ፈልግ

ቅዱስ መስቀል መዳኛችን ቅዱስ መስቀል መዳኛችን  

የሕዳር 02/2011 ዓ.ም የዘመነ ጽጌ 6ኛው ሳምንትቃለ እግዚኣብሔር በክቡር አባ ግርማቸው ተስፋዬ

በክርሰቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም መልካም ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ ዛሬ እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዐት አቆጣጠር የዘመነ ጽጌ 6ኛ ሰንበትን እናከብራለን፡፡ በዚህም ዕለት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በተነበቡት ንባባት አማካኝነት ወደ እያንዳዳችን በመምጣት የልባችንን በር ያንኳኳል ለእያንዳንዳችን የሚሆን የሕይወት ስንቅ ይሰጠናል የሕይወት ምግብም ይመግበናል ስለዚህ ስለማያልቀው ሥጦታውና ፍቅሩ ሥሙ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የተመሰገነ ይሁን፡፡ በዛሬው በመጀመሪያ ንባብ እንደሰማነው ቅዱስ ሐዋርያውጳውሎስ በመጀመሪያ እንደ መመረጡ እንደ ሐዋርያነቱ አረማውያንን ለማገልገል ቢሆንም በአጠቃላይ ለአይሁዳውያን መዳን ያስብና ይጨነቅ በእነርሱም መዳን ደግሞ እጅግ ተስፋ ያደረግ ነበር፡፡ እግዚኣብሔር የሰውን ልጅ ለማዳን ከኃጢኣትም በስተቀር በሰው ሕይወት ለመሳተፍ ሰውን ከኣምላኩ ጋር ለማስታረቅ ወደዚህ ምድር ሲመጣ በኣይሁዳውያን በኩል ኣድርጎ ነበር ምክንያቱም እግዚኣብሔር በእነሱ በኩል ለመምጣት ወደደ በዚህም ምክንያት በመጀመሪያ ወንጌል የተሰበከው ለእነዚህ ለአይሁዳውያኑ ነው  ቢሆንም ቅሉ እነርሱ ግን ይህንን ወንጌል ባለመቀበላቸው ምክንያት ይህ ወንጌል ወደ አረማውያን ተሰራጨ አረማውያኑም ከኣይሁዳውያኑ በተሻለ መልኩ ወንጌልን ተቀበሉ በጌታችን እየሱስ ክርስቶም አምነው ተጠመቁ የእርሱንም ትዕዛዝ ለመጠበቅና ተግባራዊ ለማድረግ እንደ ቃሉም ለመመላለስ ተነሳሱ፡፡

በዚህ በመጀመሪያው ንባብ ላይ እንደተመለከትነው ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ  አይሁዳውያን አሁን ወንጌልን ባለማመናቸው የአምላክን አንድያ ልጅ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ባለመቀበላቸው ቢሳሳቱም፡ የእነርሱ የዘር ግንድ የእነርሱ ሥር መሠረት ልክ በምሳሌው እንደተገለፀው ከእግዚኣብሔር ጋር የቅርብ ትሥሥር የነበራቸው ከእግዚኣብሔር ጋር በግልጽ እስከመወያየት የደረሱ ቅዱሳኖች ነበሩ፡፡ እስራኤላውያን እንደ ባሕላቸው የመጀመሪያ የሆነውን ምርትም ይሁን እንስሳ ለእግዚብሔር መሥዋት ያቀርባሉ ይህ ወደ እግዚኣብሔር የሚቀርበውም መሥዋዕት ኣንድም የኃጢያታቸው ማስተሥረያ ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ይህ መሥዋዕት የእነርሱን ሕይወት ይቀድሳል የተቀረውን የእነርሱንም ምርትም ይሁን የበኩር ልጅ ይባርካል ስለዚህ እነዚህ ኣይሁዳውያኑ የኣብርሃም የይስሃቅና የያዕቆብ ዘሮች ናቸውና በእነርሱ ምክንያት ተባርከዋል የቀድሞ ኣባቶቻቸው ቅዱሳን ነበሩና እነርሱም የዚህ ቅድስና ተካፋዮች ሆነዋል ከእነርሱም የሚወለዱት ልጆች ይሁኑ  በምድራቸው ላይ የሚያመርቱት ምርት በእነርሱ በኩል ተባርኮላቸዋል።

