ፈልግ

የሚያዝያ 14/2010 ዓ.ም የሦስተኛው የፋሲካ ሳምንት እለተ ሰንበት ምንባባት እና የወንጌል አስተንትኖ በክቡር አባ ግርማቸው ተስፋዬ የሚያዝያ 14/2010 ዓ.ም የሦስተኛው የፋሲካ ሳምንት እለተ ሰንበት ምንባባት እና የወንጌል አስተንትኖ በክቡር አባ ግርማቸው ተስፋዬ 

የሚያዝያ 14/2010 ዓ.ም የሦስተኛው የፋሲካ ሳምንት እለተ ሰንበት ምንባባት እና የወንጌል አስተንት

ዛሬ እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት አቆጣጠር የትንሳኤ ሦስተኛ የተሰኘውን ሰንበትን እናከብራለን።

የሚያዝያ 14/2010 ዓ.ም የሦስተኛው የፋሲካ ሳምንት እለተ ሰንበት ምንባባት እና የወንጌል አስተንትኖ በክቡር አባ ግርማቸው ተስፋዬ

በእለቱ የተነበቡት ምንባባት

1.     2ቆሮ 5፡ 11-21 2

2.    ጴጥ 3፡14-18

3.    ሐዋ 21፡ 31-40

ሉቃስ 24፡ 13-32

በኤማሁስ መንገድ ላይ

በዚሁ ቀን ከደቀ መዛሙርት ሁለቱ፣ ከኢየሩሳሌም ዐሥራ አንድ ኪሎ ሜትር ያህል ወደሚርቅ፣ ኤማሁስ ወደሚባል መንደር ይሄዱ ነበር፤ እነርሱም ስለ ሆነው ነገር ሁሉ እርስ በርስ ይነጋገሩ ነበር። እየተነጋገሩና እየተወያዩ ሳሉም ኢየሱስ ራሱ ቀርቦ ከእነርሱ ጋር ይሄድ ጀመር፤ ነገር ግን እንዳያውቁት ዐይናቸው ተይዞ ነበር።

እርሱም፣ “እየሄዳችሁ፣ መንገድ ላይ እርስ በርስ እንዲህ የምትወያዩት ምንድን ነው?” አላቸው። እነርሱም በሐዘን ክው ብለው ቆሙ። ከእነርሱም አንዱ፣ ቀለዮጳ የተባለው፣ “በእነዚህ ቀናት እዚህ በኢየሩሳሌም የሆነውን ነገር የማታውቅ፣ አንተ ብቻ ለአገሩ እንግዳ ነህን?” ሲል መለሰለት እርሱም፣ “የሆነው ነገር ምንድን ነው?” አላቸው።

እነርሱም እንዲህ አሉት፤ “በእግዚአብሔርና በሰው ሁሉ ፊት በተግባርና በቃል ብርቱ ነቢይ ስለ ነበረው ስለ ናዝሬቱ ኢየሱስ ነው፤ እርሱን የካህናት አለቆችና ገዦቻችን ለሞት ፍርድ አሳልፈው ሰጡት፤ ሰቀሉትም። እኛ ግን እስራኤልን ይቤዣል ብለን ተስፋ ያደረግነው እርሱን ነበር፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ ይህ ከሆነ ዛሬ ሦስተኛው ቀን ነው። ደግሞም ከእኛው መካከል አንዳንድ ሴቶች አስገረሙን፤ እነርሱም ማልደው ወደ መቃብሩ ሄደው ነበር፤ ሥጋውንም ባጡ ጊዜ መጥተው እርሱ በሕይወት እንዳለ የነገሯቸውን መላእክት በራእይ እንዳዩ አወሩልን። ከእኛም መካከል አንዳንዶች ወደ መቃብሩ ሄደው፣ ልክ ሴቶቹ እንዳሉት ሆኖ አገኙት፤ እርሱን ግን አላዩትም።” እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ የማታስተውሉ ሰዎች፣ ልባችሁም ነቢያት የተናገሩትን ሁሉ ከማመን የዘገየ፣ ክርስቶስ ይህን መከራ መቀበልና ወደ ክብሩም መግባት አይገባውምን?” ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ በቅዱሳት መጻሕፍት ስለ እርሱ የተጻፈውን አስረዳቸው።

