤተመቅደስም ጋር ልዩ ግንኙነት እንደሚኖረው ተስፋ አለ፡፡

ምንጭ፡ በዶ/ር አባ አንጦንዮስ አልቤርቶ ካፑቺን በተዘጋጀው ታዋቂ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የካቶሊክ ቤተመቅደሶች በዓለም ላይ ከሚለው መጽሐፍ ከገጽ 169-171 ላይ የተወሰደ እና በአባ ኃ/ገብርኤል መለቁ የተጻፈ።

09 February 2019, 11:00