ፈልግ

የኢየሱስ መልክ በታቦር ተራራ ላይ በተቀየረበት ወቅት የኢየሱስ መልክ በታቦር ተራራ ላይ በተቀየረበት ወቅት  

የነሐሴ 13/2010 ዓ.ም ሰንብት ዘደብረታቦር/ዘክረምት 7ኛ ቃለ እግዚኣብሔር አስተንትኖ

“በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት የሚል ድምጽ መጣ” (ሉቃ 9፡ 28-34)

የዕለቱ ምንባባት

1.     ዕብ 11፡23-29

2.    1ጴጥ 1፡15-21

3.    ሐዋ 7፡44-50

4.    ሉቃ 9፡ 28-37

የተከበራችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እና በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

ምድርን በሰማያዊ ጠል እያለመለመ ለእኛ ይሆኑ ዘንድ ፍሬን እንዲሰጡ እጽዋትን በምድር ላይ እንዲበቅሉ ያደረገ ልዑል እግዚአብሔር ዘመነ ክረምትን በማስዋብ እስከዚህ አድርሶናልና ስሙ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የተመሰገነ ይሁን።

በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ስርዓተ ዓምልኮ መሰረት ዛሬ የደብረ ታቦር ወይንም ቡሄ ይከበራል። ቡሄ በመላው ሀገራችን በየዓመቱ ነሐሴ 13 ቀን የሚከበር በዓል ሲሆን በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ዓቢይ ወይም ዋና ከሚባሉት በዓላት ውስጥ አንዱ ነው፡፡

የዚህ በዓል መሠረት የክርስቲያን እምነት ሲሆን ደብረ ታቦር በግዕዝ የታቦር ተራራ ማለት ነው፣ ይህ ተራራ የሚገኘው አሁን ፍልስጤም ተብሎ በሚጠራው ሀገር ነው፡፡ ደብረ ታቦር ወይንም የታቦር ተራራ ኢየሱስ ክርስቶስ ሦስት ደቀ-መዛሙርቱን ይዞ ወደ ተራራው የወጣበትና ፊቱ እንደጸሐይ የበራበት ልብሱም እንደብርሃን ነጭ የሆነበት ቦታ ነው፡፡ ይህ ቦታ ጌታ ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት ተራራ ነው።

ታሪኩም እንዲህ ነው ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ይዞ ለመጸለይ ወደ አንድ ተራራ ላይ ወጣ፡፡ በሚጸልይበትም ጊዜ መልኩ ተለወጠ ልብሱም ነጭ ሆኖ አንጸባረቀ፡፡ እነሆም ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው፡፡ ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን “ጌታ ሆይ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው ብትወድስ በዚህ ሦስት ዳስ አንዱን ለአንተ አንዱን ለሙሴ አንዱንም ለኤልያስ እንሥራ አለ፡፡ እርሱም ገና ሲናገር እነሆ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው እነሆም ከደመናው፡፡ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት የሚል ድምጽ መጣ” (ሉቃ 9፡ 28-34)። የደብረ ታቦር አብይ መሠረቱ ይሄ ሲሆን በአገራችን የክረምቱ አፈና ተወግዶ የብርሃን ወገግታ የሚታየውም በዚህ በዓል አካባቢ ስለሆነ ይቺ ዕለት ቡሄ የሚለውን ስያሜ አገኘች፥፡ ቡሄ ማለት ገላጣ የተገለጠ  ማለት ነው፡

ቅዱሳን የእግዚአብሔር ቤተሰቦች! የእምነት ጉዳይ የሕይወት ጉዳይ ነው! ይህም በመሆኑ ሰዎች ሕይወትን ያገኙ ዘንድ አንዱ ስለ ብዙዎች ራሱን አሳልፎ ሰጠ፡፡ ከማስተማርና የተአምራትን ሥራ ከማሳየት ጀምሮ ስለ ሰው ልጆች ሕይወት መከራን መቀበሉ በሰው ልጆች ፍጹም ፍቅር ተገዶ ነው፡፡ ዛሬም የእግዚአብሔር ልጆች በዚህ ታላቅና አምላካዊ ሕግ ይታወቃሉ፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም እምነት በመጽናት ክርስቲያናዊ ጉዞአቸውን ይገፋሉ፡፡

ታላላቅ የእምነት አባቶቻችንም በዚህ ታላቅ እምነት በዘራቸው በነገዳቸው በጊዜያዊ ሃብት ሳይታለሉ በመጽናት እስከ ፈጻሜ ደርሰዋል፡፡ ዛሬ ከተነበቡልን ምንባባቶች የምንረዳው ይህንኑ ነው፡፡ የዕብራውያን ደራሲ ስለ ሙሴ ሲናገር ሙሴ ካደገ በኋላ የፈርዖን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እምቢ አለ፣ ከግብጽም ብዙ ገንዘብ ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለ ጠግነት እንዲሆን አስቦአልና ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ (ዕብ 11፥ 24-26) እያለ በእምነት ጸንቶ መኖር የሚያስገኘውን ውጤት ታላቅ መሆኑን ያሳየናል፡፡

