አባ ፔድሮ ኦፔካ አባ ፔድሮ ኦፔካ  

አባ ፔድሮ ኦፔካ ድህነትን ወደ ተስፋ የቀየሩ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ካህን ናቸው

ድህነትን ወደ ተስፋ የቀየሩ አንድ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ካህን ተግባር የሚያመለክት ዘጋቢ ፊልም በቅርቡ በቫቲካን ይፋ መደረጉ ይታወሳል። እኛህ ካህን በትውልድ አርጄንቲናዊ የሆኑ በአሁኑ ወቅት በማዳጋስካር ሚስዮናዊ በመሆን በማገልገል ላይ የሚገኙ የቅዱስ ቪንሰንት ማኅበር ወይም የላዛሪስት ማኅበር አባል የሆኑ አባ ፔድሮ ኦፔካ በመባል ይታወቃሉ።

የዚህ ዜና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

የአባ ፔድሮ ኦፔካን መልካም ሥራ የተመለከቱ አንዳንድ ሰዎች “ቅዱሱ ተዋጊ" ወይም "ተዓምር ሰሪ” በማለት ያወድሱዋቸዋል። በስቃይ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ፍቅር እርሳቸው ውቅያኖሶችን እና ተራሮችን አቋርጠው የራሳቸውን የግል ፍላጎት ሳይሆን ነገር ግን ጠንካራ እና አስደናቂ በሆኑ ተግባሮቻቸው ውስጥ ለክርስቶስ ያላቸው እምነት እና በመልካም ሥራዎቻቸው ውስጥ የክርስቶስ ፊት እንዲታይ በማሰብ የገዛ ሀገራቸውን ጥለው ወደ አፍርቃ አህጉር በመሄድ መልካም ሥራቸውን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ለማዳጋስካር ሕዝብ በማበርከት ላይ የገኛሉ።

አባ ፔድሮ ኦፔካ እንደ አውሮፓዊያኑ የቀን አቆጣጠር በ1975 ዓ.ም (የዛሬ 43 ዓመት ገደማ ማለት ነው) የትውልድ ሀገራቸው የሆነችውን አርጄንቲና ጥለው በድህነት የተጎሳቆለችሁን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በድህነት ወደ ሚሰቃዩባት ማዳጋስካር ያቀናሉ። ማዳጋስካር በደረሱ ወቅት በወቅቱ በእዚያ የነበረው የድህነት ሁኔታ አስከፊ መሆኑን ከተገነዘቡ በኃላ ይህንን ሁኔታ ለመቀየር እና የሰው ልጆች ተገቢ የሆነ ሕይወት እንዲኖራቸው በማሰብ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ለመቅረጽ ያስባሉ፣ በተለይም በማኅበረሰቡ ውስጥ አቅመ ደካማ የተባሉ ሰዎችን ለማብቃት ከፍተኛ የሆነ ጥረት ማደርግ ይጀምራሉ።

በመሆኑም በተለየ ሁኔታ የአባ ፐድሮ ኦፔካን ቀልብ የሳበው ሥፍራ ለዘመናት ያህል የቆሻሻ መጣያ ሆኖ የከረመው እና ብዙ ድሆች ከቆሻሻ ጋር ተቀላቅለው የሚጣሉ ቁሳቁሶችን በመሰብሰብ እለታዊ የሆነ ኑሮዋቸውን ለማሸነፍ ይረዳቸው ዘንድ በዚህ በቆሻሻ መጣያ ስፍራ በመገኘት በተቻላቸው መጠን ከቆሻሻ ጋር ተቀላቅለው የተጣሉ ቁሳቁሶችን በመፈለግ ሥራ ላይ ተሰማርተው ማየታቸው እርሳቸው ልባቸው እንዲነካ ካደርጉ ነገሮች መካከል አንዱ ሲሆን በተለይም ደግሞ በዚህ አስከፊ በሆነው ሥራ ላይ አቅመ ደካማ የሆኑ አዛውንቶች እና ሕጻናት ተሰማርተው ማየታቸው ልባቸው በከፍተኛ ሁኔታ እንዲነካ ያደርጉ አጋጣሚዎች እንደ ሆኑ በተለያዩ ጊዜያት ከሰጡት መግለጫ ለመረዳት ተችሉዋል።

በማዳጋስካር ዋና ከተማ በአንታናናሪቮ በሚገኝ አንድ የቆሻሻ መጣያ ስፍራ አጠገብ በጣም የተጎሳቆለ በማላጋሽ ቋንቋ “አካማዞዋ” በአማሪኛው በግርድፉ ሲተረጎም “መልካም ጓደኛ” በሚል መጠሪያ የሚታወቅ አንድ የተጎሳቆለ መንደር ይገኛል። በዚህች መንደር ውስጥ በጣም በርካታ የሆኑ በቆሻሻ መልቀም ሥራ ላይ የተሰማሩ የተጎሳቆሉ ድሆች ይኖራሉ። አባ ፔትሮ ኦፔካ ይህንን ሁኔታ በመቀየር እነዚህ በርካታ የተጎሳቆሉ ሰዎች ሰብዓዊ ክብራቸው ተጠብቆ እንደ አንድ ሰው ተቆጥረው በተገቢው መንገድ መኖር ይችሉ ዘንድ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ከበርካታ ጥረቶች እና ከከፍተኛ ድካም በኋላ ያ የቆሻሻ መጣያ ስፍራ የነበረውን መንደር አስደናቂ በሆነ ሁኔታ በመቀየር ከ23ሺ በላይ ለሆኑ ድሆች በቂ የሆነ የመኖርያ ቤት በማዘጋጀት የጤና ክብካቤ መስጫ ተቋማት፣ መዋለ ሕጻናት፣ ትምህርት ቤቶችን እና ለመዝናኛነት የሚያገለግሉ ፓርኮችን ያካተተ መንደር እንዲመሰረት አድርገዋል።

ይህንን የአባ ፔትሮ ኦፔካ ታሪክ እና ስኬት በተመለከተ “ፔድሮ ኦፔካ- ቦን አሚኮ” (አባ ፔድሮ ኦፔካ መልካም ጉደኛ) በሚል አርእስት የተሰራ አንድ ዘጋቢ ፊልም በቅርቡ በቫቲካን ለእይታ መቅረቡ የታወቀ ሲሆን  በዚህ ዘጋቢ ፊልም ውስጥ በማዳጋስካር የሚታየውን አስከፊ ድህነት፣ አባ ፔድሮ ኦፔካ ይህንን አሰቃቂ ድህነት ወደ ተስፋ መቀየራቸውን፣ ከፍተኛ ጥረት ከተደረገ ድህነት የማይሸንፍበት ምክንያት እንደ ሌለ፣ ድህነትን ለማስወገድ በተከታታይ ድሃውን ሕዝብ ባሳተፈ መልኩ ተከታታይ ተግባሮችን ማከናወን እንደ ሚጠይቅ፣ በጽናት ከተሠራ የሰው ልጆችን ሕልውና በማስጠበቅ ተስፋቸውን ዳግም ማለምለም እንደ ሚችላ በሰፊው የሚያትት ዘጋቢ ፊልም እንደ ሆነ ለመረዳት ተችሉዋል።

22 November 2018, 14:18