ቅዱስ ሐዋርያውጳውሎስ ከአንድ የተቦከ ሊጥ ተቆንጥሮ የተጋገረ ዳቦ ለመሥዋት ወደ እግዚኣብሔር ሲቀርብ በዚህ ዳቦ ኣማካኝነት ሁሉም ሊጥ ይባረካል ከዚህም ሊጥ የተጋገረ ደቦ ሁሉ ቅዱስ ይሆናል ይላል፡፡ እንዲሁም የእነዚህ የእስራኤላውያን የቀድሞ አባቶች ቅዱሳን እንደነበሩ እንዲሁም ከእነርሱ የሚመጡ ዘሮች ሁሉ ምንም እንኳን ባለማመናቸው ቢኮነኑም መሠረታቸው ግን በቅዱሳኖቹ በኣብርሃም በይስሃቅ በያዕቆብ የዘር መሠረት ላይ የበቀለ ነውና በእነርሱ ኣማካኝነት በረከትን ኣግኝተዋል፡፡

እንግዲህ ከዚህ አነጋገር እንደምንረዳው በኣብርሃም በይስሃቅና በያዕቆብ ኣማካኝነት ኣይሁዳውያኑ እንደተባረኩ በንዲቱ ዳቦ ምክንያት ሊጡ ሁሉ እንደተባረከ  በአርአያ ሥላሴ ኣምሳል የተፈጠሩት ሁሉ ቅዱስ ከሆነው ከእግዚአብሔር የሚጋራቸው ነገር አለና ሁላችንም በአርአያ ሥላሴ የተፈጠርን ሁሉ ከዚህ ከእግዚኣብሔር ቅድስና እንጋራለንና ሁላችን ቅዱሳኖች ነን ነገር ግን ይህንን ቅድስናችንን ጠብቀን ይዘን ልንጓዝ ይገባል ይህ ደግሞ ለእኛም ይሁን ለሌሎች መቀደስ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል። በእንዲህ አኳሃን የምንጓዝ ከሆነ የእግዚአብሔር እገዛና ርህራኄ ሁልጊዜም ከእኛ ጋር ይሆናል፡፡

ይህንን ቅድሳናችንን ይዘን የማንጓዝ ከሆነ ደግሞ ምንም እንኳን የእግዚአብሔር እገዛና ርኀራኄ  ከእኛ ጋር ቢሆንም ይህ በላያችን ላይ ያለን የእግዚአብሔር እገዛም ይሁን ርኀራኄ ልንረዳው እንችልም፡፡ ማንኛውም ሰው ራሱን ሙሉ በሙሉ ለኣምላኩ ካልሰጠ ኣምላኩንም በፍጹም ልቡ  በፍጹም ነፍሱ በፍጹም ሓሳቡ እንዲሁም  በፍጹም ኃይሉ ኣምላኩን ከልወደደ እግዚኣብሔር በእርሱ ላይ ያለዉን ዕቅድ በፍጹም ሊረዳው ኣይችልም። ኣብዛኛውን ጊዜ ሰይጣን እግዚኣብሔር በእኛ ላይ ያለዉን መልካም ዕቅድ እንዳንረዳ ልባችንን በመስረቅ ሓሳባችንን በመክፈል ከእግዚኣብሔር መንገድ ሊያርቀን ሁሌም ይጥራል የሚቻለውን ሁሉ ያደርጋል እኛም ኣስቀድመን ይህንን ነገር ልንረዳው ይገባናል።

ሰው ቅድስናውን ይዞ እንዳይጓዝ ሰይጣን ሌት ተቀን እንደሚሰራ መዘንጋት የለብንም በዬሐንስ ራዕይ 12፡13-18 እንደተጠቀሰው ሰይጣን ሴቲቱን ለመጉዳት ባለመቻሉ ከልጆቹ ጋር ጦርነት ለማድረግ ሄደ ይላል፡፡

