በኪንሻሳ የሕዝብ ድምጽ ቆጠራ ሲካሄድ በኪንሻሳ የሕዝብ ድምጽ ቆጠራ ሲካሄድ 

የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ብጹዓን ጳጳሳት የምርጫ ድምጽ ውጤት ይፋ እንዲሆን ጠየቁ።

ክቡር አባ ንሾሌ፣ በሃገሪቱ ሊካሄዱ የታቀዱት በርካታ የምርጫ ቀናት ላልተወሰነ ጊዜ ሲራዘሙ መቆየታቸውን ገልጸው ለዚህም ምክንያቶቹ በሃገሪቱ የሚታየው የጸጥታ አለመረጋጋት፣ በምርጫ ምዝገባ ሥርዓት አለመደሰትና የኤሌክትሮኒክ የድምጽ መስጫ ማሽኖች ስምሪት በፈጠረው ቅሬታ እንደነበሩ አስረድተዋል። አባ ንሾሌ በንግግራቸው፣ ዘንድሮ በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ፕሬዚደንታዊ ምርጫን ለማድረግ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ታሕሳስ 22 ቀን 2009 ዓ. ም. በአደራዳሪነት የተጫወቱት ሚና ለስምምነት መንገድ እንደከፈተ አስታውሰው አመስግነዋቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ፣ ታሕሳስ 21 ቀን 2011 ዓ. ም. የተካሄደው ፕሬዚደንታዊ የምርጫ ድምጽ ውጤት ይፋ እንዲሆን የአገሪቱ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት የምርጫ ቦርዱን ጠየቁ። የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ብጹዓን ጳጳሳት በአገራቸው የተካሄደውን ፕሬዚደንታዊ ምርጫን በማስመልከት ሐሙስ ዕለት ባቀረቡት ሪፖርታቸው፣ ነፃ ብሔራዊ የምርጫ ኮሚሽኑ የኮንጎ ዴሞክርቲክ ሪፓብሊክ ሕዝብ ቀጣዩን ፕሬዚደንታቸውን ለመምረጥ የሰጠው ድምጽ ትክክለኛውና ፍትሐዊ ውጤት እንዲያደርግ ጠይቀዋል። የምርጫ ኮሚሽኑም የሕዝቡን የድምጽ አሰጣጥ የሚከታተሉ፣ ከ40,000 በላይ የምርጫ ታዛቢዎችን በመላው የአገሪቱ ክፍሎች ማሰማራቱ ታውቋል።  

የኮንጎ ሕዝብ ምኞቱን ድምጽን በመስጠት ገልጿል፣

የምርጫ ድምጽ አሰጣጥን በቅርብ ሆነው እንዲከታተሉ የተላኩት የታዛቢዎች ቡድን በሪፖርቱ እንደገለጸው በጥቂት ቦታዎች የታዩት ይህ ነው የማይባሉ እንቅፋቶች ቢኖሩም በምርጫው ሂደት ላይ የጎላ ጉዳትን ያላስከተሉ፣ ነገር ግን የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ሕዝብ በምርጫው ዕለት ምኞቱንና የሚፈልገውን፣ ድምጽ በመስጠት የገለጸበት እንደሆነ አስረድቷል።

ምርጫው የተሳካለት ነበር ማለት ይቻላል፣

ከደቡብ አፍሪቃ ልማት ማሕበረሰብ የተጋበዙት የምርጫ ታዛቢ ቡድን ረቡዕ ዕለት በሰጠው መግለጫ በአንዳንድ የሃገሪቱ ክፍሎች አለመረጋጋቶች ቢታዩም ምርጫው ከሞላ ጎደል በጥሩ ሁኔታ ተካሂዷል ማለት ይቻላል ብሎ፣ እሁድ ታሕሳስ 21 ቀን 2011 ዓ. ም. የተካሄደው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ፣ አብዛኛው የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ሕዝብ መሪውን በነጻነት የመምረጥ መብቱን የገለጠበት እንደነበር አስረድቷል። ቡድኑ አክሎም የምርጭ ድምጽ ቆጠራም ግልጽ እንደነበርና እንዲታዘብም በተሰጡት 59 ከመቶ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ የድምጽ አሰጣጡ ሂደት የተጀመረው የተቀመጠለትን የጊዜ ሰሌዳን የተከተለ፣ የጸጥታ አስከባሪዎችም ግዴታቸውን በሰላማዊ መንገድ የተወጡበት እንደነበር ገልጿል። በሌላ ወገን ከሃገር ውስጥ የተወጣጣው የምርጫ ታዛቢ ቡድን በበኩሉ ሐሙስ ዕለት ባቀረበው ሪፖርቱ የድምጽ አሰጣጡ ሂደት ብዙ አለመረጋጋቶች የተከሰቱበት ቢሆንም ነገር ግን የድምጽ ማጭበርበር ተግባር አልታየበትም ብሏል።

የታሕሳስ 22 ቀን 2009 ዓ. ም. ስምምነት ብሔራዊ ምርጫ እንዲካሄድ መንገድ ከፍቷል፣

ከካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በኩል የሆኑት ክቡር አባ ንሾሌ፣ በሃገሪቱ ሊካሄዱ የታቀዱት በርካታ የምርጫ ቀናት ላልተወሰነ ጊዜ ሲራዘሙ መቆየታቸውን ገልጸው ለዚህም ምክንያቶቹ በሃገሪቱ የሚታየው የጸጥታ አለመረጋጋት፣ በምርጫ ምዝገባ ሥርዓት አለመደሰትና የኤሌክትሮኒክ የድምጽ መስጫ ማሽኖች ስምሪት በፈጠረው ቅሬታ እንደነበሩ አስረድተዋል። አባ ንሾሌ በንግግራቸው፣ ዘንድሮ በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ፕሬዚደንታዊ ምርጫን ለማድረግ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ታሕሳስ 22 ቀን 2009 ዓ. ም. በአደራዳሪነት የተጫወቱት ሚና ለስምምነት መንገድ እንደከፈተ አስታውሰው አመስግነዋቸዋል።

በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ፣ ታሕሳስ 21 ቀን 2011 ዓ. ም. በተካሄደው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ፣ ከበኒ ግዛት ሕዝብ፣ በሰሜን ኪቩ ግዛት ከቡቴምቤ ሕዝብና፣ በዩምቢ ግዛት ከማይ ንዶምቤ ሕዝብ በስተቀር አብዛኛው የአገሪቱ ሕዝብ ድምጹን የሰጠበት እንደነበር ተገልጿል። የመንግስት ባለስልጣናትም ምርጫው እንዲራዘም የተደረገበት ምክንያት በአገሪቱ በተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝና በጸጥታ መጓደል ምክንያት እንደነበር ገልጿል። ላለፉት 17 ዓመታት ሃገሪቱን በፕሬዚደንትነት የመሩትን ዮሴፍ ካቢላን ለመተካት ለምርጫ የቀረቡት ግንባር ቀደም ተወዳዳሪዎችም ተቃዋሚዮቻቸው ማርቲን ፋዩሉ እና ፌሊክስ ሺሴከዲ ሲሆኑ፣ ዮሴፍ ካቢላም እርሳቸውን እንዲተኳቸው ያቀረቧቸው የቀድሞ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩ አማኑ ኤል ራማዛኒ ሻዳሪ መሆናቸው ታውቋል።

05 January 2019, 16:26