Rifugiati siriani in Libano -  Lasalliani, Fratelli delle scuole cristiane  Rifugiati siriani in Libano - Lasalliani, Fratelli delle scuole cristiane  

በሶርያ ውስጥ የሚገኙ ኩርዶች ክርስቲያኖችን እንደማይፈልጓቸው ተገለጸ።

ከኩርድ ባለስልጣናት በኩል ይፋ የሆነው ትዕዛዝ፣ በቃሚሺሊ፣ በዳርባሲያ እና በማሊኪያ ከተሞች የሚገኙትና የቤተክርስቲያን ንብረት የሆኑ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ የሚያዝ ቢሆንም የቤተክርሲያን አባቶች ችላ ማለታቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሰሜን ምስራቅ ሶርያ፣ ከደማስቆ እውቅናን ያላገኘች የኩርድ ግዛት፣ በአካባቢው የሚገኙ የቤተክርስቲያን ንብረት የሆኑ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ማድረጉን ብጹዕ አቡነ ሂንዶ ገልጸዋል። ይህን ድርጊት አለም አቀፉ ማሕበረሰብ በዝምታ እንዳይመለከተው ጥሪ መቅረቡን ብጹዕ አቡነ ሂንዶ ተናግረዋል።

ከኩርድ ባለስልጣናት በኩል ይፋ የሆነው ትዕዛዝ፣ በቃሚሺሊ፣ በዳርባሲያ እና በማሊኪያ ከተሞች የሚገኙትና የቤተክርስቲያን ንብረት የሆኑ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ የሚያዝ ቢሆንም የቤተክርሲያን አባቶች ችላ ማለታቸው ታውቋል። የኩርድ ባለስልጣናት ትምህርት ቤቶቹ እንዲዘጉ የወሰኑበት ዋናው ምክንያት በትምህርት ተቋማቱ ሲነገርበት የቆየው የሶርያ ጥንታዊ ቋንቋ እንዳይገለገልበትና የኩርዶችን ታሪክ እንዲጠፋ ስለሚያደርግ የታሪክ ትምህርትም እንዳይሰጥ ስለሚፈለግ ነው ተብሏል።

የክርስትያን ማሕበረሰብን ለማግለል የተደረገ ሴራ ነው፣

የሶርያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ዣክ ቤናም ሂንዶ፣ ስደት ላይ ለሚገኝ ቤተክርስቲያን እርዳታን ለጋሽ ለሆነው ካቶሊካዊ ድርጅት እንዳስታወቁት በሶርያ ሰሜናዊው ምስራቅ ክፍለ ሃገር ችግሩ እየከፋ መምጣቱን ገልጸዋል። ሊቀ ጳጳሱ እንደገለጹት ከሶርያ መንግስት እውቅናን ያላገኘ ነገር ግን በሰሜናዊ ምስራቅ ክፍለ ሃገር ራስ ገዝ መንግስትን ለመመስረት በመንቀሳቀስ ላይ ያለ የሶሪያ ዴሞክራሲያዊ ፌደሬሽን ቡድን በአካባቢው የሚገኙ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ማድረጉን ገልጸዋል። ሊቀ ጳጳሱ እንደገለጹት ከአንድ አመት በፊት በግዛቱ የሚገኘውን የመንግሥት ትምህርት ቤትን በቁጥጥሩ ሥር በማዋል የራሱን የትምህርት እቅድ በመዘርጋት ለራሱ በሚስማማ መንገድ የመማሪያ መጽሐፍትን ማሳተሙን አስረድተዋል። ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሂንዶ በማከልም የኩርድ ባለስልጣናት ከዚህ በፊት የግል ትምህርት ቤቶች እንደማይነኩ ቃል የተገባላቸው ቢሆንም ቃላቸውን አፍርሰው የትምሕርት ቤቶቹ በሮች ተዘግተው እንዲታሸጉ አድርገዋል ብለዋል። 

