Camerun manifestazioni a Bamenda Camerun manifestazioni a Bamenda 

በካሜሩን የታገቱትን ሚሲዮናዊያን ለማስለቀቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑ ታወቀ።

የምዕራብ አፍሪቃ አገር የሆነችው ካሜሩን፣ ከረጅም ዓመታት ወዲህ የእንግሊዘኛ ቋንቋ ተናጋሪ ክፍለ ሃገርና የፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ ክፍለሃገር በመባል ለሁለት የተከፈለች መሆኗ ይታወቃል። በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት የኖረው ክፍለ ሀገር ከጠቅላላው የሀገሪቱ ክፍል 20 ከመቶ የያዘ ሲሆን በመንግሥት አስተዳደርና በሃብት ክፍፍል ፍትሃዊነት ይጎላል በማለት ብሶት ሲያሰማ እንደቆየ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በካሜሩን በምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን፣ የክላሬቲያን ገዳም ሚሲዮናዊያን ማሕበር ጠቅላይ ጸሐፊ የሆኑት ክቡር አባ ዮሴባ ካሚሯጋ በመሣሪያ ታጣቂዎች የታገቱት የማሕበራቸው አባላት እንዲለቀቁ በማለት ጥሪ ማቅረባቸው ተነግሯል። በካሜሩን ከደቡብ ምእራብ ከፍለ ሀገር በመሣሪያ ታጣቂዎች ተይዘው የተወሰዱት ሚሲዮናዊያን ሦስት እንደሆኑና ከእነርሱም ጋር አንድ ምዕመን እንዳለበት ለማወቅ ተችሏል። ሚሲዮናዊያንን አገተው የወሰዱት መሣሪያ ታጣቂዎች የደቡብ ምእራብ ክፍለ ሀገርን ነጻ ለማውጣት የሚታገል ቡድን አባላት መሆናቸው ታውቋል።

ሕዳር 15 ቀን 2011 ዓ. ም. በመሣሪያ ታጣቂዎች ተይዘው የተወሰዱት ሚሲዮናዊያን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ንጹሕ ልብ ማሕበር አባላት መሆናቸው ሲታወቅ፣ ሚሲዮናዊያኑ በካሜሩን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪ በሆነው የደቡብ ምእራብ ክፍለ ሀገር ነዋሪዎች እንደሆኑ የቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋዜጠኛ አቶ አመደዎ ሎሞናኮ የላከልን ዜና ያስረዳል። ሚሲዮናዊያን በመሣሪያ ታጣቂዎች ተይዘው የተወሰዱት ሙየንጄ በተባለ አካባቢ ለሚኖሩት የቁምስና ምእመናን ሐዋሪያዊ አገልግሎታቸውን ለማበርከት፣ እንዲሁም ለአካባቢው ነዋሪዎች የሚያቀርቡትን ማሕበራዊ አገልግሎት ለመከታተል ብለው በመጓዝ ላይ እንዳሉ መሆኑ ታውቋል። በዚሁ አካባቢ ከዚህ በፊት ማለትም ህዳር 12 ቀን 2011 ዓ. ም. ኬንያዊ ዘግነት ያላቸው ካቶሊካዊ ካህን በመሣሪያ ታጣቂዎች መገደላቸው ይታወሳል።

ኢሰብዓዊ አመጽ፣

በካሜሩን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች የሚኖሩባት የደቡብ ምእራብ ክፍለ ሀገር፣ የክፍለ ሀገሩን ነጻነት ለማወጅ በሚንቀሳቀሱ አማጽያን ቡድኖችና በመንግሥት ወታደሮች መካከል ጦርነት የሚካሄድባት ክፍለሀገር እንደሆነች ይታወቃል። በዚህች ክፍለ ሀገር ካለፉት ጥቂት ቀናት በፊት በመንግሥት ወታደሮችና በአማጺ ቡድን መካከል በተካሄደው ጦርነት፣ 60 ሰዎች መሞታቸው ሲነገር 450 ሺህ ሰዎችም ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸው ተነግሯል። የካሜሩን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በቅርቡ ባወጣው መግለጫ ጦርነቱን በጽኑ አውግዞ፣ በዚያች አገር እየተካሄደ ያለው ጦርነት ፈጽሞ ትርጉም የሌለውና ኢሰብዓዊም ነው ብሏል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በእንግሊዝኛ ተናጋሪ የካሜሩን ደቡብ ምእራብ ክፍለ ሀገር እየተካሄደ ያለው ጦርነት እጅግ እንዳሳሰበው ገልጾ፣ በአካባቢው ሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ የሚደርስ የሞትና የምቁሰል አደጋዎች እንዲሁም የንብረት መውደም ከመንግሥት ወታደሮችና ከነጻ አውጪ አማጺያን ቡድኖች በኩል እንደሆነ ገልጿል።

