ፈልግ

Migranti: ex Moi Torino, si sgombera una palazzina Migranti: ex Moi Torino, si sgombera una palazzina  

የቅዱስ ኤጂዲዮ ማህበር፣ ስደተኞች ማህበራዊ ኑሮአቸውን ለማሳደግ ጥረት እንዲያደርጉ አሳሰበ።

በአሥሩ የኢጣሊያ ከተሞች የሚኖሩት ስደተኞች የአውሮጳውያኑን የቀን አቆጣጠር ከሚከተሉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ጋር በመሆን የፍልሰታ ማርያም ክብረ በዓል በሕብረት አክብረው ውለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የአውሮጳውያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ ትናንት ተከብሮ የዋለውን የፍልሰታ ማርያም በዓል ምክንያት በማድረግ፣ በኢጣሊያ የቅዱስ ኤጂዲዮ ማህበሩ ባስተላለፈው የአደራ መልዕክት፣ በኢጣሊያ የሚገኙ ስደተኞች ከሕዝቡ ጋር ያላቸውን ማህበራዊ ግንኙነት ለማሳደግ ጥረት እንዲያደርጉ አሳስቧል። ከኢጣሊያ ከተሞች መካከል በአሥሩ የሚኖሩት ስደተኞች እና የስደተኛ ቤተ ሰብ አባላት ከሚኖሩበት መንደር ወጥተው፣ ከአካባቢው ሕዝብ ጋር በመሆን የአውሮጳውያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ጋር በመሆን ትናንት ዓመታዊውን የፍልሰታ ማርያም ክብረ በዓል በሕብረት አክብረው መዋላቸው ታውቋል። 

አሉታዊ አመለካከት ይወገድ! 

በኢጣሊያ ውስጥ ቋሚ መኖሪያ ለሌላቸው ስደተኞች፣ የመኖሪያ ቤት አገልግሎት መስጫ ክፍል አስተባባሪ የሆኑት ክቡር አቶ አውጉስቶ ዳ አንጀሎ፣ የቅዱስ ኤጂዲዮ ማህበርን በመወከል እንዳስገነዘቡት፣ ዓመታዊውን የፍልሰታ ማርያም በዓል በጋራ ለማክበር የተፈለገበት ምክንያት በኢጣሊያ ሕዝብ እና በስደተኛው ማሕበረ ሰብ መካከል ያለው ግንኙነት የበለጠ ለማሳደግ ነው ብለዋል። ከቅርብ ወራት ወዲህ በአንዳንድ የኢጣሊያ ግዛቶች ውስጥ የታዩትን አሉታዊ ገጽታዎች የጠቆሙት አቶ አውጉስቶ ዳ አንጀሎ፣ ለዚህ ምክንያቱ በሕዝቦች መካከል የረባ ግንኙነት እና ትውውቅ ባለመኖሩ ነው ብለዋል። ስለዚህ ይህን ታላቅ በዓል በሕብረት በማክበር፣ የስደተኞችን ችግር በቅርብ ሆነው በመመልከት፣ በሁለት ዓይነት ሕዝብ መካከል የትውውቅ እና የመተጋገዝ ባህልን ለማሳደግ ነው ብለዋል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “መልካምን አድርጉ!”

የኢጣሊያ ካቶሊካዊ ምዕመናን ከስደተኛው ቤተ ሰብ ጋር በጋራ ባከበሩት በዓል አዛውንት፣ ስደተኛ ቤተሰብ እና ወጣቶችም መገኘታቸውን የገለጹት አቶ አውጉስቶ ዳ አንጀሎ፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “ክርስቲያን ለመሆን ክፉ አለማድረግ በቂ አይደለም፣ ነገር ግን መልካምን ማድረግ ያስፈልጋል” ያሉትን አስታውሰው በቅርቡ በርካታ ቁጥር ያላቸው ወጣት ስደተኞች ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ለመገናኘውት ወደ ሮም ከተማ መጥተው እንደነበር አስታውሰው፣ ከቅዱስ ኤጂዲዮ ማሕበር ጋር በመተባበር ርዕሠ ሊቃነ ፍራንቺስኮስ የነገሯቸውን ምክር ተቀብለው በተግባር እየገለጹ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ስደተኞች ለሚኖሩበት አገር ሃብት ናቸው፣

ስደተኞች ለሚኖሩበት አገር ትልቅ ሃብት ናቸው ያሉት አቶ አውጉስቶ ዳ አንጀሎ ስደተኞች አቅመ ደካማ የሆኑ አዛውንትን በመንከባከብ፣ ረዳት የሌላቸውን ቤተ ሰብ በመርዳትና ሕጻናትን በመጠበቅና በማሳደግ እጅግ አስፈላጊ ሥራዎችን ያከናውናሉ ብለዋል። አቶ አውጉስቶ ዳ አንጀሎ በንግግራቸው እንደገለጹት የኢጣሊያ ሕዝብ በአገሩ በሚገኙት ስደተኞች ላይ እምነት ቢጎድላቸው ምክንያቱ የተሰደዱበትን ምክንያት ካለማወቅ እና ስደተኞች ለሚኖሩበት አገሩ ሕዝብ የሚሰጡትን ድጋፍ ካለመረዳት የተነሳ ነው ብለዋል። በማከልም ስደተኞም ቢሆኑ፣ በርካታ ወጣቶች ወደ ኢጣሊያ ሲመጡ በጥርጣሬ እና በስጋት የተሞላ ልብ ይዘው ቢመጡም ከአጭር ጊዜ ቆይታ በኋላ ያ ሁሉ ተወግዶ ወደ መልካም መግባባት ላይ ይደርሳሉ ብለዋል።

ማሕበራዊ ቀውሶችን ለማስወገድ መተባበር፣

በቅዱስ ኤጂዲዮ ማህበር ሥር፣ ቋሚ መኖሪያ ቤት ለሌላቸው ስደተኞች፣ የመኖሪያ ቤት አገልግሎት መስጫ ክፍል አስተባባሪ የሆኑት ክቡር አቶ አውጉስቶ ዳ አንጀሎ እንዳስገነዘቡት በኢጣሊያ ሕዝብ እና በስደተኛው ማህበረ ሰብ መካከል መተዋወቅ ካለ ወደ ፊት ሊያጋጥሙ የሚችሉትን ማሕበራዊ ችግሮች በጋራ መወጣት ይቻላል ብለዋል። በመጨረሻም የኢጣሊያ ሕዝብ በአገሩ በሚገኙት ስደተኞች ላይ እምነት ቢስ ከመሆን ይልቅ ከማሕበራዊ ቀውስ ለመውጣት ድጋፍ የሚሆኑትን ስደተኛ ወጣቶችን ማቅረብ እንደሚያስፈልግና አብሮ በሰላምና በፍቅር የሚዘልቅ ማሕበራዊ ኑሮ ምኑን ያህል ውጤታማ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል።

16 August 2018, 18:06