ወጣቶች ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ጋር በሮም በተገናኙበት ወቅት ወጣቶች ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ጋር በሮም በተገናኙበት ወቅት  

ዛሬ በሮም ከተማ በርካታ ከኢጣሊያ ከተሞች የመጡ ወጣቶች መገናኘታቸው ተገለጸ።

“እነሆ መጥተናል” በሚል መርህ ቃል የኢጣሊያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ባዘጋጀው ፌስቲቫል ለመገኘት ከ70 ሺህ በላይ የሚሆኑ ወጣቶች በሮም ከተማ ውስጥ፣ ችርኮ ማሲሞ በተባለ ስፍራ ተገኝተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

መንፈሳው ሕይወታቸውን ቀስ በቀስ በማሳደግ ላይ የሚገኙ የኢጣሊያ ካቶሊካዊ ሃገረ ስብከቶች ወጣቶች በሮም ከተማ ተገኝተዋል። ወደ ሮም ከተማ የመጡበት ዋና ዓላማ፣ በኢጣሊያ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ፣ የወጣቶች ሐዋርያዊ አገልግሎት ማስተባበሪያ ክፍል በኩል በተዘጋጀላቸው የበዓሉ መርሃ ግብር መሠረት፣ የሕብረት ጸሎትን ለማድረስና በጋራ ዝማሬ እግዚአብሔርን ለማመስገን መሆኑ ታውቋል። በሮም ከተማ ውስጥ፣ ችርኮ ማሲሞ በተባለ የሕዝብ መሰብሰቢያ ስፍራ የተገኙት ወጣቶች የአዲሱን ትውልድ የወደ ፊት ብሩህ የሕይወት ተስፋን ታላቅ ፍላጐት ለመጋራት እንደሆን ታውቋል።

ከኢጣሊያ ሀገረ ስብከቶች “እነሆ መጥተናል” በማለት በርካታ ወጣቶች የተገኙበት ይህ ፌስቲቫል፣ በመጭው ዓመት ከመስከረም 23 እስከ ጥቅምት 18 2011 ዓ. ም. በሮም ሊካሄድ ከታቀደው 15ኛው የካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት አጠቃላይ መደበኛ ጉባኤ ጥቂት ወራት አስቀድሞ ያደረጉት የመጨረሻው የበጋ ጊዜ  ግንኙነት ነው ተብሏል። ወጣቶች፣ እምነት እና የጥሪያቸውን ትክክለኛ ውሳኔን ጥበብና ማስተዋል በታከለበት መንገድ እንዲያደርጉ በሚሉት ርዕሠ ጉዳዮች፣ በሮም የመላው ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ለማድረግ ዕቅድ መያዙ  ይታወቃል። በርካታ ወጣቶች የዛሬውን ፌስቲቫል ለመካፈል ወደ ሮም ከተማ ያደረጉት መንፈሳዊ ጉዞ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ የተጀመረ መንፈሳዊ ጉዞ አካል እንደሆነ ታውቋል። ከዛሬው የዋዜማ ፌስቲቫል በኋላ ነገ እሁድ መላው የኢጣሊያ ወጣቶች ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር እንደሚገናኙ ከወጣው መርሃ ግብር ለማወቅ ተችሏል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከዚህ በፊት ባሰሙት ንግግራቸው፣ “ወጣቶች የሕይወታቸውን ጥሪ በሚገባ እንዲገነዘቡ፣ የተጠሩበትንም ዓላማ በክብር ተቀብለው በሕይወታቸው እንዲኖሩበት እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ ወጣት የፍቅር ጥሪውን በግል ያቀርባል ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን በማከልም ወጣቶች የእግዚአብሔርን ጥሪ በትክክል የተገነዘቡ ከሆነ ይህ ጥሪ በደስታ የሚሞላቸው የጸጋ ስጦታ መሆኑን በመግለጽ ከሁሉ አስቀድሞ ወጣቶች እግዚአብሔር እንደሚወዳችውና እንደሚፈልጋችው እርግጠኞች መሆን ያስፈልጋል፣ እርሱ ታማኝ ነው፣ ተስፋውንም በወጣቶች ላይ አድርጎአል። እምነታቸውን በእግዚአብሔር ላይ ላደረጉት ሁሉ እግዚአብሔር ታማኝ መሆኑን ልነግራችሁ እፈልጋለሁ።” ማለታቸው የሚታወስ ነው።

ወጣቶች ነገ እሁድ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ከተገኛኙ በኋላ፣ የከሰዓት በኋላው ዝግጅት የሙዚቃ እና የመዝናኛ ጊዜ እንደሚሆን ከወጣው መርሃ ግብር ለማወቅ ተችሏል። ከሙዚቃው ዝግጅት በተጨማሪ የወጣቶች የሕይወት ታሪክና ምስክርነት እንዲሁም ሕብረታቸውን የሚገልጹበት ዝግጅቶች እንደሚቀርቡ ታውቋል። የዚህ ዝግጅት ሙሉ ይዘትም በአገሩ የሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ተኩል ላይ የሚጀምር የቴለቪዥን ስርጭት በቲቪ 2000 በኩል በቀጥታ የሚተላለፍ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

በርካታ ወጣቶች ነገ እሁድ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከርዕሠ ሊቃነ ፍራንችስኮስ ጋር የሚያደርጉት ግንኙነት እና ቅዱስነታቸው ለወጣቶች የሚለግሱት ሐዋርያዊ ምክር፣ ወጣቶች በተረጋጋ መንፈስ ሕይወታቸውን እንዲመረምሩ የሚያስችላቸውን ሃይል ይጠይቃል። ወጣቶች ነገ በሮም ከተማ ውስጥ በሚያሳልፉት ምሽት፣ በሮም ከተማ ውስጥ ክፍት ሆነው በሚጠብቋቸው ቤተ ክርስቲያን በመሄድ የግልና የጋራ ጸሎት እንዲያደርጉ፣ እንዲሁም ኑዛዜን የሚገቡበት ጊዜም እንደተመቻቸላቸው ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ነገ እሁድ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ ለሚገኙት ወጣቶች በሚያስተላልፉት መልዕክት፣ ወጣቶች ወደ መጡበት ሀገረ ስብከቶች ሲመለሱ የሚያከናውኑትን ተልዕኮ እንደሚያሳውቁ እና በመቀጠልም ሐዋርያዊ ቡራኬ አቸውን እንደሚሰጧቸው ይጠበቃል። የኢጣሊያ ወጣቶች የላቲን አሜርካ አገር በሆነችው በፓናማ በሚከበረው የዓለም ወጣቶች ቀን በዓል ላይ ለመገኘት ይዘው የሚሄዱትን ሁለቱን ስጦታዎች እነርሱም በኢጣሊያ አሲሲ ከተማ በሚገኘው በቅዱስ ዳሚያኖ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኘውን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀልንና በሎረቶ የሚገኘውን የእመ ቤታችንን ቅድስት ድንግል ማርያም ምስልን ባርከው እንደሚሰጡ ታውቋል። በነገው ዕለት የኢጣሊያ ወጣቶች ከርዕሠ ሊቃነ ፍራንችስኮስ ጋር የሚያደርጉት ግንኙነት የሚከናወነው፣ የኢጣሊያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት፣ ብጹዕ ካርዲናል ጓልቲየሮ ባሰቲ ከሚመሩት መስዋዕተ ቅዳሴ በኋላ እንደሚሆን ለማወቅ ተችሏል።  

11 August 2018, 15:39