ፈልግ

Centrafrica, Domenica Palme Bangui Centrafrica, Domenica Palme Bangui 

የመካከለኛው አፍሪቃ ሪፑብሊክ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ካህን የሆኑት ክቡር አባ ግባጓ ተገደሉ

በመካከለኛው አፍሪቃ ሪፑብሊክ ሲካሄድ የሰነበተው አመጽ የበርካታ ሰዎች ሕይወት ማጥፋቱ ሲታወቅ፣ በዚያች አገር የባምባሪ ሀገረ ስብከት ጠቅላይ ጸሐፊ የሆኑት ክቡር አባ ግባጓ ያለፈው አርብ ሰኔ 22 ቀን 2010 ዓ ም በአመጸኞች እጅ መገደላቸው ታውቋል።

የመካከለኛው አፍሪቃ ሪፑብሊክ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ካህን የሆኑት ክቡር አባ ግባጓ ተገደሉ መገደል በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ትልቅ ሐዘንን ማስከተሉ ተነገረ።

በመካከለኛው አፍሪቃ ሪፑብሊክ ሲካሄድ የሰነበተው አመጽ የበርካታ ሰዎች ሕይወት ማጥፋቱ ሲታወቅ፣ በዚያች አገር የባምባሪ ሀገረ ስብከት ጠቅላይ ጸሐፊ የሆኑት ክቡር አባ ግባጓ ያለፈው አርብ ሰኔ 22 ቀን 2010 ዓ ም በአመጸኞች እጅ መገደላቸው ታውቋል። የአይን እማኝ የሆኑት አባ ቦዶቦ፣ በሀገሪቱ የጸጥታ ሁኔታ መባባሱንና የሕይወት ዋስትናም እየጠፋ መምጣቱን ገልጸዋል። በማከልም ቤተ ክርስቲያናቸው ይህን ጉዳይ በዝምታ እንደማትመለከተው አስረድተዋል።

የዚህ ዜና አዘጋጅ ዮሐንስ መኰንን

ከምሽቱ ወደ አንድ ሰዓት ገደማ በጥይት ተደብድበው በአሰቃቂ ሁኔታ ከመገደላቸው በፊት፣ ክቡር አባ ግባጓ ከሌሎች ካህናት ጋር እራታቸውን ሊበሉ በገበታ ላይ እንደነበሩ ታውቋል። የመካከለኛው አፍሪቃ ሪፑብሊክ ዋና መዲና ባንጊ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካቴድራል ቆሞስ የሆኑት ክቡር አባ ማቴዎስ ቦዶቦ በቃለ ምልልሱ ወቅት እንደተናገሩት፣ በሀገሪቱ ውስጥ ጸጥታን የማስከበር አገልግሎት በመጥፋቱ የሰው ልጅ ሕይወት ዋስትና እንደሌለ ገልጸዋል። ይህንን ቤተ ክርስቲያናቸው በዝምታ እንደማትመለከተው ተናግረው የአባ ግባጓ ሕይወት በከንቱ መገደልም በቤተ ክርስቲያናቸው ላይ ከባድ ሐዘንን እንዳስከተለ ገልጸዋል።

ከሁለት ሺህ አምስት ዓ ም ጀምሮ በመካከለኛው አፍሪቃ ሪፑብሊክ፣ በተለይ በሰሜናዊው ክፍለ ሀገር በሚፋለሙ ታጣቂ አንጃዎች መካከል የሚካሄደው ፍልሚያ እያደገ መምጣቱ ይነገራል። ይህ ፍልሚያ በተለይ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ገዳማውያንንና የወንጌል ልዑካን፣ በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታ አስከባሪዋችና በእርዳታ ስርጭት ላይ በተሰማሩት ሰራተኞች ላይ ያነጣጠረ እንደ ሆነ ታውቋል። በተጨማሪም በርካታ መንደሮች በእሳት ጋይተዋል፣ በሕጻናትና በእናቶች ላይ ግፍ ይፈጸምባቸዋል ተብሏል። ክቡር አባ ማቴዎስ ቦንዶቦ ጥቃቱ በሀገሪቱ በሚገኘው መላው ቤተ ክህነት መካከል ያደረሰውን ጥልቅ ሐዘን አልሸሸጉም። በማከልም የመካከለኛው አፍሪቃ ርፑብሊክ መንግሥት ባለስልጣናት በንጹሀን ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት እንዲከላከል አሳስበዋል።

