በአቡ ዳቢ የተሰበሰቡት የተለያዩ የእምነት ተቋማት መሪዎች በአቡ ዳቢ የተሰበሰቡት የተለያዩ የእምነት ተቋማት መሪዎች  

በአቡ ዳቢ የተሰበሰቡት የተለያዩ የእምነት ተቋማት መሪዎች አስተያየታቸውን እያካፈሉ መሆናቸው ተገለጸ።

“የሰላም መሣሪያ አድርገኝ” በሚል ርዕሥ የተዘጋጀው ይህ የተለያዩ የእምነት ተቋማት መሪዎች ስብሰባ ዋና ትኩረቱ በሰላም አብሮ መኖርን፣ መቻቻልን፣ ከፋፋይ ርዕዮተ ዓለማዊ አስተሳሰቦች መወገድ እንዳለባቸው የሚያሳስቡ ሐይማኖታዊ እሴቶችን በጋራ ለመመልከት እንደሆነ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከጥር 26 – 28 ቀን 2011 ዓ. ም. ድረስ፣ “ሰብዓዊ ወንድማማችነት” በሚል መሪ ቃል፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዋና ከተማ በሆነችው በአቡ ዳቢ የተሰበሰቡት የተለያዩ የእምነት ተቋማት መሪዎች እና ተወካዮች በጋራ ያካሄዱትን ስብሰባ በማስመልከት አስተያየቶችን መስጠት መጀመራቸው ታውቋል።

ወደ አረቡ ባሕረ ሰላጤ አገሮች ሲጓዙ የመጀመሪያው የሆኑት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ባደረጉበት 27ኛው ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት ከተለያዩ የእምነት ተቋማት መሪዎች ጋር ሆነው ስብሰባውን መካፈላቸው ታውቋል።  

“የሰላም መሣሪያ አድርገኝ” በሚል ርዕሥ የተዘጋጀው ይህ የተለያዩ የእምነት ተቋማት መሪዎች ስብሰባ ዋና ትኩረቱ በሰላም አብሮ መኖርን፣ መቻቻልን፣ ከፋፋይ ርዕዮተ ዓለማዊ አስተሳሰቦች መወገድ እንዳለባቸው የሚያሳስቡ ሐይማኖታዊ እሴቶችን በጋራ ለመመልከት እንደሆነ ታውቋል። ይህን ስብሰባ ለመካፈል በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዋና ከተማ በሆነችው በአቡ ዳቢ የተገኙት የተለያዩ የእምነት መሪዎች እና ተወካዮች በስብሰባቸው ማግስት አስተያየቶቻቸውን መስጠታቸው ታውቋል።

በሰሜናዊው የአረብ አገሮች ማለትም የኩዌት፣ የባሕሬን፣ የካታር እና የስውዲ አረቢያ ካቶሊካዊ ሐዋርያዊ አስተዳደር ጳጳስ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ባሊኒ ካሚሎ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት እንደገለጹት በተለያዩ የእምነት መሪዎች እና ተወካዮች መካከል የተደረገውን ስብሰባ አድንቀው በሕዝቦች መካከል የተሻለ ግንኙነት እንዲታይ ያደርጋል ብለዋል። ብጹዕ ባሊኒ በንግግራቸው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በስብሰባው ላይ መገኘት ብርታትን በመስጠት በህዝቡ አእምሮ ውስጥ ከዚህ በፊት ከነበረው አስተሳሰብ የተለየ አስተሳሰብ ይፈጥራል ብለዋል። ብጹዕ አቡነ ባሊኒ በማከልም መቻቻል ከሚለው ቃል ይልቅ ወንድማማችነት የሚለውን እንደሚመርጡ ለዚህም ምክንያቱም ወንድማማችነት የሚለው ቃል በሕዝቦች መካከል ሊኖር የሚገባውን እኩልነት የበለጠ ስለሚገልጽ ነው ብለው፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ወደ ተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት በሌሎች የአረብ ባሕረ ሰላጤ አገሮችም ቢደረግ መልካም ይሆናል ብለዋል።