ወደሚሄዱበትም መንደር በተቃረቡ ጊዜ፣ ኢየሱስ አልፎ የሚሄድ መሰለ። እነርሱ ግን፣ “ምሽት እየተቃረበ፣ ቀኑም እየመሸ ስለ ሆነ ከእኛ ጋር እደር” ብለው አጥብቀው ለመኑት፤ ስለዚህ ከእነርሱ ጋር ለማደር ገባ።

አብሮአቸውም በማእድ በተቀመጠ ጊዜ እንጀራውን አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ሰጣቸው። በዚህ ጊዜ ዐይናቸው ተከፈተ፤ ዐወቁትም፤ እርሱም ከእነርሱ ተሰወረ። እነርሱም፣ “በመንገድ ሳለን፣ እያነጋገረን ቅዱሳት መጻሕፍትንም ገልጦ ሲያስረዳን፣ ልባችን እንደ እሳት ይቃጠልብን አልነበረምን?” ተባባሉ። በዚያኑም ሰዓት ተነሥተው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ ዐሥራ አንዱና ከእነርሱ ጋር የነበሩትም በዚያ በአንድነት ተሰብስበው አገኟቸው፤ “እነርሱም ጌታ በእርግጥ ተነሥቶአል! ለስምዖንም ታይቶአል” ይባባሉ ነበር። ሁለቱ ደቀ መዛሙርትም በመንገድ ላይ የሆነውንና ኢየሱስ እንጀራውን በቈረሰ ጊዜ እንዴት እንዳወቁት ተረኩላቸው።

የወንጌል አስተንትኖ በክቡር አባ ግርማቸው ተስፋዬ

 

በክርሰቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

ዛሬ እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት አቆጣጠር የትንሳኤ ሦስተኛ  የተሰኘውን ሰንበትን እናከብራለን።

በዚህም ዕለት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ሕይወታችን እንዲቀደስና በበረከቱም እንዲጠግብ ሕይወታችንን ለማስትካከልና በትክክለኛ መንገድ ለመምራት በኑሮኣችን በኣካሄዳችን እውነተኛ ክርስቲያኖች ሆነን የእርሱን ኣቅጣጫ የእርሱን ፈለግ በሙላት መከተል እንድንችል በተለያዩ የመጽሓፍ ቅዱስ ንባባት ኣማካኝነት ወደ እኛ ወደልጆቹ ይመጣል በዚሁም መሠረት እንግዲህ ቅድስት ቤተክርስቲያን በዚህ ሰንበት እንድናነባቸው እንድናስተነትንባቸው የዕለቱን የመጽሓፍ ቅዱስ ንባባት ወደ እኛ ታደርሳለች።

በዛሬው በመጀመሪያ ንባብ ቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ በሁለተኛው መልዕክቱ ለቆሮንጦስ ሰዎች በእነሱም በኩል ኣድርጎ ሁላችን በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ኣምነን ለተጠመቅን ሁሉ በውጫዊና ዓላማዊ ነገር ወይንም ደግሞ በጊዜያዊ ነገር ላይ እምነታችንን አንዳናስቀምጥ ይመክረናል። በሚታየውና በሚያምረው ገፅታችን ወይንም በመልካችን ሳይሆን እምነታችን ሁሌም በማይታየው ልባችን ባለው በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በእርሱና በእርሱ ላይ ብቻ ሊሆን እንደሚገባ ይነግረናል። ምክንያቱም እርሱ የሌለበት ሕይወት የተሟላ ሕይወት ሊሆን ኣይችልም እርሱ የሌለበት ሥራ የሰመረ ሥራ ሊሆን ኣይችልም እርሱ የሌለበት እርምጃ የተቃና እርምጃ ሊሆን ኣይችልም እርሱ የሌለበት ዕረፍት ሰላማዊና የተረጋጋ ዕረፍት ሊሆን ኣይችልም እርሱ የሌለበት ትዳር እርሱ የሌለበት ቤተሰብ በይቅርታና በመተሳሰብ ላይ የተመሠረተ እውነተኛ ፍቅርን የሚንፀባርቅ ትዳር ወይንም ቤተሰብ ጉዞ ሊሆን ኣይችልም።

ስለዚህ እውነተኛ መመኪያችን እውነተኛ ማረፊያችን የአብ አንድያ ልጅ የሆነው ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። የሰማይና የምድር ፈጣሪ የነገሮችና የጊዜኣት ሁሉ ባለቤት እርሱ ነው። እርሱ ጊዜን ካልሰጠ እርሱ ሕይወትን ካልሰጠ እርሱ ማስተዋልን ካልሰጠ ሁሉም ከንቱ ነው። ቅዱስ ዳዊት በመዝሙር 127፡1 አንዲህ ይላል እግዚኣብሔር ቤትን ካልሠራ ሠራተኞች በከንቱ ይደክማሉ እግዚኣብሔር ከተማን ካልጠበቀ ጠባቂ በከንቱ ይተጋል ይላል።

