የፓኪስታን ምዕመናን በጸሎት ላይ የፓኪስታን ምዕመናን በጸሎት ላይ 

የፓክስታን ቤተክርስቲያን አዲሱ የጎርጎሮሳዊያኑ ዓመት የውይይት ዓመት እንደሚሆን አስታወቀች።

ብጹዕ አቡነ ሰባስቲያን ፍራንሲስ ሻው ለፊደስ የዜና አውታር እንዳስረዱት በግለ ሰቦች መካከል፣ በቤተሰብ መካከል፣ በማሕበረሰብ መካከልና በተለያዩ የእምነት ክፍሎች መካከል የሚደረግ ውይይት በሰዎች መካከል አዲስ ተስፋን ለማግኘት፣ አለመግባባቶችን ለማስወገድ እና ግንኙነቶችን ለማጠናከር ይረዳል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በፓክስታን የሚገኝ የላሆረ ቤተክርስቲያን አዲስ የገባው የጎርጎሮሳዊያኑ 2019 ዓ. ም. በግለ ሰቦች መካከል፣ በቤተሰብ መካከል፣ በማሕበረሰብ መካከልና በተለያዩ የእምነት ክፍሎች መካከል ውይይት በማድረግ በመካከላቸው ያለውን ግንኙነት የሚያጠናክሩበትና አዲስ ተስፋን የሚያገኙበት ዓመት እንደሚሆን የላሆረ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሰባስቲያን ፍራንሲስ ሻው ተናግረዋል።

ዛሬ ሰዎች ዘመናዊና ፈጣን የመገናኛ መሣሪያዎችን ለመጠቀም ዕድል ያገኙ ቢሆንም በቂ ጊዜ የላቸውም። ነገር ግን ቢጠቀሙ ኖሮ እነዚህ የመገናኛ መሣሪያዎች እርስ በርስ ለመወያየት ምቹ በመሆናቸው ማበረታታት ያስፈልጋል ብለዋል። የጋራ ውይይትም ማሕበራዊ ሕይወትን ለማሳደግና ብሎም ለሰላም ዋና መንገድ ነው ብለዋል። ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሰባስቲያን ፍራንሲስ ሻው፣ ፊደስ ከተሰኘ የዜና አውታር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ መሆኑ ታውቋል። አቡነ ሰባስቲያን ፍራንሲስ ሻው፣ እርሳቸው በሚያገለግሉት በላሆረ ሀገረ ስብከት፣ አዲሱ የጎርጎሮርሳዊያኑ 2019 ዓ. ም. ለምዕመናኑም ሆነ በአካባቢው ለሚገኙት ማሕበረሰብ የውይይት ዓመት እንደሚሆን፣ በሃገረ ስብከታቸው በሚገኝ የተሃድሶ ማዕከል ውስጥ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ወቅት ተናግረዋል።

የጋራ ውይይት በሁሉም ዘንድ አዲስ ተስፋን ሊያስገኝ ይችላል፣

ብጹዕ አቡነ ሰባስቲያን ፍራንሲስ ሻው ለፊደስ የዜና አውታር እንዳስረዱት በግለ ሰቦች መካከል፣ በቤተሰብ መካከል፣ በማሕበረሰብ መካከልና በተለያዩ የእምነት ክፍሎች መካከል የሚደረግ ውይይት በሰዎች መካከል አዲስ ተስፋን ለማግኘት፣ አለመግባባቶችን ለማስወገድ እና ግንኙነቶችን ለማጠናከር ይረዳል ብለዋል። አቡነ ሰባስቲያን ፍራንሲስ ንግግራቸውን በመቀጠል፣ ቅዱሳት መጽሐፍትን በምናነብበት ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር እንደምንነጋገርና እንደምንወያይ እናውቃለን ብለው፣ ከእግዚአብሔር ጋር የሚደረግ ውይይት የተጀመረው በብሉይ ኪዳን፣ በዘፍጥረት ምዕ. 3, 9 ላይ እግዚአብሔር ከአዳም ጋር ካደረገው ውይይት ይጀምራል ብለው፣ እግዚአብሔርም በዚህ ሁኔታ ከሰው ዘር ጋር ግንኙነቱን ሊያጸና ይፈልጋል ብለዋል። አቡነ ሰባስቲያን ፍራንሲስ ሻው በማከልም በአገራቸው የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የአዲሱ የጎርጎሮርሳዊያኑ 2019 ዓ. ም. ተልዕኮ በምዕመናኑ መካከል ያለውን ግንኙነት በውይይት ማጠናከር እንደሆነ ገልጸዋል።

እግዚአብሔር ከሰው ዘር ጋር ግንኙነቱን አጸና፣

እግዚአብሔር አብርሃምን ንብረቱን፣ ቤተሰቡን፣ አገሩን ትቶ እንዲሄድ፣ ሙሴንም የእስራኤል ሕዝብ ነጻነትን ያገኝ ዘንድ ከፌሪኦን ጋር እንዲስማማ መናገሩን የገለጹት አቡነ ሰባስቲያን በአዲስ ኪዳንም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከቅዱስ ገብርኤል ጋር በመነጋገር የእግዚ አብሄርን እቅድ ማወቅ መቻሏን ገልጸው፣ ውይይት በሁሉም የኑሮ ደረጃ ላይ በሚገኝ ማሕበረሰብ ዘንድ መከናወን ያለበት መሆኑን ገልጸው በቤተሰብ መካከል፣ ካህናት ከቁምሳናዎቻቸው መንፈሳዊ ማሕበራት ጋር፣ ከምዕመናን ሐዋርያዊ ምክር ቤቶች ጋር፣ የተለያዩ እምነት ተከታዮችም ጭምር በመካከላቸው እርስ በርስ መወያየት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

በሐይማኖት መሪዎችና በካከልና በሕዝባዊ ተቋማትም መካከል ውይይት እንዲኖር ያስፈልጋል፣

ከአዲሱ የጎርጎሮሳዊያኑ 2019 ዓ. ም. እቅዶች አንዱ በሐይማኖቶች መካከል የሚደረግ ውይይት እንደሆነ የገለጡት አቡነ ሰባስቲያን ፍራንሲስ፣ በተለይም በክርስቲያኖችና በእስልምና እምነቶች መካከል የሚደረግ ውይይት እንደሆነ ገልጸው ይህን ተግባራዊ ለማደርግ ካህናትን፣ ደናግልን፣ ወጣቶችንና መምህራንን እንደሚያዘጋጁ ገልጸዋል።   

09 January 2019, 15:46