በውሳኔው መላው ክርስቲያን ሰለባ ይሆናል፣

በውሳኔ የተሰማቸውን ስጋት ያልሸሸጉት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሂንዶ እንደገለጹት በሃሳክ የሚገኙ ሌሎች ስድስት ትምህርት ቤቶችም እንደሚዘጉና ይህም በኩርድ ሥርዓተ ትምህርት ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችልና ተማሪዎችንም በጽኑ ሊጎዳቸው እንደሚችል ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል። ይህ ውሳኔ ተማሪዎች መቅሰም ያለባቸውን በጥራት የታገዘ የትምህርት ሥርዓትን በማደናቀፉ የተነሳ መላው ትውልድ የችግሩ ሰላባ እንደሚሆን ለኩርድ ባለስልጣናት ማስረዳታቸውን ተናግረዋል። ሊቀ ጳጳሱ ለኩርድ ባለስልጣናት ላቀረቡት ሃስብ የተሰጣቸውን መልስ ሲናገሩ፣ የኩርድ መንግሥት ይዞ የተነሳውን ዓላማ እስከሚያሳካ ድረስ ስድስትም ይሁን ሰባት ትውልድ ሊያልፍ ይችላል ማለታቸውን ገልጸዋል።

የኩርዶችን ይዞታ ለማስፋት ክርስቲያኖችን ማስወገድ፣

በአካባቢው ኩርዶች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የሚያመላክተው አካባቢውን በሙሉ የኩርዶች ግዛት ለማድረግ በመፈልግ ክርስቲያኖችን በማግለልና በማራቅ ላይ እንደሆነ መመልከት ይቻላል በማለት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሂንዶ አስረድተዋል። ይህ እንደሚከሰት ስጋት እንዳደረባቸው ከ2007 ዓ. ም. ወዲህ ስሞታን ሲያቀርቡ መቆየታቸውን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሂንዶ ተናግረዋል። በማከልም ኩርዶች ክርስቲያኖችን ከክልላቸው አስወጥተው የራሳቸውን አስተዳደር ለማንሰራራትና የጎሳቸውን ቁጥር ለማሳደግ ጥረት እንደሚያደርጉ አስረድተዋል። በሶርያ ከጠቅላላው የሕዝብ ብዛት የኩርዶች ቁጥር 20 በመቶ ብቻ እንደሆንና ከእነዚህም መካከል ግማሹ ብቻ የራሱን መንግሥት ሊያቋቁም እንደሚንቀሳቀስ አስረድተዋል።

የዓለሙ ማሕበረሰብ በዝምታ መመልከት የለበትም፣

የሶርያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ዣክ ቤናም ሂንዶ፣ ስደት ላይ ለሚገኝ ቤተክርስቲያን እርዳታን ለጋሽ ካቶሊካዊ ድርጅት ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፣ የዓለሙ ማሕበረሰብ በተለይም ለአውሮፓ ሕብረት አገሮች መንግሥታት ጥሪያቸውን አቅርበዋል። በክልሉ የሚገኙት የቤተክርስቲያን የትምህርት ተቋማትን ከባድ ሕዘን ያጋጥማቸዋል ያሉት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዣክ ቤናም ሂንዶ ንግግራቸውን በመቀጠል እንደገለጹት፣ ቤተክርስቲያናቸው በስሩ የሚገኙትን ትምህርት ቤቶችን ከ1924 ዓ. ም. ጀምሮ ሲያስተዳድር እንደቆየ ገልጸው፣ ከረጅም ዓመታት አገልግሎት በኋላ ሊዘጋ ይችላል የሚል ግምት እንዳልነበራቸው አስረድተዋል። የኩርዶችን ውሳኔ የምዕራቡ ዓለም በዝምታ መመልከት የለበትም ብለው ክርስቲያንነታችሁን የምትገልጹት ሰብዓዊ መብቶቻችንን በማስከበር፣ በትውልድ አገራችን የሚደርስብንን ጥቃት በመከላከል የሰላም ብርሃን እንዲበራ በማድረግ መሆን አለበት ብለዋል።  

           

03 September 2018, 18:04