እንግዲህ የሴቲቱ ልጆች ተብሎ የተጠቀሱት እኛ በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ አምነን የተጠመቅን ሁላችን ነን በመሆኑም ሰይጣን ሁልጊዜ በዙሪያችን በመሽከርከር ይህን ከእግዚአብሔር የወረስነውን ቅድስና ለማደፍረስ ከእግዚአብሔር ያለንን ግንኙነት ለመደምሰስ ይጥራል ነገር ግን እኛ በሮሜ 8፡31 ላይ እንደተጠቀሰው ከእግዚአብሔር ጋር ከሆንን ማን ሊቃወመን ይችላል? በሚለው ቃል መሠረት ማንኛውንም ዓይነት የሰይጣን ፈተናና ትንኮሳ ሊያሸንፈን እንዲሁም ከእግዚአብሔር እቅፍ ውስጥ ሊያወጣን አይችልም፡፡

በሐዋርያት ሥራ 11፡1-11 ላይ እንደምንረዳው ደግሞ እንዳንድ ጊዜ ሰዎች ከፍቅር ይልቅ ለሕግ ቅድሚያና ቦታ ሲሰጡ ይታያል፡፡ በተለይ የኣይሁዳውያንን ሕግ ስንመለከት ትልቅ ትኩረት ሰጥተው የሚያዩት ጉዳይ የሕግን ነገር ብቻ ነው። ለዚህም ነው አይሁዳውያን ከአረማውያን ጋር አይብሉ የሚለውን የአይሁድ ሕግ ቅዱስ ጴጥሮስ ከአረማውያን ጋር በልቷል በማለት አይሁዳውያን የሚከሱት፡፡

ይህ አካሄድ በተለያየ መልኩ በቤተክርስቲያንም ውስጥ ጭምር ይከሰታል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ እግዚአብሔር በቤተክርስቲያን ውስጥ ብዙ ድንቅ ነገሮችን በተለያዩ ሰዎች ኣማካኝነት ሲያደርግ የማይደሰቱ ሰዎች ይኖራሉ፡፡ ምክንያቱም ቅድም እንደጠቀስነው ሰይጣን በተለያየ መልኩ የእግዚአብሔር መልካም ሥራ የሚቋረጥበትንና የሚጠፋበትን መንገድ ያመቻቻል አንዳንድ ጊዜም በእምነታቸው ያልጠነከሩትን ሰዎች ልብ በመስለብ በእነርሱ አማካኝነት የእግዚአብሔርን መልካም ሥራ ለማዳናቀፍ ይጥራል የመለያየትና ከእግዚአብሔር መንገድ የሚያርቀንን ኣቅጣጫ እንድንከተል ይጎተጉተናል፡፡

ማንኛውም ሰው መልካም ሥራ በመሠራቱ የመልካም ሥራ ተካፋይ በመሆኑ ቅር የሚሰኝ ወይንም የሚከፋ ሰው በተዘዋዋሪ መልኩ በእግዚብሔር ላይ ማመፁንና ማጉረምረሙን መርሳት የለበትም ምክንያቱመ የመልካም ሥራ ባለቤትና አነሳሹ ሁልጊዜም ቢሆን እግዚአብሔር ራሱ ነውና ነው፡፡ በእግዚኣብሔር ላይ ማጉረምረም ከእርሱ የሚመጣውን በረከት እንዳናገኝና በተለይም ደግሞ ሰይጣን በልባችን የሚልከው በእግዚኣብሔር ላይ በጠላትነት እንድንነሳ የሚያደርግበት ዓይነተኛ መሣሪያው ነው። በእግዚኣብሔር ላይ የሚያምጽ ሰው ሰለሰራው ክፉ ሥራ የክፉ ሥራን ውጤት ያጭዳል።  እስራኤላውየን የተደረገላቸውን መልካም ሥራ ሁሉ እረስተው በእግዚአብሔር ላይ ማጉረምረማቸውን ተከትሎ እግዚአብሔር ወደ ተሰፋይቱ ምድር እንዳይገቡ እድርጐአቸዋል ኦሪት ዘኁልቅ 14፡26-30 እንዲሁ ደግሞ እግዚአብሔር በተለያዩ ሰዎች በኩል አድርጐ ለሚያከናውናቸው መልካም ሥራዎች እንቅፋት የሚሆኑት ሁሉ ከዚህ ከተሳሳተ አካሄደቸው ካልተቆጠቡ ተመሳሳይ ነገር ሊገጥማቸው ይችላል፡፡

