2018.10.19 sinodo giovani 2018: monsignor Naffah Liban 2018.10.19 sinodo giovani 2018: monsignor Naffah Liban 

የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ለዓለም መንግሥታት መሪዎች ድምጹን እንዲያሰማ ወጣቶች ጠየቁ።

ወጣቶች ሰፊ ውይይት እንዲያደርጉባቸው የሚፈልጓቸውት ርዕሶች፣ ጦርነት፣ ድህነት፣ ሥራ አጥነት፣ ስደትና የሕገ ወጥ መሣሪያ ዝውውር ናቸው።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ወጣቶች፣ እምነትና ጥሪያቸውን ጥበብ በተሞላበት ሁኔታ እንዲያውቁት ለማድረግ በሚል ርዕስ በቫቲካን ከተማ 15ኛ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤ እየተካሄደ መሆኑ ይታወቃል።

የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ያለፈው ቅዳሜ ባካሄደው ጉባኤ፣ ብጹዓን ጳጳሳት ወጣቶችን በሚመለከቱ ጉዳዮች ድምጻቸውን እንዲያሰሙ፣ ወጣቶች ለስደት ሳይዳረጉ፣ በተወለዱበት አገር ሆነው በቂ የእድገት እድሎችን የማግኘት መብታቸው እንዲረጋገጥ ማድረግ፣ ለወጣቶች ቅዱሳት መጽሕፍትን ለማዳረስ የሚቻልበት መድረኮች ማመቻቸትን በሚመለከት መወያየታቸው ታውቋል።

በቫቲካን የመገናኛ ጽሕፈት ቤት ዋና ተጠሪ የሆኑት ክቡር አቶ ፓውሎ ሩፊኒ፣ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ፣ በወጣቶች ሐዋርያዊ አገልግሎት ዙሪያ የቀረበውን ሦስተኛ ሰነድ መመልከቱን ገልጸው በዚህ ሰነድ ላይ የቀረቡት ሃሳቦች ተሰባስበው ወደ ብጹዓን ጳጳሳት ቅርቦ የመጨረሻ ውይይት እንደሚደረግባቸ ገልጸዋል።

የሰሜን አሜርካዉ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ብሌዝ ኩፒች እንዳስረዱት፣ የወጣቶችን ሐዋርያዊ አገልግሎት በሚመለከት ሰነድ ላይ በቀረቡት ጉዳዮች ድምጻቸውን እንደሚያሰሙና፣ ይህ የመወያያ ሰነድ የሲኖዶሱ ብጹዓን ጳጳሳት በስፋት እንዲወያዩበት በማለት ጥያቄን የሚያቀርቡበት እንደሆነ አስረድተዋል። ብጹዕ ካርዲና ብሌዝ በማከልም ብጹዓን ጳጳሳት ሰፊ ውይይት እንዲያደርጉባቸው ወጣቶች የሚፈልጉት ርዕሶች፣ ጦርነት፣ ድህነት፣ ሥራ አጥነት፣ ስደት፣ የሕገ ወጥ መሳሪያ ዝውውር እንደሆኑ ገልጸዋል። በእነዚህ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ ብጹዓን ጳጳሳት ውይይት አድረገው ለዓለም መንግሥታት መሪዎች ድምጻቸውን እንዲያሰሙ ወጣቶች ማሳሰባቸውን ገልጸው ይህም የዓለም መንግሥታት ዛሬ የሚወስዱት ውሳኔ የመጭውን ትውልድ የወደፊት ዕጣ ፈንታን ስለሚወስን ነው ብለዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ኩፒችና የፓፗ ኒው ጊኒ ተወካይ ጆን ሪባት እንደተናገሩት በርካታ ሕዝቦች ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስን ቢመርጡም፣ ሰዎች በተውለዱበት አገር ሆነው የልማትና ውጤት ተጠቃሚ የመሆን መብታቸው የተጠበቀ እንዲሆንላቸው ያስፈልጋል ብለው የሰዎችም ምርጫ ከተወለዱበት አገራቸው ርቀው ቋንቋቸውንና ባሕላቸውን መርሳት እንደማይፈልጉ አስረድተዋል።

የአውስትራሊያ ልቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፒተር አንድሪው በበኩላቸው በብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ የሚደረጉት ውይይቶች ገንቢና ሰፊ ርዕሠ ጉዳዮችን በመዳሰስ፣ ቅዱሳት መጽሐፍትን በማካተት ሃሳባቸውን ያካፈሉበት እንደሆነ አስረድተው በዚህም መሠረት የሲኖዶሱ አባቶች፣ ቅዱስ ወንጌል ስለ ወጣቶች ሕይወት በማስመልከት አጠቃላይ ወቅታዊ ገጽታን እንዲገልጽ መፈለጋቸውን ተናግረዋል።

የሲኖዶሱ አባቶች በጉባኤው መካከል ከእምነት የራቁ ቤተሰቦች ልጆች መኖራቸውን በማስታወስ እነዚህ ወጣቶች በጉባኤው ላይ ወላጆቻቸውንና ጓደኞቻቸውን በመወከል ሃሳባቸውን መግለጻቸውን ተናግረዋል። ሊቀ ጳጳስ ኮመንሶሊ ከእምነታቸው የራቁትን ቤተሰቦች አስመልክተው ሰፊ ውይይት መደረግ እንዳለበት ገልጸው፣ ውይይቱም በየአገራቱ በሚገኙ የብጹዓን ጳጳሳት ጉቤዎች በኩል ቢደረግ መልካም ይሆናል ብለዋል። የየአገራቱ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ወላጆች ወይም ልጆቻቸው ከእምነታቸው ወደ ኋላ ያሉበትን ምክንያት በዝርዝር አጥንተው ምላሽ ለመስጠት እንደሚችሉ ገልጸዋል።            

22 October 2018, 17:23