የታኅሳስ 07/2011 ዓ.ም 1ኛው የስብከተ ገና ሳምንት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የታኅሳስ 07/2011 ዓ.ም 1ኛው የስብከተ ገና ሳምንት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ 

የታኅሳስ 07/2011 ዓ.ም 1ኛው የስብከተ ገና ሳምንት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ኢየሱስን ለመቀበል ያስችለን ዘንድ ልባችንን መክፈት ይኖርብናል”

በኢትዮጲያ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የላቲን ስርዓተ አምልኮ የቀን አቆጣጠር ደንብ መሰረት ከታኅሳስ 07-28/2011 ዓ.ም ድረስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚወለድበትን የገና በዓል ተገቢ በሆነ መልኩ ለማክበር የምያስችለን መንፈሳዊ ዝግጅት የሚደረግበት የስብከተና ወቅት ሲሆን በእነዚህ ሳምንታት ምዕመኑ በጸሎት፣ በአስተንትኖ፣ በኖቪና እና በመሳሰሉ መንገዶች መንፈሳዊ ዝግጅቶችን በማድረግ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት ቀን ለማክበር የሚዘጋጁበት ወቅት ነው።

የመጀርያ ስብከተ ገና ሳምንት ምንባባት

1.     ት.ኤርሚያስ 33፡14-16

2.     መዝ. 24

3.     ተሰሎንቄ፡ 3፡12-4፡2

4.     ሉቃስ 21፡25-28, 34-36

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

በፀሐይና በጨረቃም በከዋክብትም ምልክት ይሆናል፤ በምድር ላይም አሕዛብ ከባሕሩና ከሞገዱም ድምፅ የተነሣ እያመነቱ ይጨነቃሉ፤  ሰዎችም ከፍርሃትና በዓለም የሚመጣበትን ከመጠበቅ የተነሣ ይደክማሉ፤ የሰማያት ኃይላት ይናወጣሉና።በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በኃይልና በብዙ ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል።ይህም ሊሆን ሲጀምር ቤዛችሁ ቀርቦአልና አሻቅባችሁ ራሳችሁን አንሡ።

ነገር ግን ልባችሁ በመጠጥ ብዛትና በስካር ስለ ትዳርም በማሰብ እንዳይከብድ፥ ያ ቀንም በድንገት ንዳይመጣባችሁ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤  በምድር ሁሉ ላይ በሚቀመጡ ሁሉ እንደ ወጥመድ ይደርስባቸዋልና።  እንግዲህ ሊመጣ ካለው ከዚህ ሁሉ ለማምለጥ፥ በሰው ልጅም ፊት ለመቆም እንድትችሉ በጸሎት ሁል ጊዜ ትጉ ሉቃስ 21፡25-28, 34-36 ።

 

የታኅሳስ 07/2011 ዓ.ም 1ኛው የስብከተ ገና ሳምንት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

“ኢየሱስን ለመቀበል ያስችለን ዘንድ ልባችንን መክፈት ይኖርብናል”

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደ ምን አረፈዳችሁ!

