ፈልግ

Torre Hassan, Rabat - Marocco Torre Hassan, Rabat - Marocco 

የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የሞሮኮ ጉብኝት በሐይማኖቶች መካከል ግንኙነትን እንደሚያጠናክር ተገለጸ።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቀዳሚ ተልዕኮ፣ ሊቀ ጳጳሳት ክርስቶባር ሎፔዝ እንደገለጹት፣ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቀዳሚ ተልዕኮ፣ በእምነታችን ሊያበረታቱን ነው ብለው፣ ከዚህም በተጨማሪ ቅዱስነታቸው በሞሮኮ የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንን ለማወቅ፣ ሕይወቷንም ለመጋራት፣ ሊያበረታቷት፣ ከምዕመናኑ ጋር አብረው ለመጸለይና ሊባርኩን ነው ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የሞሮኮ ዋና ከተማ የሆነችው የራባት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ክርስቶባል ሎፔዝ ማክሰኞ ህዳር 4 ቀን 2011 ዓ. ም. ይፋ ባደረጉት መልዕክታቸው፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ሞሮኮ ሐዋርያዊ ጉብኝት እንደሚያደርጉ አስታውቀው፣ ጉብኝታቸውም በእስልምናና በክርስትና እምነቶች መካከል የሚደረገውን ውይይት እንደሚያጎለብተውና እንደሚያጠናክረው ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። 

የራባት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ክርስቶባል ሎፔዝ “ውድ ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች” በማለት ባስተላለፉት መልዕክታቸው፣ መጋቢት 21 እና 22፣ 2011 ዓ. ም. ቅዱስነታቸው ወደ ሞሮኮ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት መረጋገጡን የቅድስት መንበር የዜና ክፍል ዋና ተጠሪ የሆኑት አቶ ግረግ ቡርኬ ማሳወቃቸውን አስታውሰው በሞሮኮ ውስጥ በስደት ላይ ያሉ፣ ወደ አውሮጳ ለመድረስ በጉዞ ላይ የሚገኙ በርካታ ክርስቲያኖች መኖራቸውን አስታውሰዋል።

የፍቅርና የተስፋ ማስታወሻዎች፣

የራባት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ክርስቶባር ሎፔዝ ንግግራቸውን በመቀጠል ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ፣ በንጉሥ ሐሰን 2ኛ ዘመን ማለትም በ1977 ዓ. ም. ወደ ሞሮኮ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት አስታውሰው፣ ይህ ጉብኝታቸው ለመላው የሞሮኮ ሕዝብና ለካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ትልቅ ተስፋን፣ ፍቅርንና በረከትን እንዳስገኘ አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ሞሮኮ ሐዋርያዊ ጉብኝት እንደሚያደርጉ የቅድስት መንበር የዜና ክፍል ዋና ተጠሪ የሆኑት አቶ ግረግ ቡርኬ ማክሰኞ ህዳር 4 ቀን 20011 ዓ. ም. መግለጻቸው ይታወሳል። የቅድስት መንበር የዜና ክፍል ዋና ተጠሪው ለጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስረዱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከሞሮኮ ንጉሥ መሐመድ 6ኛ እና ከሞሮኮ ብጹዓን ጳጳሳት የቀረበላቸውን ግብዣ በደስታ መቀበላቸውን ገልጸዋል። በዚህም መሠረት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ሞሮኮ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት መጋቢት 21 እና 22፣ 2011 ዓ. ም. እንደሚሆንና ይህም ቅዱስነታቸው ወደ ዓለም ዙሪያ ለሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት 26ኛው እንደሚሆን ታውቋል።

ከዚህ በፊት ነሐሴ 13 ቀን 1977 ዓ. ም. በንጉሥ ሐሰን 2ኛ ዘመን፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ ወደ ሞሮኮ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት አል አዳት ማግሪቢያ የተባለ የሃገሪቱ ጋዜጣ ታሪካዊ ነበር በማለት አስታውሶታል። ጋዜጣው በማከልም የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ጉብኝት በክርስትናና በእስልምና እምነቶች መካከል ዘላቂ ውይይቶችን ለመጀመር በር ከፋች ነበር ብሎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ በወቅቱ በካዛ ብላንካ ስታዲዮም ባሰሙት ንግግራቸው ክርስቲያኖችና ሙስሊሞች በተሳሳተ መንገድ በመጓዝ ባለፉት ጊዜያት እስከ ቶርነት ደርሰናል። እንደ አማኞችና ሰው እንደመሆናችንም ብዙ የጋራ እሴቶች አሉን፣ የምንኖርበት ዓለም በብዙ ተስፋ ሰጭ እና በስቃይም ምልክቶች የተሞላ ነው፣ አብርሐም ለእኛ የእምነት ምሳሌ ነው፣ ለእግዚ አብሔር ፈቃድ መገዛት፣ በእርሱ መልካምነት መታመን፣ ዓለምን የፈጠረና ፍጥረታቱንም ወደ ፍጽምናቸው የሚያመጣ አንድ አምላክ አለ ያሉትንም ጋዜጣው አስታውሷል።      

የአንድነትና የውይይት መንፈስን ማሳደግ፣

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቀዳሚ ተልዕኮ፣ ሊቀ ጳጳሳት ክርስቶባር ሎፔዝ እንደገለጹት፣ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቀዳሚ ተልዕኮ፣ በእምነታችን ሊያበረታቱን ነው ብለው፣ ከዚህም በተጨማሪ ቅዱስነታቸው በሞሮኮ የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንን ለማወቅ፣ ሕይወቷንም ለመጋራት፣ ሊያበረታቷት፣ ከምዕመናኑ ጋር አብረው ለመጸለይና ሊባርኩን ነው ብለዋል። ሊቀ ጳጳስ ክርስቶባር በማከልም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከሞሮኮ ሕዝብና ከአገሪቱ ባለስልጣናት ጋር ለመገናኘት ምኞት እንዳላቸው ገልጸው በተለይም ከሞሮኮ ንጉሥ፣ ግርማዊነታቸው መሐመድ 6ኛ ጋር በመገናኘት በሁለቱ እምነቶች መካከል የሚታየውን የውይይት ፍላጎት ለማሳደግ ነው ብለዋል።

የራባት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ክርስቶባር ሎፔዝ፣ በሞሮኮ ክርስቲያኖች መካከል ያለው ሕብረት እንዲያድግ ትልቅ ፍላጎት መኖሩን ገልጸው እንደዚሁም ከሌሎች እምነቶችም ጋር ያለው ግንኙነት እንዲጠናከር፣ ከሮማው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር የጠበቀ ግንኙነትን በመፍጠር ይህም ወደ መላዋ ቤተክርስቲያን አንድነት ስለሚያደርስ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ሞሮኮ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ግንኙነት መልካም አጋጣሚ እንደሚሆን አስረድተዋል።

ለውጤታማ ሐዋርያዊ ጉዞ እንጸልይ፣

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ክርስቶባር ሎፔዝ በመጨረሻም በሞሮኮ ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ የሚመጡትን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን በደስታ ለመቀበል ዝግጅት እንዲያደርጉ ክርስቲያኖችን በሙሉ አደራ ብለዋል። የጉብኝታቸው መርሃ ግብር ይፋ እስከሚሆን፣ ለቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት ፍሬያማነት ዘወትር በጸሎት መበርታት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።           

15 November 2018, 16:30