ፈልግ

የነሐሴ 06/2010 ዓ.ም ሰንበት ዘክረምት 6ኛ ቃለ እግዚኣብሔር አስተንትኖ በክቡር አባ ግርማቸው ተስፋዬ የነሐሴ 06/2010 ዓ.ም ሰንበት ዘክረምት 6ኛ ቃለ እግዚኣብሔር አስተንትኖ በክቡር አባ ግርማቸው ተስፋዬ 

የነሐሴ 06/2010 ዓ.ም ሰንበት ዘክረምት 6ኛ ቃለ እግዚኣብሔር አስተንትኖ

በክቡር አባ ግርማቸው ተስፋዬ

የነሐሴ 06/2010 ዓ.ም ሰንበት ዘክረምት 6ኛ ቃለ እግዚኣብሔር አስተንትኖ በክቡር አባ ግርማቸው ተስፋዬ

 

የዕለቱ ምንባባት

1.     1ቆሮ 8፡ 1-13

2.      1ጴጥ 4፡ 1-5

3.     ሐዋ 26፡ 1-23

4.     ማቴ 12፡ 38-50

 

የተከበራችሁ የእግዚአብሔር ቅዱሳን ቤተሰቦች እና በጎ ፈቀድ ያላችሁ ሁሉ!

በቤተ ክርስቲያናችን የስርዓተ አምልኮ አቆጣጠር ደንብ መሰረት የዛሬው ሰንበት ሰንበት ዘክረምት 6ኛ በመባል የሚጠራ ሲሆን ታላቅ የሆነው እግዚኣብሔር በእድሜአችን ውስጥ ዛሬን እንድናይ ፈቅዱዋልና ስሙ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የተመሰገነ ይሁን፡፡ እንደ ሁልጊዜው በቃሉ አማካኝነት ሲጎበኘን ዛሬ በተነበቡልን ምንባባቶችም አባታዊ ምክሩንና አምላካዊ ተግባሩንም ያስታውሰናል፡፡ አሁን የምንገኝበት ወቅት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ሰማይ መውጣቱዋን ለማስታወስ የአስራ ስድስት ቀን ጾምና ሱባዔ በማድረግ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ቦታ በመስጠት እያንዳንዳችን ራሳችንን የምንመረምርበት ጊዜ ነው፡፡

ብዙ ሥጋዊ ነገሮችን እየወደድናቸው ለጌታ ክብር ብለን እንዳልወደድናቸው በመተው በሁለንተናዊ የሕይወት ጉዞአችን ለሌሎች ምሳሌ በመሆን እንድንጓዝ በአንደኛው ቆሮንቶስ 8፥1-13 ባለው ክፍል ያስተምረናል በዚህ መንፈስ ተጉዘን እንደሆን ለእኛ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ፣ ለእርሱ የሆንን፣ አንድ አምላክ አብ አለን፣ ነገር ሁሉም በእርሱ በኩል የሆነ እኛም በእርሱ በኩል የሆንን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን፣ በማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ (1ኛ ቆሮንቶስ 8፡ 8) ላይ ያረጋግጥልናል፡፡

ስለዚህ ይህንን ጌታ ለማገልገል ዝግጁ  እንድንሆንና ሁለንተናዊ ማንነታችን በእርሱ በጌታችን በአምላካችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ጥለን ራሳችንን ዝቅ አድርገን እርሱ ወደ ሚመራን እርሱ ወደ ሚጠቁመንና ያዋጣችኋል ወዳለን ወደ እርሱ እንድንገሰግስ ተጋብዘናል፡፡ ምክንያቱም ይህ ጌታ ነው ስለ እኛ በስጋው መከራንና ስቃይን ተቀብሎ ነጻ ያወጣን ሰለሆነ ከእንግዲህ ወዲህ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ እንደ ሰው ምኞት እንዳንኖር ተጠርተናል ይህም በ1ጴጥ 4፥1-2 ላይ ተብራርቶልናል፡፡ በእርግጥ ይህ ጉዞ ቀላል አይደለም ብዙ ድካምና መከራ አለው፡፡