ማንም ሰው መልካም ሥራን ለመሥራት በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት ሲነሳሳ የሥራው ባለቤት ራሱ እግዚአብሔር ነው ስለዚህ በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት የተጀመረን ሥራ ማንኛውም ዓይነት ምድራዊም ይሁን ሰማያዊ ኃይል ወይንም ጉልበት ሊቋቋመው አይችልም። በዚህ ሠሰረት ቅዱስ ሐዋርያው ጴጥሮስ ምንም እንኳን ክርስቲያን በሆኑ አይሁዶችና ክርስቲያን ባልሆኑ አይሁዶች ቢከሰስም በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ሁሉንም እውነታ አስረዳቸው በመንፈስ ቅዱስ እገዛ ልባቸውን ከፈተላቸው አብዛኞቹም አምነው ተጠመቁ እግዚአብሔር ንጹሕ ያደረገውን አንተ ርኩስ ነው ማለት አትችልም በሚለው ቃል ተማምነውና ተስማምተው በኣንድነት እግዚብሔርን አመሰገኑ፡፡

ይህ የዛሬው የማቴወስ ወንጌል ምዕራፍ  21፡33-46 ያለው ቃል በትንቢተ ኢሳያስ 5፡1-7 ካለው ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡ ይህ ታሪክ የእስራኤልን ሕዝብ ታሪክ ይወክላል፡፡ የንስሃንና የጽድቅን ፍሬ ያገኝባቸው ዘንድ እግዚአብሔር ተራ በተራ የቡልይ ኪዳንን ዓበይትና ንዑሳን ነቢያት ወደ እስራኤላውያን ልኳል እስራኤላውያኑ ግን እግዚኣብሔር በነቢያት ኣማካኝነት የሚነግራቸውን ቃል መስማት ትተው እያንዳንዱን ነቢይ በማሰቃየትና በመግደል እግዚአብሔር አስቀየሙ፡፡ በስተመጨረሻም እግዚአብሔ አንድያ ልጁን ወደ እነዚህ ሕዝቦች ላከ እነርሱም ይህማ ወራሹ ነው ብለው እርሱንም ገደሉት፡፡

እንግዲህ የወይኑ እርሻ ባለቤት ሲመጣ እነዚያን ገዳዮች በሙሉ ያስወግድና የወይኑን እርሻ ለሌሎች ገበሬዎች ያከራያል፡፡ ይህ ምሳሌ በ70 ዓ.ም. ሮማውያን እየሩሳሌምን በደመሰሉ ጉዜ የተፈፀመ ትንቢት ነው፡፡ ይህም ማለት የእግዚአብሐር ቃል የእግዚአብሔር የማዳን ታሪክ ለእስራኤለውያን ቢሰጥም እነርሱ ግን ይህንን ጸጋ ለመቀበል የተገቡ አልነበሩምና ይህ ጸጋ ከእነርሱ ተወስዶ ለሌሎች አሕዛብ እንደሚሰጥ ያስረዳናል፡፡ ዛሬም ቢሆን ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ለሁላችን ይህን ጸጋና በረከት ሰጥቶናል ነገር ግን እኛም የዚህ ጸጋና በረከት ተጠቃሚዎች ካልሆንን ይህ ጸጋ ከእኛ ተወስዶ ለሌሎች እንደሚሰጥ መረዳት መቻል አለብን፡፡ ዛሬ እኛ እያንዳንዳችን ሌሎች ገበሬዎች የተባሉትን የወንጌሉን ገጸ ባህሪ እንወክላለን፡፡ ስለዚህ በዚህ በወይን እርሻ ውስጥ በሚገባ እንድንሠራ ብሎም መልካም ፍሬ እንድናፈራ ተጋብዘናል፡፡ ይህ የወይን እርሻ የእያንዳዳችን ሕይወት ነው ስለዚህ በገባንበትና በምንመራው ሕይወት ውስጥ እግዚአብሔርና ሰውን ሁሉ የሚያስደስት ሥራ እንድንሰራ ዘወትር እግዚአብሔር በልጁ አማካኝነት በሰጠን ጸጋና ባስተማረን ትምሕርት መሠረት እንድንመላለስ ያስፈልጋል ይህ ካልሆነ አሁንም ይህ ጸጋ ከእኛ ይነጠቃል ለሌሎችም ይሰጣል፡፡

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
10 November 2018, 16:37