ክቡር አባ ማቴዎስ ቦንዶቦ፣ የአባ ግባጓ ግድያ ሁኔታ እጅግ የሚያሳዝን እንደነበር አስረድተው፣ ካህኑ የሰላም መልዕክተኛ፣ የመካከለኛው አፍሪቃ ሪፑብሊክ ሕዝቦች በፍቅር አብረው እንዲኖሩ ለተ ቀን የሚሰብኩ የሰላምና የፍቅር መልዕክተኛ እንደነበሩ ተናግረዋል። ከረጅም ጊዜ ወዲህ ስለ ሰላም እና በፍቅር አብሮ ስለመኖር ስንደክም ቆይተን አሁን በሀገሪቱ የተስፋፋው አመጽ የሰላም ሂደቱን እንደሚያወሳስበው እና በሕዝቦች መካከል የከፋ አመጽ እንዲከሰት ያደርጋል ብለዋል። አባ ግባጓ ሀገረ በስብከታቸው በባምባሪ ዘወትር የእውነት መስካሪ እና የሰላም መልዕክተኛ ነበሩ ብለዋል። ይህ ሆኖ ሳለ የአባ ግባጓ መገደል፣ ሰላምን ለማምጣት የሚደረግ ጥረት ምኑን ያህል መስዋዕትነትን  የሚያስከፍል እንደሆነ ገልጸዋል። በመካከለኛው አፍሪቃ ሪፑብሊክ በርካታ መሳሪያ ታጣቂዎች፣ ነፍሰ ገዳዮች፣ በንጹሐን ዜጎች ላይ ግፍን የሚፈጽሙ ግለ ሰቦች በተለይ በባምባሪ ከተማ ውስጥ አሁንም ተሰግስገው እንዳሉ ገልጸዋል። ባምባሪ ጸጥታ የሰፈነባት፣ የጦር መሳሪያ የሌለባት ከተማ እንደሆነች ሲነገር ቢቆይም የክቡር አባ ግብጓ መገደል ይህን አባባል ፈጽሞ ሐሰት ያደርገዋል ብለዋል።

ባሁኑ ጊዜ በመካከለኛዋ የአፍሪቃ ሪፑብሊክ አመጽ እየተስፋፋ መምጣቱ የሀገሪቱ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤን እያሳሰበ መምጣቱ ታውቋል። የጳጳሳት ጉባኤ በሰኔ 17 ቀን 2010 ዓ ም ባደረገው ጠቅላላ ጉባኤ መጨረሻ ላይ ባወጣው መግለጫቸው እንደገለጸው፣ በሀገሪቱ አዲስ አማጺ ቡድን እየተደራጀ መምጣቱ፣ ለሰላሙ ሂደቱ እንቅፋት እየሆነ መምጣቱን ገልጿል። ጳጳሳቱ እነዚህ አማጺ ቡድኖችም በሰላሙ ጥረት ጫናን የሚያሳድሩ እና ጠብን የሚቀስቅሱ በመሆናቸው ሰላምን አያመጡም ብለዋል። ይህን በማስታወስ የጳጳሳት ጉባኤ መግለጫ በማከልም ከዚህ በፊት የተገቡት ስምምነቶች ታጣቂ ሚሊሻዎችን የሚወግኑ በመሆኑ ምንም ዓይነት ውጤት እንዳላመጡ ጠቅሰው፣ ካሁን ወዲያ ከመንግሥት ባለስልጣና ጋር የሚደረግ ስምምነት ምንም ዓይነት ተቀባይነት እንደሌለው መንግሥትን፣ ዓለም አቀፍ ማሕበረሰብንና የተለያዩ ታጣቂ ቡድኖችን አሳስበዋል።

02 July 2018, 11:52