የተወደዳችሁ የክርስቶስ ቤተሰቦች! ብዙ ቅዱሳን አባቶች ጌታን መከተል የቻሉትና እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ ድረስ እሱን መስለው ሕይወታቸውን ያሳለፉት በክርስቲያናዊ ጉዞአቸው መንገዱ ሁልጊዜ አለጋ በአልጋ እየሆነላቸው አልነበረም፡፡ በብዙ ድካምና መከራ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንገባ ዘንድ ይገባናል (ሐዋ 14፥22) ብለው ሐዋርያት እንዳስተማሩን ያለ ኃጢአታቸው እየተከሰሱ እየተደበደቡ አንዳንዴም ለተራበ አንበሳ እየተሰጡ መከራን በትዕግሥት እየተቀበሉ ነበር፡፡ ክርስቶስን መምሰል እና መስቀሉን መሽከም ማለት ያለ ኃጢአት ለወንጌል ለቤተ ክርስቲያን ህልውና ለእግዚአብሔር ክቡር ስም ሲሉ ከዓለምና ከዓለማውያን የሚመጣ መከራን ሳይሳቀቁ መቀበል ነው ይህም እግዚአብሔር ስለ እኛ ያደረገው መልካም ነገር መሆኑን ማመን ይኖርብናል፥

መልካምን ነገር እንደ ጥፋት መቁጠር ከክርስቶስ እቅፍ ውስጥ እንደ መውጣት ይቆጠራል ምክንያቱም መልካምን ነገር ሁሉ የሚጠላ የክፋት አባት ዲያብሎስ ስለሆነ ነው፡፡ እግዚአብሔርን በሙሉ ልብ ለመከተል ምንም ዓይነት ምልክት አያሻንም ለምን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከምልክቶች በላይ የሆነውን ምልክት ሞቶ በመነሳት አሳይቶናል ነገር ግን ፈሪሳውያን ምልክት አሳየን ብለው በጠየቁት ጊዜ እነርሱን ወደ ንስሐ ለመመለስ የዮናስን ታሪክ ነበር የተረከላቸው፡፡

የተከበራችሁ የክርስቶስ ቤተሰቦች እኛ የሚያስፈልገን እንደ ፈሪሳውያን ተአምር ሳይሆን በእግዚአብሔር ላይ መታመን ነው፡፡ ይህ ከሌለን ከእግዚአብሔር ለመራቅ ቅርብ ነን በእኛ ላይ የእምቢተኝነት መንፈስ ይነግሳል፡፡ እምቢተኛነት ደግሞ ከእግዚአብሔር ያርቀናል፣ ከእግዚአብሔር መራቅ ደግሞ የእግዚአብሔርን ጸጋና በረከት የእርሱን ቸርነትና ምህረት በማጣት ሕይወታችን አሰቃቂና በመከራ የተሞላ ነው የሚሆነው፡፡ ሕይወታችን የተድላና የደስታ የጸጋና የበረከት የሰላምና የምህረት ሕይወት ሊሆን የሚችለው በእግዚአብሔር ላይ እምነት ሲኖረንና የእርሱን ፈቃድ ስንፈጽም ብቻ ነው በዚህም የእግዚአብሔር ልጆች አባትና እናት ወንድምና እህት የምንሆንበትን ጸጋ ሰጥቶናል በዛሬውም ወንጌል የተላለፈልን መልዕክት ይህ ራሱ ነው፡፡

በእግዚአብሔር ላይ እምነት የሌለው ሰው እና የእርሱንም ፈቃድ የማይፈጽም አማኝ በቤቱ ሰላምና ፍቅር ጸጋና በረከት አይኖረውም፥፥ ቤታችን፣ ቤተሰባችን፣ ሀብታችን፣ ንብረታችን፣ ልጆቻችን የሚባረኩት በእግዚአብሔር ላይ እምነት ሲኖረንና የእርሱንም ፈቃድ ስንፈጽም ብቻ ነው፥

በተጨማሪም ልክ ሐዋርያው ጳውሎስ (በሐዋ. 26፡6) ላይ “አሁንም ከእግዚአብሔር ዘንድ ለአባቶቻችን ስለ ተሰጠው ስለ ተስፋ ቃል በጽናት መመስከር የምንችልበትን ጸጋ የምናገኘውም በዚሁ የእምነት ጽናት ነው፥ ስለዚህ ሁላችንም ለዚህ ተጠርተናል በዚህ መንፈስ ተጉዘን የአባታችን የልዑል እግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ለመመስከር ተነስና በእግርህ ቁም ስለዚህ እኔን ባየህበት ነገር ለአንተም በምታይበት ነገር አገልጋይና ምስክር ትሆን ዘንድ ልሾምህ ታይቼልሃለሁና” ብሎ ጳውሎስን እንዳነሳሳው ለእኛም በዚሁ መንገድ  ግብዣውን ያቀርብልናል።

12 August 2018, 08:31