ፈልግ

አባ ዣክ ሐመል አባ ዣክ ሐመል 

አባ ዣክ ሐመል፣ የዘመናችን የቤተ ክርስቲያን ሰማዕት ናቸው

ከሁለት ዓመት በፊት፣ መስዋዕተ ቅዳሴን በማሳረግ ላይ እያሉ የተገደሉትን አባ ዣክ ሐመልን በምናስታውስበት ዕለት፣ የእርሳቸው ምሳሌነት በዓለም ውስጥ ከተሰውት ሌሎች በርካታ ክርስቲያን ሰማዕታት መካከል አንዱ መሆኑን፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ገልጹ።

ዮሐንስ መኰንን - ከቫቲካን

አባ ዣክ ሐመል፣ በሰሜን ፈረንሳይ፣ በቅዱስ ኤቲየን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መስዋዕተ ቅዳሴን በማሳረግ ላይ እያሉ፣ በእስላማዊ መንግሥት ታጣቂዎች እጅ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ፣ በስይፍ ታርደው መገደላቸው ይታወሳል። ይህ በሆነበት የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ፣ መስከረም 4 ቀን 2009 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራኣንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤታቸው፣ ዘመዶቻቸው እና የስፍራው ምዕመናን በተገኙበት፣ ከሀገረ ስብከታቸው ጳጳስ ከሆኑት ከብጹዕ አቡነ ዶሚኒክ ጋር ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ወቅት እንደገለጹት፣ አባ ዣክ ሐመል፣ ረጋ ያሉ ሰው፣ ደግ፣ የሁሉ ወዳጅ እና ወንድምም ነበሩ ብለዋል።

ዛሬ ከሁለት ዓመት በኋላ፣ አባ ዣክ ሐመል በተገደሉበት ሀገረ ስብከት፣ ለሰላም እና ለወንድማማችነት በሚል መርህ፣ ሕዝባዊ በዓል ተዘጋጅቷል። በበዓሉ ስነ ስርዓት ላይ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት ክብርት ዣክሊን ጎራው የተገኙ ሲሆን፣ በተለያዩ መንፈሳዊ ዝግጅቶች በመታገዝ፣ የመቁጠሪያ ጸሎት እንደሚደረግ፣ በመቀጠልም በለብሩ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ በብጹዕ አቡነ ዶሚኒክ የተመራ መስዋዕተ ቅዳሴ ስነ ስርዓት እንደሚከናወን አስቀድሞ በወጣው መርሃ ግብር ተገልጿል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ አባ ዣክ ሐመል በዓለም ውስጥ ከተሰውት ሌሎች በርካታ ክርስቲያን ሰማዕታት መካከል አንዱ መሆናቸውን ተናግረው፣ አሁንም ቢሆን ሌሎች በርካታ ክርስቲያኖች ግድያ፣ ግርፋት፣ እስራት፣ እና አንገታቸውን እስከመቆረጥ ይደርሳሉ ብለዋል። ይህን ለመሰለ አሟሟት የሚያበቃቸው ሌላ ሳይሆን የኢየስሱ ክርስቶስ ፍቅር አስገድዷቸው፣ እርሱን መካድ ስለማይፈልጉ ነው በማለት በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤታቸው ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ወቅት አስረድተው የአባ ዣክ ሐመል የብጽዕና ጥናት ከሚያዝያ 5 ቀን 2009 ዓ. ም. ጀምሮ በሂደት ላይ እንዳለ ገልጸዋል። 

ፍቅር እንጂ ጥላቻ አያሸንፍም፣ ጥላቻ ድልን አያገኝም፣ ያሉት ክቡር አባ ረቧር ኣውዲሽ ባሳ፣ በኢራቅ፣ የምስራቅ ቤተክርስቲያን ስርዓተ አምልኮን የምትከተል ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ካህን፣ የአባ ዣክ ሐመልን እረፍት በማስታወስ እንደተናገሩት፣ በሃገራቸው በኢራቅ በአሸባሪዎች እጅ የሚገደሉ በርካታ ክህናት እንዳሉ ገልጸዋል። አባ ረቧር አውዲሽ በማከልም ፍቅር ሁሉንም እንደሚያሸንፍ ተናግረው ከካህናቱ ሕይወት የተማርኩት ነገር ቢኖር፣ እኛ የዘለዓለም ሕይወት ወራሾች እንጂ ሞተን የምንቀር አይደለንም ብለው፣ ሰማዕታት የጽድቅን ጎዳና የተከተሉ፣ ሕይወታቸውንም ለሌላው ለመሰዋት የተዘጋጁ ናቸው ብለዋል። ክቡር አባ ረቧር የሰማዕትነትን ትርጉም ሲያብራሩ፣ ሰማዕትነት እውነተኛ ምስክርነት እንደሆነ ገልጸው በርካታ ክርስቲያኖች ሕይወታቸውን እንደሚሰው ተናግረው በኢራቅ፣ በፓክስታን፣ በፊሊፒን እና በአፍሪቃ፣ ብዙን ጊዜ ጎልቶ ባይሰማም ብዙ ክርስቲያኖች እንደሚገደሉ ተናግረዋል።

አባ ዣክ ሐመል፣ በታጣቂዎች በተገደሉበት ዕለት፣ የሰይጣንን ሥራ በመቃወም፣ አንተ ሰጣን፣ ከዚህ ወዲያ ሂድ እያሉ በመጮህ እንደነበር በመስዋዕተ ቅዳሴአቸው ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ሁሉም የእምነት ተቋማት የእግዚአብሔርን ስም እየጠሩ መግደል ሰይጣናዊ ተግባር መሆኑን በተገነዘቡ ነበር ብለዋል። አባ ረቧርም በበኩላቸው እንደገለጹት ባለ እንጀራን እንደራስ ያለመቀበል ርዕዮተ ዓለማዊ አስተሳሰብ ይህን ወደ መሰለ ክፉ ተግባር ይመራል ብለዋል። ክፉ ተግባርን የሚፈጽሙት በተለያዩ ስሞች ለምሳሌ ኢስስ፣ ቦኮሃራም ወይም አል ሸባብ ተብለዉ ሊጠሩ ይችላሉ፣ ነገር ግን ክፉ ሥራቸው ተመሳሳይ ነው። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ንግግር ያስታወውሱት አባ ረቧር፣ ክፉ ሥራቸውን፣ ለምሳሌ የግል ጥቅምን ለማንቀሳቀስ፣ ሙስናን ለማስፋፋት፣ እና የተሳሳተ የፖለቲካ አካሄድንም ለማራመድ፣ ሃይማኖትን እና የእግዚአብሔርን ስም ይጠቀማሉ ብለው፣ የሁሉንም ሰብዓዊ ክብርን እና መብትን  ለማስጠበቅ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

26 July 2018, 15:02