የቅዱሳን ኢያቄም እና ሀና አመታዊ በዓል በድምቀት ተከበረ የቅዱሳን ኢያቄም እና ሀና አመታዊ በዓል በድምቀት ተከበረ 

የቅዱሳን ኢያቄም እና ሀና አመታዊ በዓል በድምቀት ተከበረ

የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማሪያም ወላጅ ቤተሰቦች እና የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አያቶች የሆኑት የቅዱሳን ኢያቄም እና የሀና አመታዊ በዓለ በታላቅ መንፈሳዊነት ተከበረ

የቅዱሳን ኢያቄም እና ሀና አመታዊ በዓል በድምቀት ተከበረ

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በዛሬው እለት ማለትም በሐምሌ 18/2010 ዓ.ም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማሪያም ወላጅ ቤተሰቦች እና የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አያቶች የሆኑት የቅዱሳን ኢያቄም እና የሀና አመታዊ በዓለ በታላቅ መንፈሳዊነት ተክብሮ ማለፉ ይታወቃል።

የቅዱሳን ኢያቄም እና የሀና አመታዊ በዓል የአያቶች በዓለ በመባል የሚታወቅ ሲሆን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማሪያም ቤተሰቦች እና የኢየሱስ ክርስቶስ አያቶች በመባል የሚታወቁት እነዚህ ቅዱሳን በሕይወታቸው ውስጥ ሁለት አንኳር የሆኑ ተግባሮችን አከናውነው ማለፋቸው ይታወቃል። በመጀመሪያ ደረጃ የሚጠቀሰው ተግባር በወቅቱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያምን በሚገባ አስተምረው እና በስነ-ምግባር ታንጻ እንድታድግ ማድረጋቸው በቅድሚያ የሚያስመሰግናቸው ተግባር ሲሆን በመቀጠል ደግሞ የልጃቸው ልጅ  የሆነው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አያቶች በመሆን ሁለት ዋና ዋና ተግባሮችን አከናውነው ያለፉ ቅዱሳን ናቸው። በእዚህም ምክንያት በስተርጅናቸውም ሳይቀር ይህንን የልጃቸውን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማሪያምን እና የልጅ ልጃቸው የሆነውን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ተልዕኮ በማሰላሰል በእስትርጅናቸውም ሳይቀር ተልዕኮዋቸውን በሚገባ የተወጡ ቅዱሳን ናቸው ኢያቄም እና ሀና።

በእዚህም ምክንያት የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስትያን ምዕመናን ዘንድ ሐምሌ 26/2018 ዓ.ም  (በኢትዮጲያ የቀን አቆጣጠር ደግሞ በሐምሌ 18/2010 ዓ.ም ማለት ነው) የቅዱሳን የኢያቄም እና የሀና ዓመታዊ በዓለ በታላቅ መንፈሳዊነት ተከብሮ ማለፉን ከደርሰን መረጃ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን የእነዚህ ሁለት ቅዱሳን አመታዊ በዓል ለወላጆቻችን ያለንን አስተሳሰብ ጠንከር ባለ መልኩ እንድንገልጽ እና እንድናስታውስ በማድረግ ቅዱሳን ኢያቄም እና ሀና እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያምን ተንከባክበው፣ በስነ-ስረዓት እንዳሳደጉ እና በእግዚብሔር የደኽንነት ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ሚና እንድትጫወት፣ በምድር ላይ ከሚገኙ ሴቶች ሁሉ የተለየች እና የእግዚኣብሔርን የደኽንነት እቅድ እንድታስፈጽም በእግዚኣብሔር መመረጥ ትችል ዘንድ ያበቋት ቤተሰቦቿ በመሆናቸው የተነሳ እኛም የነስም  ይብዛም አሁን ላለንበት ደረጃ እንድንደርስ ከፍተኛ አስተዋጾ ያደርጉትን እና እያደርጉ የሚገኙትን ወላጆቻችንን እና አያቶቻችንን በማሰብ ለእነርሱ ያለንን ተገቢውን ፍቅር እና አክብሮት የምንገልጽበት እለት ነው።

የቀድሞ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት በነዴክቶስ 16ኛ እንደ አውሮፓዊያኑ የቀን አቆጣጠር በ2012 ዓ.ም የቅዱሳን የኢያቄም እና የሀና አመታዊ በዓለ በተከበረበት ወቅት ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት ይህንኑ በተመለከተ እንደ ገለጹት “የአንድ ኅብረተሰብ ጥራት ወይም ሥልጣኔ የሚለካው እና የሚውሰነው ለአረጋዊያን በሚደረገው እንክብካቤ እና በማኅበርሰቡ ውስጥ በሚሰጣቸው ክብር ላይ መሰረቱን ያደርገ ነው ማለታቸው” ይታወሳል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በበኩላቸው እንደ የአውሮፓዊያኑ የቀን አቆጣጠር በመስከረም 28/2018 ዓ.ም ከአረጋዊያን ጋር በተገናኙበት ወቅት በወቅቱ እንደ ገለጹት “አረጋዊያን ፍሬዎቻቸውን ይዘው እስከ መጨረሻ እንደ ሚዘልቁ ዛፎች ናቸው፣ ምንም እንኳን የእድሜ ጫና ቢኖርባቸው፣ ለአንድ ማኅበርሰብ እውነተኛ የሆነ ገጸ በረከት በመሆን እና የሕይወት ባሕል ተጠብቆ እንዲቀጥል የራሳቸውን ከፍተኛ የሆነ አሰተዋጾ ያደርጋሉ” ማለታቸው ይታወሳል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ አረጋዊያንን በተመለከተ በርከት ያሉ ንግግሮችን ማድረጋቸው የሚታወቅ ሲሆን በተለይም ደግሞ “የአረጋዊያን ጸሎት ለቤተክርስትያን በረከት ያስገኛል” በማለት በተደጋጋሚ መናገራቸው ይታወሳል። ይህንን በተመለከተ ቅዱስነታቸው ሲናገሩ የሚከተለውን ብለዋል. . .

"የአዛውንቶችና የአያቶቻችን ጸሎት ለቤተክርስትያን ጸጋ እና ሀብታም ነው! ለጠቅላላው ሰብአዊ ማኅበረሰብ በተለይም ደግሞ በሥራ ለተጠመዱ፣ በብዙ ሐሳቦች ለተወሰዱ እና በጣም ለተረበሹ የማኅበርሰባችን ክፍሎች በሙሉ ከፍተኛ የጥበብ ምንጭ እና መርህ ነው! አዛውንቶችንና አያቶቻችን ማክበር፣ ለእነርሱ መጸለይ እና መዘመር ያስፈልጋል”

ከቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች እኛም በዚህ የቅድስት ድንግል ማሪያም ወላጆች እና የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አያቶች በሆኑት የቅዱሳን ኢያቄም እና የሀና ዓመታዊ ክበረ በዓለ በተዘከረበት በዛሬው ቀን ይነስም ይብዛም አሁን ለደረስንበት ደረጃ እንድንደርስ ኮትኩተው ላሳደጉን ወላጆቻችን እና አያቶቻችን ተገቢውን ክብር እና እንክብካቤ እንዲሁም ፍቅር ልናደርግላቸው ይገባል ለማለት እንወዳለን።

 

26 July 2018, 15:14