ካርዲናል ብርሃነየሱስ    ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን  

የ2010 ዓ/ም የፍለስታ ጾም በማስመልከት የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን መልእክት

የ2010 ዓ/ም የፍለስታ ጾም በማስመልከት የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን መልእክት

 

ከሁሉ አስቀድሜ ለመላው ኢትዮጵያውያን ካቶሊካውያን ምእመናንና የፍልሰታ ማርያም ክብረ  በዓል ለሚያከብሩ ሁሉ እንኳን ለ2010 ዓ/ም ለፍልሰታ ጾም በሰላም አደረሳችሁ እያልኩ የተቀደሰ የተባረከ የፍልሰታ ጾም እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ፡፡ የ2010 ዓ.ም የፍልሰታ ማርያም ጾም በማስመልከት ለመላው ካቶሊክ ምእመናን ምኞቴንና ቡራኬዬን በምሰጥበት ጊዜ ታላቅ ደስታ እየተሰማኝ ነው፡፡ የአፍሪካ እመቤት የቤተክርስያን እናት የሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ረድታን ላለፉት 4 ዓመታት ስንዘጋጅበት የቆየነውን 19ኛው የአመሰያን ጉባኤ በታላቅ ስኬት አስተናግደን በጨረስንበት ማግስት ለዚህ የጾም ወቅት ስንዘጋጅ ከታላቅ ደስታና ምስጋና ጋር ነው፡፡

የፍልሰታ ማርያም ክብረ በዓል፤ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋዋና በነፍሷ ወደ ሰማይ የወጣችበት፤ ከእመቤታችን ድንግል ማርያም በዓላት ሁሉ ከፍ ያለ በዓል ረቡዕ ነሐሴ 16/ 2010 ዓ.ም በካቶሊካዊያን ምእመናን ዘንድ ይከበራል፡፡ ከነሐሴ 1 እስከ ነሐሴ 15 ለእመቤታችን ፍልሰታ ክብረ በዓል ምእመናን ከፍተኛ መንፈሳዊ ዝግጅት በማድረግ በጾምና በጸሎት በመትጋት ያሳልፋሉ፡፡ ይህ ጾምና ምህለላ በሙሉ ልብ መሆን እንዳለበትና የተቸገሩትን በመርዳትና የተጣሉትን በማስታረቅ እንዲሁም የበደልናቸውም ካሉ ይቅርታን በመጠየቅ ለክብረ በዓሉ መዘጋጀት አስፈላጊ እንደሆነ ለመግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ በዚህ አጋጣሚ የሰላም ንግስት የሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ለአገራችን እውነተኛ የሆነውን የልጇን ሰላም እንድታሰጠን ከልብ እንድንማፀናት አደራ እላለው፡፡

እመቤታችን ድንግል ማርያም የተቸገሩትን መርዳት አስፈለጊ እንደሆነ አስተማሪያችን ናት፡፡ ዘመድዋ ቅድስት ኤልሣቤጥ ለመውለድ በተቃረበች ጊዜ ለመርዳት ፈጥና የሄደችና የረዳቻት እርሷ ነበረች፡፡ በቃና ዘገሊላ ለሙሽሮች ወይን ባለቀባቸው ጊዜ ችግራቸውን ተረድታ ወደ ልጇ ቀርባ የረዳች እርሷ ነበረች፡፡ በዚህም የተቸገሩትንና ድሆችን መርዳት አስፈለጊ እደሆነ አስተምራናለች፡፡ እናም በርሷ የፍቅር ሥራና ትሕትና የተሞላበት ሕይወት ልንማረክ ይገባናል፡፡