በአቡ ዳቢ ከተማ የተካሄደውን የተለያዩ የእምነት መሪዎች ስብሰባን የተካፈሉት እና በዮርዳኖስ እና በቅድስት አገር ኢየሩሳሌም የሉተራን ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን ተወካይ የነበሩት ብጹዕ አቡነ ሙኒም ዩናን በበኩላቸው፣ ስብሰባውን መካፈላቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸው በቅድሚያ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮ እና የአል አዛር ታላቁ ኢማም አል ጣይብ በስብሰባው ላይ መገኘታቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸው፣ በዓለማችን የሚታየው ትልቁ ችግር ክርስትና ወይም እስልምና ሳይሆን በአይሁድ፣ በክርስትና እና በእስልምና ተከታዮች ዘንድ የሚንጸባረቅ የአክራሪነት አቋም ነው ብለው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በስብሰባው መገኘታቸው በተለያዩ ሐይማኖቶች መካከል እርቅን ለማውረድ ትልቅ እገዛን ይሰጣል ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት በአረብ አገር የሚገኙ ክርስቲያኖችን ለማስታወስ እንደሚረዳ ገልጸው፣ የክርስትና እምነት በአረቡ ዓለም የታየው መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ ከወረደበት ጊዜ አንስቶ መሆኑን ብዙ የዓለማችን ሕዝብ አያውቀውም ብለዋል። በክልሉ የሚገኙ ክርስቲያኖች እንደሌሎች የአረብ አገር ሙስሊሞች መንፈሳዊ እና ባሕላዊ እሴቶችን አክብረው እና ጠብቀው እስከ አቆይተዋል ብለዋል። በማከልም በአረብ አገሮች የሚገኙ ክርስቲያኖች የሰለጠነ ማሕበረሰብን በመገንባት፣ ሰብዓዊ መብቶችን በማክበር፣ የሐይማኖት ነጻነትን እና የዜጎች ነጻነትን በማክበር፣ በተለያዩ ጾታዎች መካከል ፍትህ እንዲኖር በማድረግ እና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ነጻነትን በማክበር ትልቅ አስተዋጽዖን ማድረጋቸውን አስታውሰዋል። አቡነ ዩናን በመጨረሻም የተለያዩ የእምነት መሪዎች በጋራ ሆነን ወንድማማችነትን፣ ፍትህ እና ሰላምን በዓለማችን እና በቅድስት አገር፣ በኢየሩሳሌምም መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።

በአቡ ዳቢ ከተማ የተካሄደውን የተለያዩ እምነት መሪዎች ስብሰባን የተካፈሉት እና በፖላንድ የአይሁድ እምነት ከፍተኛ መምህር የሆኑት ሚካኤል ሹድሪክ በበኩላቸው አንድ የአይሁድ እምነት ተቋም መሪ በአረብ አገር ሊገኝ ወይም አንድ የአይሁድ እምነት ተከታይ ከእስልምና እምነት ተከታይ ጋር መነጋገር እንደማይችል ገልጸው የእርሳቸው በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መገኘት በሁለቱ እምነቶች መካከል ያለውን መቃቃር እንደሚያረግበው ገልጸዋል። መምህር ሚካኤል በማስከተል እርሳቸው በመጡበት በፖላንድ ከሚገኙ 30 ሚሊዮን ሕዝብ መካከል 3 ሚሊዮን የአይሁድ እምነት 3 ሚሊዮን የክርስትና እምነት ተከታዮች በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት መገደላቸውን አስታውሰዋል። እንደ አንድ የእምነት ተቋም መሪ፣ ካለኝ ሃላፊነት በላይ፣ ያንን የመሰለ ጭፍጨፋ እንዳይደገም ሰላምን  ለማንገስ የሚያግዙ መንገዶችን የማስተማር ሃላፊነትም አለብኝ ብለዋል። በመጨረሻም በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የተካሄደውን የተለያዩ እምነቶች መሪዎች ስብሰባን ለመካፈል መብቃታቸው ትልቅ እድል ነው ብለዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
06 February 2019, 14:04