ፈልግ

የአሲሲው ቅዱስ ፍራንችስኮ እና የግብጹ ሱልጣን ኣል ካሚል ግንኙነት ከ800 ዓመት በፊት የአሲሲው ቅዱስ ፍራንችስኮ እና የግብጹ ሱልጣን ኣል ካሚል ግንኙነት ከ800 ዓመት በፊት  

በፓክስታን 800ኛ ዓመት የሰላም ውይይት መታሰቢያ ቀን ተከበረ።

በፓክስታን የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት እና ውህደት ብሔራዊ ምክር ቤት ከፓክስታን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ጋር በመተባበር በአገሪቱ ወደ ይቅርታ፣ ወደ ሰላም እና ወደ ወንድማማችነት ጎዳና የሚመሩ በርካታ መልዕክቶችን ሲለዋወጡ መቆየታቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በክርስትና እና በእስልምና እምነቶች መካከል ሲደረግ ለቆየው የሰላም ውይይት ቀዳሚ ተጠቃሽ የሆነው የአሲሲው ቅዱስ ፍራንችስኮስና የግብጹ ሱልጣን ኣል ካሚል ተገናኝተው ስለ ሰላም የተወያዩበት 800ኛ ዓመት በፓክስታን መከበሩ ተገልጿል። የፓክስታን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ብጹዕ አቡነ ሰባስቲያን ፍራንሲስ ሻው፣ ዕለቱን በማስታወስ ዛሬም ቢሆን የሰላም መልዕክተኞች ልንሆን ይገባል ብለዋል።

ከ800 ዓመት በፊት በሜዲተራኒያን አካባቢ አገሮች መካከል ሰላም በጠፋበት፣ በሕዝቦች መካከል ጥላቻ በተስፋፋበት ዘመን የአሲሲው ቅዱስ ፍራንችስኮስ የሰላም መልዕክትን በመያዝ ወደ ግብጽ ያቀናበት ዘመን እንደነበር ይታወሳል። ግጭቶች ወደ ተስፋፉባቸው አካባቢዎች ከመጓዙ በፊት፣ ቅዱስ ፍራንችስኮስ በወቅቱ የመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ከነበሩት ከኦኖሪዮ ሦስተኛ እጅ ቡራኬንና መልካም ፈቃድ ማግኘቱ ይታወቃል። ከግብጽ ዋና ከተማ ከካይሮ ወጣ ብሎ በጥቂት ኪሎ ሜትር ርቀት በሚገኝ፣ ዳሜታ በሚባል አካባቢ ይኖሩ የነበሩትና በዘመኑ የግብጽ ሱላጣን ከነበሩት ማሊክ ኣል ካሚል ጋር ቅዱስ ፍራንችስኮስ መገናኘቱ ይታወሳል። የሁለቱ እምነቶች ተጠቃሽ ሰዎች ተገናኝተው ስለ ሰላም መወያየታቸው ብዙ ፋይዳ ባይሰጠውም ቅዱስ ፍራንችስኮስ ከሚኖርበት አገር ተነስቶ ወደ ወደ እስልምና እምነት ተከታዮች መካከል የሄደበት የሰላም ተልዕኮ፣ ዛሬ ለምስራቁ እና ለምዕራቡ ዓለም ሰላማዊ ግንኙነት መልካም ምሳሌ ሆኖ መገኘቱ ይነገራል።  

የበዓሉ አከባበር በፓክስታን፣

ከስምንት መቶ ዓመት በፊት፣ በክርስትና እና በእስልምና እምነቶች መካከል የተካሄደው የሰላም ውይይት ቀጣይነት እንዲኖረው በማለት በፓክስታን የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት እና ውህደት ብሔራዊ ምክር ቤት ከፓክስታን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ጋር በመተባበር በአገሪቱ ወደ ይቅርታ፣ ወደ ሰላም እና ወደ ወንድማማችነት ጎዳና የሚመሩ በርካታ መልዕክቶችን ሲለዋወጡ መቆየታቸው ታውቋል። ዘንድሮ በፓክስታን፣ ላሆሬ ሃገረ ስብከት ውስጥ በተከበረው 800ኛ ዓመት የሰላም ውይይት መታሰቢያ በዓል ላይ የፓክስታን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት እና የላሆሬ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሰባስቲያን ሻው፣ ከእርሳቸውም ጋር በፓክስታን የፍራንችስካዊያን ካፑቺን ታናናሽ ወንድሞች ማሕበር አለቃ አባ ፍራንሲስ ናዲም፣ በፓክስታን የሐይማኖቶች የጋራ ውይይት እና ውህደት ብሔራዊ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ፣ የፍራንችስካዊያን ማሕበር አባላት፣ ካህናት፣ ደናግል፣ ምዕመናን፣ ከእስልምና እምነት በኩል ከአካባቢው አገሮች ጨምሮ ታዋቂ ምሁራን መገኘታቸው ታውቋል።