ታጋቾቹ በደህና ሁኔታ ላይ ናቸው፣

ክቡር አባ ዮሴባ፣ በነጻ አውጪ ታጣቂዎች ታግተው የተወሰዱት ሚሲዮናዊያን ሁኔታ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት እንደገለጹት፣ ሚሲዮናዊያኑ በደህና ሁኔታ ላይ መኖራቸውን ገልጸው፣ በነጻ ለማስለቀቅ የሚደረግ ጥረትና ድርድር በሂደት ላይ እንዳለ አስረድተዋል። በእነዚህ ቀናት ውስጥ የሚደርሷቸው መረጃዎች አወዛጋቢ እንደሆኑ የገለጹት የክላሬቲያን ሚሲዮናዊ ማሕበር ጠቅላይ ጸሐፊ የሆኑት ክቡር አባ ዮሴባ ካሚሯጋ፣ ከማሕበሩ ጠቅላይ አላቃ ጋር ሳያቁርጡ መልዕክቶችን እንደሚለዋወጡ ገልጸዋል። በታጣቂዎች ታግተው የተወሰዱት በቁጥር አራት እንደሆኑ፣ ከእነርሱም መካከል አንድ ሚሲዮናዊ ካህን፣ ሁለቱ የማሕበሩ ዲያቆናትና አንድ ሾፌር እንደሆኑ ገልጸው በመልካም የጤና ሁኔታ ላይ እንደሚገኙና በሕይወት በሕይወት እንዳሉ ማረጋገጣቸውን አስረድተዋል።

በሐዋርያዊ አገልግሎት ላይ የሚገኙትን የማሕበራቸው አባላት ያገተው ቡድን በካሜሩን ደቡባዊ ምእራብ ክፍለ ሀገር ውስጥ ለነጻነት   የሚፋለም ጠንካራና እውቅና ያለው አማጺ ቡድን እንደሆነ የገለጹት አባ ዮሴባ፣ አጋቾችን በስም ለመግለጽ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ገልጸው ከአጋቾች በኩል እስካሁን ምንም ዓይነት የገንዘብ ክፍያ ጥያቄ እንዳልደረሳቸው ገልጸዋል። አባ ዮሴባ በማከልም የአጋቾቹ ጥያቄ የገንዘብ ሳይሆን ለአካባቢው ነጻነት ያቀውረቡት ጥያቄ ፖለቲካዊ ምላሽ እንዲያገኝ የሚል እንደሆነ ተናግረዋል።

የምዕራብ አፍሪቃ አገር የሆነችው ካሜሩን፣ ከረጅም ዓመታት ወዲህ የእንግሊዘኛ ቋንቋ ተናጋሪ ክፍለ ሃገርና  የፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ ክፍለሃገር በመባል ለሁለት የተከፈለች መሆኗ ይታወቃል።  በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት የኖረው ክፍለ ሀገር ከጠቅላላው የሀገሪቱ ክፍል 20 ከመቶ የያዘ ሲሆን በመንግሥት አስተዳደርና በሃብት ክፍፍል ፍትሃዊነት ይጎላል በማለት ብሶት ሲያሰማ እንደቆየ ታውቋል። በዚህም ምክንያት በ2008 ዓ. ም. የተቀሰቀሰው የመጀመሪያው አመጽ በብዙ ቁጥር ለሚገመቱ ሰላማዊ ዜጎች ሞትና ለሌሎች በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች መታሰር ምክንያት ሆኗል ተብሏል።

ክቡር አባ ዮሴባ ከቫቲካ የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፣ ማሕበራቸው በካሜሩን ደቡባዊ ምራብ ክፍለ ሀገር ነዋሪዎች የሚያቀርበውን ሐዋርያዊና ማሕበራዊ አግልግሎት እንደሚቀጥልበት ገልጸው የባሕበራቸው ሚሲዮናዊያን ከሚሰቃይ ሕዝብ ጋር በመሆን፣ ስቃያቸውን እየተጋሩ እስከ መጨረሻዋ ሰዓት ድረስ በስፍራው እንደሚቆይ ገልጸዋል። አስቀድሞም ቢሆን ማሕበራቸው ወደዚህ ስፍራ ሄደው ሐዋርያዊ አገልግሎት ለማበርከት የፈለጉትም የሕዝቡን ስቃይ እየተጋሩ የተቻላቸውን ድጋፍና እርዳታ ለማድረግ እንደሆነ አስረድተዋል።

 

              

28 November 2018, 15:12