Presinodo giovani lombardia 2018 Presinodo giovani lombardia 2018 

ወጣቶች ለሕይወታቸው የሚጠቅም ቆራጥ ምርጫን ለማድረግ መዘጋጀታቸው ተገለጸ።

“መምህር ሆይ! የምትኖረው የት ነው?” (ዮሐ. 1፤39) በሚለው ጥቅስ በመመራት፣ በመንፈስ ቅዱስ መታደስ የወጣቶች እንቅስቃሴ፣ በኢጣሊያ ፔሩጃ ክፍለ ሀገር ከነሐሴ 2 እስከ ነሐሴ 4 ቀን 2010 ዓ. ም. ድረስ አንድ መንፈሳዊ ስብሰባ በማድረግ ላይ ናቸው።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተጠራውና ከጥቂት ወራት በኋላ ሮም ላይ በወጣቶች ጉዳይ ዙሪያ በስፋት የሚወያይ 15ኛው የመላው ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤ ሊደረግ በተቃረበበት ባሁኑ ወቅት፣ ሦስት ቀን የሚወስድ ስብሰባ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

“መምህር ሆይ! የምትኖረው የት ነው?” በሚለው፣ በዮሐንስ ወንጌል 1፤39 በተጻፈው ጥቅስ በመመራት፣ በመንፈስ ቅዱስ መታደስ የወጣቶች እንቅስቃሴ፣ በኢጣሊያ ፔሩጃ ክፍለ ሀገር ከነሐሴ 2 እስከ ነሐሴ 4 ቀን 2010 ዓ. ም. ድረስ አንድ መንፈሳዊ ስብሰባ በማድረግ ላይ መሆናቸው ታውቋል። ወጣቶች፣ እምነት እና በጥሪያቸው ጥበብና ማስተዋል ያለበት ውሳኔን እንዲያደርጉ የሚሉትን የ15ኛው የመላው ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤ ርዕሦችን ያካተተ መሆኑ ታውቋል።

በግል እምነት ላይ ማስተንተን፤

በእነዚህ ሦስት ቀናት ውስጥ ወጣቶቹ የግል ሕይወታቸውን በመመርመር፣ ከእምነታቸውና ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸው ግንኙነት  ምን እንደሚመስል፣ እንዲሁም መንፈሳዊ ጉዞአቸውንም መለስ ብለው እንደሚመለከቱት የወጣቶቹ ተወካይ አቶ አንጀሎ ብራንካለዎነ ለቫቲካን ዜና አገልግሎት ክፍል ገልጸዋል። የዚህ መንፈሳስዊ ስብሰባ መሪ ጥቅስ ከዮሐ. 1፤39 ላይ “መምህር ሆይ! የምትኖረው የት ነው?” የሚል እንደሆነ የገለጹት አቶ አንጀሎ ብራንካለዎነ፣ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ክፍል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፣ በስብሰባው መካከል ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው “የተሻለ ዓለም የሚገነባው ወጣቶች በሚደርጉት አስተዋጽዖና፣ የሚፈለገውን ተሻሽሎን ለማድረግ ወጣቶች ባላቸው ጽኑ ፍላጎትና ቸርነት በመሆኑ ሊመሰገኑ ይገባል። መንፈስ ቅዱስ የሚያቀርብላችሁን ቆራጥ ምርጫን ለማዳመጥ ፍርሃት አይዛችሁ፣ ሕሊናችሁም ጌታን እንድትከተሉ ሲጠይቃችሁ አትዘግዩ በማለት ያቀረቡት መልዕክት አቶ አንጀሎ ብራንካለዎነ አስታውሰዋል። ወጣቶች በሕይወታቸው መካከል ቆራጥ ምርጭን ለማድረግ ተዘጋጅተዋል ነገር ግን በምርጫ ወቅት አቅጣጫን ማሳየትና፣ ከእነርሱ ጎን በመሆን እገዛን መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል። አቶ አንጀሎ ብራንካለዎነ በማከልም ወጣቶች ለሕይወታቸው ትርጉም እንዲኖር የሚያደርጉት እሴቶችን ለማግኘት መስዋዕትነትን ለመክፈል የተዘጋጁ ቢሆንም ነገር ግን ችሎታ እና ብቃት ያላቸው መሪዎች ከጎናቸው እንዲሆኑ ይፈልጋሉ ብለዋል።

የቤተ ክርስቲያን ተሳትፎ፤

ወጣቶች ከቤተ ክርስቲያን ምን ይፈልጋሉ ያሉት አቶ አንጀሎ ብራንካለዎነ፣ ቤተ ክርስቲያን ከወጣቶች ጋር የቀረበ ግንኙነት እንዲኖራት ምዕመናን አስተያየታቸውን ሲያቀርቡ፣ ወጣቶች ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ሁሉን የሚያሳትፍ እንድትሆን ይፈልጋሉ ብለዋል። ከዚህም በተጨማሪ ወላጆች ለልጆቻቸው ጥንቃቄንና ክትትል የሚያደርጉ መሆን አለባቸው የሚለው የብዙሃኑ አስተያየት እንደሆነ ገልጸዋል። ከዚህ መንፈሳዊ ስብሰባ በኋላ ማለትም ነሐሴ 5 እና 6 ወጣቶቹ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ለመገናኘት ወደ ሮም እንደሚሄዱ ገልጸው፣ ወጣቶች ውስጣዊ እና ውጫዊ ሕይወታቸውን ቀስ በቀስ በመመርመር የእግዚአብሔርን አፍቃሪነት ይገነዘቡታል ብለዋል።

የስብሰባው እንግዶች፤

በፔሩጃ በተደረገው መንፈሳዊ ስብሰባ፣ በመንፈስ ቅዱስ መታደስ የወጣቶች እንቅስቃሴ መሪዎች በኩል የተዘጋጁ ዓውደ ጥናቶች፣ ሰሚናሮች እና ሲምፖዚየሞች፣ መቅረባቸው ታውቋል። በስብሰባው ከተገኙት እንግዶች መካከል በኢጣሊያ በመንፈስ ቅዱስ መታደስ እንቅስቃሴ ፕሬዚደንት የሆኑት አቶ ሳልቫቶሬ ማርቲነዝ፣ የሰነ መለኮት ጠበብት እና ደራሲ አቶ ሉዊጂ ማርያ ኤፒኮኮ እና በኢጣሊያ የቤተሰብ ማሕበር ፕሬዚደንት የሆኑት አቶ ጂጂ ደ ፓሎ መሆናቸው ታውቋል።        

08 August 2018, 16:42