እምነታችንና ተስፋችን በልዑል እግዚአብሔር ላይ አድርገን  የምንኖር ከሆነ ለፈጠረን ፍጥረቱ ሁሉ ለሕይወታችን የሚያስፈልገንን ሁሉ ይሰጠናል፡፡ በየጊዜው የምንበላውን፣ የምንጠጣውን፣ የምንለብሰውንና እንዲሁም ሌላ የሚያስፈልገንን ሁሉ ይሰጠናል፡፡ እያንዳንዳችን ያለን ሀብት፣ ቤት፣ ንብረት ሁሉ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው፡፡ ታዲያ እግዚአብሔርም  ከእኛ የሚፈልገውና የሚጠብቀው ነገር አለ፡፡ እርሱ ከእኛ የሚጠብቀው እኛ ሕጉንና ትእዛዙን እንድንጠብቀና በሕጉና በትእዛዙ ጸንተን እንድንኖር ነው፡፡ ሁላችንም በፍቅርና በሰላም በጽድቅ በንጽሕና በመልካም ስነ-ምግባር እንድንኖር ከክፋት ከተንኮል ከኃጢአት ተጠብቀን እንድንኖር እግዚአብሔር ከእኛ ይጠብቃል፡፡ እምነታችንና ተስፋችን በእርሱ ላይ እንድናደርግ ይፈልጋል። በ1ኛ ጴጥ 1፥20-21 “ዓለም ሳይፈጠር እንካን አስቀድሞ ታወቀ፣ ነገር ግን እምነታችሁና ተስፋችሁ በእግዚአብሔር ይሆን ዘንድ ከሙታን ባስነሳው ክብርንም በሰጠው በእግዚአብሔር በእርሱ ስለምታምኑ ስለ እናንተ በዘመኑ መጨረሻ ተገለጠ” በማለት ያስተምረናል፡፡

የተከበራችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች! ይህን እግዚአብሔር ተሰብስበን የምናመልክበት፣ ታላቅነቱን የምናውጅበት፣ ስለ እርሱ በድፍረት የምንመሰክርበት ቅዱስ ስፍራ ቤተ ክርስቲያን አለን። በዚህ ቅዱስ ስፍራ ቃሉ ይታወጃል፣ መስዋዕት ይሰዋል ታዲያ በፍጹም ፍቅር ልንወደውና ልንጠቀምበት የሚገባ ታላቅ ቦታ በመሆኑ ሁል ጊዜ እግዚአብሔርን “የአንተ እዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው” ብለን በልባችን እንዲኖር ልንፈቅድለት ይገባል፥

እግዚአብሔር በልዪ ልዪ ምክንያት ሰዎችን ይመርጣል፣ ለአገልግሎት ይለያል፣ ምስጢር ይገልጻል እርሱ የወደደውን ያደርጋል፣ ዛሬም ልክ እነዚህ ሦስቱን ደቀ-መዛሙርት እንደመረጠ ከእኛም መካከል እርሱ ለፈለገው ሥራ ይመርጣል ከእኛ የሚጠበቀው መዘጋጀት ብቻ ነው፡፡ ሰው ሲመርጥ ፊትን ያያል፣ እግዚአብሔር ግን  ሲመርጥ ልብን ያያል፡፡ ስለዚህ በእግዚአብሔር ለመመረጥ እንትጋ፣ እርሱ ሲመርጥ ለክብር ነው ለከፍታ ነው፡፡

“እንደ ብርሃን ነጭ ሆኖ ታያቸው” ይላል ወንጌሉ አዎ ብርሃን ጨለማን እያስወገደ ሰዎች ሁሉ ሳይሰናከሉና ሳይደናቀፉ ሳይወድቁም ወደ አሰቡበት ቦታ እንዲደርሱ ሊሠሩ ያሰቡትንም ሥራ እንዲሠሩ የሚያስችል የልዑል እግዚአብሔር ታላቅ ስጦታ ነው። ክርስቶስ እውነተኛ ብርሃን ነው። ስለዚህ ሁሉ በእርሱ የሚሆንና የሚከናወን ያለ እርሱ ምንም የሚሆን ነገር የሌለ እውነተኛ የዓለም ብርሃን ኢየሱስ ክርስቶስ ጨለማ በማያሸንፈው እውነተኛ ብርሃን ተመስሉዋል።

እኛም መልካም ሥራ ለመሥራት ከመረጣቸው ሰዎች መካከል ነን። እውነትን እንድናደርግ መርጦናል ስለሆነም ለዚህ ታላቅ ሥራ የተገባን እንድንሆን ዘወትር በጸሎት ልንተጋ ይገባል። በጨለማ የተመሰለውን ክፉ ሥራችንን አስወግደን መልካም ሥራችን ግልጽ ይሆን ዘንድ ጨለማ በማያሸንፈው በእውነተኛ ብርሃን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንና በመንገዱ መመላለስ ይገባናል፡፡ ይህንን እንድናደርግ አምላካችን እግዚአብሔር በጸጋው ይርዳን አሜን!!!

በድምጽ የቀረበውን ዘገባ ለማዳመጥ ተጫወት የሚለውን ምልክት ይጫኑ
18 August 2018, 11:56