ዛሬ የሚጀመረው የስብከተ ገና ሳምንት ስርዓተ አምልኮ ለገና በዓል የምያዘጋጃን ወቅት ሲሆን ኢየሱስን ለመቀበል ልባችንን መክፈት እንችል ዘንድ ይጋብዘናል። በስብከተ ገና ወቅት እየተጠባበቅን የምንገኘው ጌታ የተወለደበትን ቀን ብቻ አይደለም፡ ነገር ግን በተጨማሪም ክርስቶስ ዳግመኛ በክብር የሚመጣበትን ቀን በጉጉት ነቅተን እንድንጠባበቅ ጭምር ይጋብዘናል- እርሱ በመጨረሻው የፍርድ ቀን ተመልሶ በሚመጣበት ወቅት ከእሱ ጋር ለመገናኘት ያስችለን ዘንድ የሚረዱንን ተገቢ የሆኑ ምርጫዎችን በማድረግ በብርታት በእርሱ ፊት እንቆም ዘንድ የሚረዱንን ተግባሮች በመፈጸም ተዘጋጅተን የምንጠብቅበት ወቅት ነው። የገናን በዓል ስናስታውስ፣ ክርስቶስ በክብር የሚመጣበትን ቀን በምንጠባበቅበት ወቅት፣ እኛም ከእርሱ ጋር በግለሰብ ደረጃ ለመገናኘት በመዘጋጀት፣ ክርስቶስ በሚጠራን ወቅት ለእርሱ ጥሪ ምልስ ለመስጠት የምንዘጋጅበት ወቅት ነው። በእነዚህ አራት ሳምንታት ውስጥ ከተገለለና ከተለመደ የሕይወት ጎዳና እንድንወጣ እና በአዲስ ጎዳና ላይ ተስፋ በማድረግ እንድንራመድ ጥሪ የሚያደርጉልን ሳምንታት ሲሆኑ በተጨማሪም የወደፊቱን ተስፋ በማለምለም የወደፊቱ ኑሮዋችንን በአዲስ መልክ ለመኖር የምናልምበት እና በዚህ መልክ እንድንኖር ጥሪ የሚያቀርብልን ወቅት ነው። በዚህ እለተ ሰንበት (ኅዳር 23/2011 ዓ.ም) የተነበበል ቅዱስ ወንጌል (ሉቃ 21፡25-28, 34-36) በዚህ አቅጣጫ በትክክል እንድንሄድ ጥሪ በማድረግ በራስ ወዳድ መንፈስ የመኖር አባዜን በመተው፣ የአኗኗራችንን ዘይቤ መገምገም እንደ ሚገባን ያስጠነቅቀናል። በዚህ ረገድ ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት በጣም ወሳኝ የሆኑ ቃላት ናቸው፡ እንዲህም ይላል፡ ነገር ግን ልባችሁ በመጠጥ ብዛትና በስካር፣ በመባከን እና ስለዓለማዊ ኑሮ በመጨነቅ ልባችሁ እንዳይዝል ተጠንቀቁ። ስለዚህ ከሚመጣው ክፉ ነገር ሁሉ ለማምለጥ ኃይል እንድታገኙ እና በሰው ልጅም ፊት ለመቆም እንድትችሉ ስትጸልዩ ሁል ጊዜ ትጉ” (ሉቃ. 21፡ 34,36) በማለት ያስጠነቅቀናል።

ከዛሬ ቀን ጀምሮ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበትን የገና በዓለ እስከ ምናከብርበት ቀን ድረስ ያሉትን የስብከተ ገና ሳምንታት መኖር የሚገባን ተግቶ በመጠበቅ እና በጸሎት ሊሆን የገባል። ተግቶ መጠበቅ እና መጸለይ!! ውስጣዊ የሆነ እንቅልፍ የሚከሰተው ኑሮዋችንን ራሳችንን ብቻ ባማከለ መልኩ በምንኖርበት ወቅት እና በሕይወት ውስጥ በምያጋጥሙን ችግሮች፣ ደስታዎች፣ ሕመሞች ውስጥ ራሳችንን በራሳችን ቆልፈን ስንቀምጥ ነው። እናም ይሄ ያደክመናል፣ ይህ ስልቹዎች እንድንሆን ያደርገናል፣ ይህ ተስፋ እንድንቆርጥ ያደርገናል። የዛሬ ቅዱስ ወንጌሉ የሚናገረው ይህንኑ ነው፣ ደንዝዘን እና ሰንፈን እንዳንቀመጥ ይጠይቀናል። ይህ የስብከተ ገና ወቅት ከራሳችን ውጭ በመሄድ ሌሎችን እንድንመለከት፣ እራሳችንን እና ልባችንን በማስፋት፣ ለሕዝቦች እና ለወንድሞቻችን  ፍላጎት ልባችንን በመክፈት  በአዲስ ዓለም ውስጥ ለመኖር ያላቸውን ምኞት እውን ለማድረግ እንድንሠራ ይጋብዘናል። ይህም በረሃብ፣ በፍትሕ መዛባትና በጦርነት የተሠቃዩ የብዙ ሕዝቦች ፍላጎት እና ምኞት ነው፡ የድሆች፣ የደካማዎች  እና የተተው ወይም የተረሱ ሰዎች ምኞት ነው። ይህ የስብከተ ገና ወቅት ህይወታችንን እንዴት እና ለማን መክፈት እንዳለብን በማሰብ ግልጽ ጥያቄዎችን መጠየቅ እንድንችል ልባችንን ለመክፈት እድሉን ይፈጥርልናል።