በአሁን ሰዓት በየቤቱ በችግር ላይ ያሉ ወገኖችን ማሰብ አለብን፡፡ ሁላችንም ክርስቲያኖች እግዚአብሔር ከሰጠን ፀጋ ለድሆች በማካፈል ጾማችንን በትግባር መኖር አለብን፡፡ ነገር ግን ይህ በጾም ወቅት ብቻ የሚደረግ የአንድ ጊዜ ተግባር ሳይሆን ለዘለቄታ መለማመድ ያለብን ተግባር ነው፡፡ በተለይም እያንዳንዱ ማህበራዊ ውሳኔዎቻችን ድሆችን ከግንዛቤ ውስጥ ያስገባ ማድረግ አለብን፡፡

በተለይ በዚህ ጊዜ በአገራችን የተለያዩ ክፍሎች በሚከሰቱ ግጭቶች ምክኒያት ከየቀያቸው ተፈናቅለው በችግር ላይ የሚገኙ በርካታ ቤተሠቦች አሉ፡፡ ቤተሠብ ሲፈናቀል ደግሞ በቅድሚያ የሚጠቁት ሕጻናትና እናቶች ናቸው፤ በዚህ የጾም ወቅት ለነዚህ ወገኖች ልዩ ጸሎትና ድጋፍ ማድረግ አለብን፡፡ ቤተክርስቲያናችን እንደተለመደው ከህዝብ ጎን በመቆም ተፈናቃዮች ባሉበት ቦታ ተገኝታ ለተጎዱ ወገኖች አስፈላጊውን መንፈሳዊና ቁሳዊ ድጋፍ በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡ መእምናንም ይህንኑ ተግባር በመደገፍ በጸሎትና በተግባር ከቤተክርስቲያን ጋር እንዲተባበሩ እንዲሁም በየአቅራቢያቸው ለሚያጋጥሟቸው ተጎጂዎች የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ አደራ እንላለን፡፡ በተለይም ባለፉት ሁለት ቀናት በሶማሌ ክልል በጅጅጋ በተፈጠረው አለመረጋጋ በአከባቢው ላሉ ነዋሪዎች ከባድ ፈተና ሆኖ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ እነኚህን ወገኖች የሰላም እናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም በጥበቃዋ ስር እንድታደርጋቸውና ሰላሙን እንድታማልደን መእምናን ሁላችሁም በጸሎት እንድትተጉ አደራ እላለሁ፡፡

በመጨረሻም

1.     ክርስቲያኖች ከሌሎች እምነት ተከታዮች ጋር በሰላም፣ በመከባበር እና እርስ በርስ ተዋደው በመኖር የጾምና የጸሎት መንፈስ ለብሰው እንዲጓዙ አሳስባለሁ፡፡

2.     ሁላችንም የሰላም መሳሪያ በመሆን ለአገራችን ብሎም ለመላው ምስራቅ አፍሪካ ሰላማዊ አንድነት መረጋገጥ እንድንተጋ አደራ እላለው፡፡

3.     ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ቀርቶ ሰዎች በአገራቸው ሠርተው እንዲበለጽጉና አገራቸውን እንዲያሳድጉ ለማሳሰብ እፈልጋለሁ፡፡

4.     እግዚአብሔር ክረምቱን ባርኮ ዝናቡን በሚያስፈልግበት ቦታ ሁሉ እንዲሰጠን መጸለይ እንድንቀጥል አደራ እላለው፡፡

የጾም ወራትን በጾምና በጸሎት በተጋድሎም በማሳለፍ ለበዓለ ፍልሰታዋ በሰላም ለመድረስ ያብቃን፡፡ አምላክ የተቀደስ የተባረከ ጾመ ፍልሰታ ለመላው ካቶሊካዊያን ምእምናን ያድርግልን እያልኩ የአፍሪካ እመቤት፣ የሰላም ንግስት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለኛ ለልጆቿ ትለምንልን፡፡ አሜን

ቸሩ አምላካችን በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ኢትዮጵያን ይባርካት፡፡

 

† ካርዲናል ብርሃነየሱስ

  ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን

  የካቶሊካውያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንትና የአመሰያ የበላይ ጠባቂ

የ2010 ዓ/ም የፍለስታ ጾም በማስመልከት የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን መልእክት
08 August 2018, 16:22