ከሰላም ውይይት አካባቢ የሚመነጩ ሃሳቦች፣

ከስምንት መቶ ዓመት በፊት፣ ጦርነትና ጥላቻ በነገሰበት ወቅት የሰላምንና የይቅርታን መልዕክት ይዘው የተነሱት፣ በክርስትና እምነት በኩል፣ በኢጣሊያ ውስጥ የአሲሲው ቅዱስ ፍራንችስኮ እና በእስልምና እምነት በኩል የግብጹ ሱልጣን ኣል ካሚል መሆናቸውን በፓክስታን የፍራንችስካዊያን ካፑቺን ታናናሽ ወንድሞች ማሕበር አለቃ የሆኑት አባ ፍራንሲስ ናዲም ገልጸው እነዚህ የሰላምና የይቅርታ ምሳሌ የሆኑት ሁለቱ ጓደኛሞች ለሐይማኖቶች የጋራ የሰላምና የእርቅ ውይይት እና ውህደት መልካም ምሳሌ ሆነው መገኘታቸውን አስታውሰዋል። ፊደስ የዜና ምንጭ ዘገባ መሠረት በፓክስታን፣ ላሆሬ ከተማ በተከበረው 800ኛ የሰላምና የዕርቅ መታሰቢያ በዓል ላይ የሰላም ተስፋ ምሳሌ የሆኑት እርግቦች እንዲበሩ መደረጉን ጥቅሶ፣ ፓክስታንን ጨምሮ በሐይማኖት ተቋማት መካከል ጦርነትና አመጽ በሚካሄድባቸው፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት በሚታይባቸው አገሮች በሙሉ የሰላምና የዕርቅ መልዕክት እንዲደርሳቸው በማለት በፓክስታን የፍራንችስካዊያን ካፑቺን ታናናሽ ወንድሞች ማሕበር አለቃ የሆኑት አባ ፍራንሲስ ናዲም የተናገሩትን መዘገቡ ታውቋል። የፍራንችስካዊያን ካፑቺን ታናናሽ ወንድሞች ማሕበር አባል የሆኑት  አባ ሻዛድ በበኩላቸው ከ800 ዓመት በፊት የአሲሲው ቅዱስ ፍራንችስኮስና የግብጹ ሱልጣን ኣል ካሚል ላደርጉት የሰላም እና የእርቅ ግንኙነት ታሪካዊ ትርጉም፣ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት በነዲክቶስ 16ኛ ስለ አሲሲው ቅዱስ ፍራንችስኮስ መንፈሳዊነት፣ ስነ መለኮታዊ ትርጉምንን እና የትምህርተ ክርስቶስን አገላለጽን ተከትለው ከጻፉት መጽሐፍ ውስጥ አግኝተው ማብራሪያ መስጠታቸው ታውቋል። አባ ሻዛድ በማከልም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም በሐይማኖት ተቋማት መካከል የሚደረግ የሰላም ውይይት አስፈላጊነት በየጊዜው መናገራቸውን እና የርዕሠ ሊቃነ ጵጵስና ስማቸውም ፍራንችስኮስ ተብሎ እንዲጠራ መፈለጋቸውን አስረድተዋል።

የሰላም መልዕክተኞች ስለ መሆን፣

የፓክስታን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት እና የላሆሬ ከተማ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሰባስቲያን ሻው፣ በበዓሉ ላይ ለተገኙት በሙሉ ባስተላለፉት መልዕክታቸው ከስምንት መቶ ዓመት በፊት ስለ ሰላም ማውራት አስቸጋሪ በነበረበት ጊዜ የሰላም መልዕክተኞች ሆነው የተገኙት፣ የአሲሲውን ቅዱስ ፍራንችስኮ እና የግብጹን ሱልጣን ኣል ካሚል ፈለግ በመከተል የሰላም መልዕክተኞች መሆን እንደሚገባ ማሳሰባቸው ታውቋል። አባ ናዲም በበኩላቸው የጎርጎሮሳዊያኑ 2019 ዓ. ም. የሰላም ዓመት እንዲሆን በማለት በመላው ፓክስታን በሚገኙት ሃገረ ስብከቶች ውስጥ የሚገኙት የዘርዓ ክህነት ተማሪዎች፣ ወጣቶች፣ ሕጻናት፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ ክርስቲያኖችና ሙስሊሞች በሙሉ የሰላም መልእክተኞች በሚሆኑበት እንቅስቃሴዎች ውስጥ እንደሚሳተፉ ገልጸዋል። የሰላም መልዕክታቸው በአገራቸው የጥላቻ ስሜት ባደረባቸውና 30 ከመቶ ወደሚሆኑ የእስልምና እምነት መሪዎች ዘንድም እንደሚደርስ ያላቸውን እምነት አባ ናዲም ገልጸው፣ በፓክስታን ሰላም ይወርድ ዘንድ የተቀሩት የእስልምና እምነት ተከታዮች በሚሰጧቸው ድጋፍ በመታገዝ ስለ ሰላም በድፍረት እንደሚናገሩ ተናግረዋል።

በፓክስታን ከታወቁት የእስልምና እምነት መሪዎችና ምሁራን መካከል አንዱ የሆኑት ማውላ መሐመድ ኣሲም ማክዱም በበኩላቸው ከክርስቲያን ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ጋር በመሆን የቅዱስ ፍራንችስኮስን እና የሱልጣን ኣል ካሚል የሰላም ተልዕኮን ማሳደግ፣ በሐይማኖት ተቋማት መካከል የሚታየውን ጥላቻን ማስወገድ፣ በጎርጎሮሳዊው 2019 ዓ. ም. በአገራችን ሰላምን ማስፈን የሁላችን ተልዕኮ መሆን አለበት ብለው፣  በፓክስታን 800ኛ ዓመት የሰላም ውይይት የተደረገበትን በዓል በናከብርበት በዘንድሮ ዓመት በሐይማኖት ተቋማት መካከል ውይይት በማድረግ ሰላምን ፍቅርን በአገራቸው ማውረድ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። በመጨረሻም የሁለቱ  ሐይማኖት ተቋማት በጋራ ሆነው ባሳረጉት የሰላም ጸሎት የበዓሉ ፍጻሜ መሆኑን የቫቲካን ዜና አገልግሎት ጋዜጠኛ፣ ቸቺሊያ ሴፒያ ከስፍራው የደረሰውን ዘገባ ዋቢ በማድረግ ገልጻለች።

16 January 2019, 15:01