በዚህ በስብከተ ገና ወቅት ጌታን በመልካም ሁኔታ ላይ በመሆን ለመጠባበቅ ከሚያስችሉን ባሕሪያት መላከል በሁለተኛ ደረጅ የሚጠቀሰው ደግሞ ጸሎት ነው። ይህ ሁሉ መሆን በሚጀምርበት ጊዜ ደኅንነታችሁ ቀርቦአልና ቀና ብላችሁ ወደ ላይ ተመልከቱ” (ሉቃ 21፡28) በማለት የሉቃስ ወንጌል ያሳስበናል። ይህም የምያመልክተው አስተሳሰባችንን እና ልባችንን በኢየሱስ ላይ በማድረግ ነቀተን እንድንጸልይ ነው። አንድ ነገር ወይም አንድን ሰው የምንጠብቀው ተነስተን በመቆም ነው። እኛም በዚሁ መልክ ኢየሱስን በምንጠባበቅበት ወቅት በጸሎት መንፈስ በመሆን እርሱን መጠበቅ ይኖርብናል፣ ይህም ተግባር በቀጥታ ተግቶ ከመጠበቅ ጋር ይያያዛል። ኢየሱስን ለመጠበቅ፣ ራሳችንን በራሳችን ሳንዘጋ ሌሎችን ነቅተን ለመጠበቅ እንችል ዘንድ እና በትጋት ለመቆም ያስችለን ዘንድ መጸለይ ያስፈልጋል። ነገር ግን እኛ የገናን በዓለ ለማክበር እንዲሁ የፍጆታ ቁሳቁሶችን ብቻ በመግዛት የተጠመድን ከሆነ፣ ይህንን ነገር ወይም ያንን ነገር ለማድረግ፣ ይህንን ብገዛ ወይም ያንን ብገዛ እያልን ዓለማዊ የሆነ በዓል ለማክበር በምንሞክርበት ወቅት በዚህ አኳኋን እያለን ኢየሱስ በሚመጣበት ወቅት እኛን አልፎ ይሄዳል፣ እኛም እርሱን ልናገኘው አንችልም። እኛ ግን ኢየሱስን ለመጠበቅ እንፈልጋለን፣ በጸሎት መንፈስ በትዕግስት ልንጠብቀው እንፈልጋለን፣ ይህም በቀጥታ ተግቶ ከመጠበቅ ጋር የተያያዘ ነው።

ይሁን እንጂ የጸሎታችን እጣ ፈንታ ምንድነው? ይህንን ከሁሉም በላይ በመጽሐፍ ቅዱስ ወስጥ የተጠቀሱት የነቢያት ድምጾች ያሳያሉ። በዚህም ረገድ በዛሬው ጊዜ በግዞት ስለሞቱ ሰዎች እና ማንነታቸውን ለማጥፋት ለሚያስቡ ሰዎች የሚናግረው ነቢዩ ኤርምያስ ነው። እኛም ክርስቲያኖች የእግዚኣብሔር ሕዝብ አንዱ አካል በመሆናችን የተነሳ ማንነታችንን እንድናጣ ከሚያደርገን ዓለማዊ ተግባራት "የአረማዊነት" ባህሪይ በመተው የክርስትና እምነት መለያችንን በመልበስ በዚህ የኑሮ ዘይቤ መኖር ይኖርብናል። ስለዚህ በነቢዩ ኤርሚያስ በኩል የታወጀው የእግዚአብሔር ቃል ያስፈልገናል እንዲህም ይላል እነሆ የተናገርሁትን መልካም ቃል የምፈጽምበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር።  በዚያም ዘመን በዚያም ጊዜ ለዳዊት የጽድቅን ቍጥቋጥ አበቅልለታለሁ፤ እርሱም ፍርድንና ጽድቅን በምድር ያደርጋል” (ት.ኤር. 33፡14-15)። ይህ የሚበቅለው ቁጥቋጦ ኢየሱስ ራሱ ነው፣ የምንጠባበቀው እና የሚመጣው ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ነው። ወደ ኢየሱስ እንድንቀርብ የምታደርገን፣ በጸሎት እና በትዕግስት የመጠባበቅ ተምሳሌት የሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልጇ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠንን ተስፋ መጠባበቅ የምንችልበትን ኃይል እንድትሰጠን፣ በታሪክ ሂደት ውስጥ እግዚአብሔር ሁል ጊዜ ታማኝ በመሆን እና ምንም እንኳን የሰው ልጆች በስህተቶች ተሞልተው የሚኖሩ ቢሆንም ቅሉ፣ ነገር ግን የእርሱን መለኮታዊ ምሕረት በትዕግስት መጠባበቅ እንችል ዘንድ አማላጅነቷን መማጸን ያስፈልጋል።

 

ምንጭ፡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የአውሮፓዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ 1ኛው የስብከተ ገና ሳምንት ላይ ካደረጉት ስብከት የተወሰደ።

አቅራቢ፡ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

15 December 2018, 15:43