የ47 ዓመት ዕድሜ ባለ ጸጋ አሲያ ቢቢ የ47 ዓመት ዕድሜ ባለ ጸጋ አሲያ ቢቢ  

የፓክስታን ከፍተኛ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አሲያ ቢቢ ምህረት ማግኘቷን አረጋገጠ።

በጥቅምት ወር አሲያ ቢቢ ነጻ መለቀቋ በአገሪቱ በሚገኙ እስልምና አክራሪዎች ዘንድ ቁጣን በማስነሳቱ በመላው የሃገሪቱ ክፍሎች አመጽ የታከሉበት ሰልፎች ሲካሄዱ መቆየታቸው የሚታወስ ሲሆን በኋላ ግን የአሲያ ቢቢ ጉዳይ በይግባኝ እንደገና እንዲታይ ሲደረግ መቀዝቀዙ ይታወሳል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በፓክስታን የሃገሩ ከፍተኛ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የእስምናን ሐይማኖት አጉድፋለች፣ የነቢዩን መሐመድ ስም አጥፍታለች በሚል ወንጀል የሐሰት ክስ የተመሠረተባትንና ከአገርም እንዳትወጣ የተከለከለች አሲያ ቢቢ በምሕረት መለቀቋን አስታውቋል። የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ወሳኔ በአገሪቱ የመልካም ለውጥ ጅማሬ ነው ተብሏል። አሲያ ቢቢ ከዚህ በፊት የሞት ፍርድ የተፈረደባት እና ለዘጠኝ ዓመት ታስራ መቆየቷ ታውቋል። ዛሬ አሲያ ቢቢ ከተበየነባት ፍርድ ነጻ በመሆን ከአገርም ለመውጣት የሚያስችል ነጻነት ማግኘቷን ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ይፋ አድርጓል።

በቀድሞው ክስም ምንም ስህተት አልተገኘባትም፣

ለአሲያ ቢቢ የተሰጠውን የምህርት ፍርድ ካጸደቁላት ሦስት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች መካከል አንዱና የፍርድ ቤቱ ፕሬዚደንት የሆኑት አሲፍ ሳኢድ ኮሳ እንደገለጹት በአሲያ ቢቢ ክስ የመሠረቱት የእስልምና እምነት ተከታይ የሆኑት ቃሪ ሳላም፣ እንደ ጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር 2009 ዓ. ም. ላቀረቡት የክስ ሰነድ ማስረጃን ማቅረብ አለመቻላቸውን ተከትሎ የፓክስታን ከፍተኛ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አሲያ ቢቢን ነጻ ሊያሰናብት መወሰኑን ገልጸዋል። 

በንጹሐን ላይ መፍረድ አይቻልም፣

የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዚደንት አሲፍ ሳኢድ ኮሳ እንደገለጹት የአሲያ ቢቢ ከሳሽ የተጠየቁትን ማስረጃ ማቅረብ ካለመቻል በተጨማሪ ምስክሮችንም ማቅረብ አልቻሉም ብለው እስላማዊ ፍርድ ቤትስ ቢሆን ምንም ጥፋት ባልተገኘበት ተከሳሽ ምን ዓይነይ ፍርድሊሰጥ ይችላል ብለዋል።

አሲያ ቢቢ ከልጆቿ ጋር ልትቀላቀል ትችላለች፣

ከ9 ዓመት እስራት በኋላ ባለፈው የጥቅምት ወር የፓክስታን ጠቅላይ ፍርድ ነጻ እንድትሆን ያደረጋት አሲያ በአገሯ የግድያ ዛቻና ማስፈራሪያ ስለሚደረግባት ወደ አንድ ያልታወቀ ድብቅ ስፍራ መወሰዷ እና በዚያም ከባሏ አሺክ ማሲ ጋር እንድትቀመጥ መደረጉ ይታወሳል። በጥቅምት ወር አሲያ ቢቢ ነጻ መለቀቋ በአገሪቱ በሚገኙ እስልምና አክራሪዎች ዘንድ ቁጣን በማስነሳቱ በመላው የሃገሪቱ ክፍሎች አመጽ የታከሉበት ሰልፎች ሲካሄዱ መቆየታቸው የሚታወስ ሲሆን በኋላ ግን የአሲያ ቢቢ ጉዳይ በይግባኝ እንደገና እንዲታይ ሲደረግ መቀዝቀዙ ይታወሳል። የአሲያ ቢቢ ባለቤት አሺክ ማሲ፣ ለአሜርካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ለእንግሊዟ ጠቅላይ ሚንስትር ተሬዛ ሜይ እና ለካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጃስቲን ትሩዶ የፖለቲካ ጥገኝነት ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው እንዲሰጣቸው ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወሳል። አቶ አሺክ ማሲ ለእነዚህ ሦስት የመንግሥታት መሪዎች በቪዲዮ ምስል በኩል ባቀረቡት ተማጽኖ እርሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ከሚደርስባቸው ጥቃት ለመከላከል የተቻላቸውን ሁሉ እንዲያደርጉላቸው መጠየቃቸው ይታወሳል።   

በእስልምና እምነት ላይ ለሚፈጸም "የስድብ ቃል" ላይ ድል የተቀዳጀበት፣

በእስልምና እምነት ሕግ መሠረት፣ የነቢዩ መሐመድ ስም ማጥፋት እና በቅዱስ ቁርዓን ላይ የሚሰነዘር "የስድብ ቃል" የሞት ፍርድ ቅጣትን የሚያስከትል መሆኑ ሲታወቅ ነገር ግን ተግባራዊነቱ በዓለም ዙሪያ ጥያቄን እያስነሳ መጥቷል ተብሏል።

የ47 ዓመት ዕድሜ ባለ ጸጋ አሲያ ቢቢ የካቶሊክ እምነት ተከታይ እና የ5 ልጆች እናት መሆኗ ታውቋል። የአሲያ ቢቢ ልጅ ኤሻም ከአባቷ ከአሺክ ማሲ ጋር በመሆን ባለፈው ዓመት የካቲት ወር 2010 ዓ. ም. ወደ ሮም መጥተው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ማግኘታቸውና በወቅቱም በሮም ከተማ ታላቅ የጸሎት ስነ ስርዓት መፈጸሙ ይታወሳል። ኤሻም ከአባቷ ጋር በመሆን ወደ ሮም ከመጓዟ ከጥቂት ቀናት በፊት እስር ቤት የነበረች እናቷን እንደጎበኘቻት እና ወደ ሮም በምታደርገው ጉብኝት ወቅት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን እንደምታገኛቸው እና በሮም ከተማ የሚገኘው ኮሎሴውም በቀይ መብራት ደምቆ፣ መላው የዓለም ሕዝብም በጸሎት እንደሚያስታውሳት መናገሯ ይታወሳል። አሲያ ቢቢም በልጇ በኩል ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ልባዊ ሰላምታዋን መላኳ ሲታወስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ኤሻምንና የኤሻምን አባት በቫቲካን ተቀብለው ባነጋገሯቸው ወቅት፣ አሲያ ቢቢን በጸሎታቸው እንደምያስታውሷት ገልጸው አሲያ ቢቢ ጠንካራ ሰማዕት መሆኗን መናገራቸው ይታወሳል።

30 January 2019, 16:22