ስለዚህ ይህንን እውነታ በመረዳት ከሁሉ ነገር ይልቅ ቅድሚያ ለእርሱ መስጠት ግድ ይለናል። በተለይም ደግሞ በዐሥርቱ ትዕዛዛት ላይም ሰፍሮ እንደምናገኘው በሰንበት ቀን የኣንድ ክርስቲያን ተቀዳሚ ተግባር ሊሆን የሚገባው ወደ ቤተክርስቲያን በመሔድ እግዚኣብሔርን ስለሰጠው መልካም ነገር ሁሉ እርሱን ማመስገን ነው። እግዚኣብሔር ለኛ ከሰጠን ነገር ኣንፃር ሲታይ የእኛ በሰንበት ቀን ለእርሱ ቅድሚያ መስጠት ከምንም ነገር የሚቆጠር ኣይደለም። ሁላችንም እንደምናቀው እግዚኣብሔር ፍጹም ኣምላክ ነው የእኛ እርሱን ማመስገን በእርሱ ላይ የሚጨምረው ወይንም ደግሞ የሚቀንሰው ነገር የለም። ይልቁንም እኛ ከእርሱ ከሚመጣ ጸጋና በረከት ከእርሱ ከሚመጣ ኣባታዊ ቡራኬ ከእርሱ ከሚመጣ ኣምላካዊ ጥበቃ ተቋዳሾች እንሆናለን።

ቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ ይህንን ነገር በመረዳቱ ይመስላል ራሱን ሙሉ በሙሉ ለጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ኣሳልፎ ሰቷል ራሱን ሙሉ በሙሉ ለጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ኣስገዝቷል። ይህንን በመመልከት የቆሮንጦስ ሰዎች ኣብዷል ራሱን ስቷል በማለት ኣሉባልታ ሲሰነዝሩበት ሰምተናል ነገር ግን ቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ ሲመልስላቸው ይህ ያላችሁትን ብሆንም እንኳን ስለ እርሱ ፍቅር ስል ነው ይል ነበር። በተመሳሳይ መልኩ ዛሬም ክርስቲያኖች የጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ፈለግ በመከተል እውነተኛ የክርስትናን መንገድ ለመጓዝ ጥረት ሲያደርጉ እነሱን በተለያየ የኣሉባልታ ወሬና ሐሜት የሚጎነትሉ በክርስትና ሕይወት ያሉ ወይንም በክርስትና ሕይወት የሌሉ ወንድሞችና እህቶች ኣይጠፉም። እኛ ግን የእነርሱን ኣሉባልታ በመስማት ወደ ኋላ ከማለት ይልቅ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ሰይጣን እንደተመለከተን ተገንዝበን በከርስትና ሕይወታችን የበለጠ ልንበረታ ይገባናል። ልክ እንደ ቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ ራሳችንን ሙሉ በሙሉ ለጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በማስገዛት ይህ የምትሉትን ሁሉ የሆንኩት ለእርሱ ፍቅር ስል ነው በማለት ክርስትናችንን መመስከር ስለእነዛም ሰዎች መጸለይ ያስፈልጋል።

ሰዎች ጌታችን እየሱስ ክርስቶስን በተለያየ መንገድ እንደተቃወሙት ሥሙን እንዳጠፉት እንዲሁ ደግሞ ለሐዋርያት ተመሳሳይ ነገር እንዳደረጉባቸው ዛሬም ለእኛ ተመሳሳይ ነገር ያደርጉብናል ነገር ግን ይህ ሁሉ በእምነታችን በክርስትና ጉዞኣችን ይበልጥ እንድንጠነክርና ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ጋር ያለንን መቀራረብ እንድናጎለብት ልዩ ኣጋጣሚ ይፈጥርልናል።

ይህንን ካደረግን ይላል ቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ በሁለተኛ መልዕክቱ የኣዲሲቷ ምድር የኣዲሲቷ ሰማይ እጩዎች ነን ይላል ምክንያቱም በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ጸጋ አድገናልና እርሱም ማን እንደሆነ በሚገባ ተረድተናልና በማለት ይጠቅሰዋል።

ጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ኣውቀናል እርሱን በሚገባ ተረድተናል ብለን ስንናገር ቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያ መልዕክቱ እንደሰማነው ራሳችንን ሙሉ በሙሉ ለእርሱ ኣስገዝተናል የራሳችንን ፈቃድ በመተው የእርሱን ፈቃድ ለመፈጸምና ለእርሱ ፈቃድ ሙሉ በሙሉ ተገዢ ሆነናል ማለታችን ነው። ይህንን በማድረጋችን ደግሞ ክርስቶስ ወደደረሰበት ወደ ዘለዓለማዊ ክብር  ወደ ዘለዓለማዊ ሕይወት እንሸጋገራለን። የዕለቱ የሐዋርያት ሥራ ንባብም ጌታችን እየሱስ ክርስቶስን መከተል በእርግጥ ብርቱ ጥንካሬና ብርቱ ተጋድሎ እንደሚያስፈልግ ይነግረናል። ሓዋርያቶችም ሆኑ ቅዱሳን ሰማዕታት ይህንን ጉዞ በማድረጋቸው የመስቀሉ ጉዞ ተካፋዮች በመሆናቸው ዛሬ በታላቅ ክብርና ሞገስ በእግዚኣብሔር ፊት ይገኛሉ።

በዛሬው ዕለት የተነበበው የሉቃስ ወንጌልም የሚያተኩረው በተመሳሳይ ሓሳብ ነው ይኸውም የእግዚኣብሔርን ቃል በታላቅ ማስተዋልና በታላቅ ቅንነት ልንመለከተው በታላቅ ቅንነት ልናዳምጠው እንደሚገባ ይነግረናል።

እንዚህ የኤማሁስ ተጓዦች ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በመንገዳቸው ተገልጾ ከሙሴና ከነቢያትሁሉ ጀምሮ ያለውን እየጠቀሰ ቢያስረዳቸውም ኣንድ ጊዜ መንፈሳዊ ዓይናቸው ታውሯልና በፍጹም ማን እንደሆነ ሊያውቁት ኣልቻሉም። ምን ኣልባት ይህ ተመሳሳይ ሁኔታ በእኛም ሕይወት ውስጥ ብዙ ጊዜ ያጋጥም ይሆናል። ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ጋር ኣብረን እየተጓዝን ከማን ጋር እየተጓዝን እንዳለ የማንረዳበት ኣጋጣሚ ሊከሰት ይችላል። እነዚህ ሁለቱ የኤማሁስ ተጓዦች በውስጣቸው ከተፈጠረ ፍርሃት ኣንፃርና ከእምነታቸው ኣለመጠንከር የተነሳ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስን እንዳላወቁት ሁሉ ዛሬ እኛም ከእርሱ ጋር ኣብረን ብንጓዝም ሙሉ እምነታችንን በእርሱ ላይ ካላስቀመጥን ፍርሃት ወደውስጣችን ይገባል ይህ ፍርሃትም ጥርጣሬንና የመሳሰሉትን ሁሉ በውስጣችን በማሳደር ኣብረነው የምንጓዘውን ክርስቶስን በሙላት እንዳንረዳ ይጋርደናል። በምስጢራት ኣማካኝነት የምንቀበለውን ክርስቶስን በሙሉ ልባችን እንዳንረዳ ጋሬጣ ይሆንብናል በስተመጨረሻም ከመንገዳችን ያሰናክለናል።

እነዚህ የኤማሁስ ተጓዦች በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ሞት ልክ እንደሌሎቹ ደቀመዝሙሮች ተስፋ ቆርጠው ነበር ነገር ግን በስተመጨረሻ እርሱ መሆኑን ሲያውቁ ተስፋቸው ለመለመ የደከመ ሰውነታቸውም ጉልበትን ኣገኘ ስለዚህም በወንጌሉ ሲነበብ እንደሰማነው በዚያችም ሰዓት ተነስተው ወደ እየሩሳሌም ተመልሱ። ይህም የሚያስረዳን እውነታ ይህ ነው ሁል ጊዜ ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ጋር ስንጓዝ ተስፋችን የለመለመ ጉልበታችን የበረታ እምነታችንም የጠነከረ ይሆናል። ይህም ደግሞ በሙሉ ቁርጠኝነት ልክ እንደ ቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ ራሳችንን ሙሉ በሙሉ ለእርሱ እንድንሰጥና በእርሱ ፍቅር ብቻ እንድንመላለስ ያደርገናል። እንግዲህ እኛም እንደ ቃሉ ይህንን ሁሉ ፈፅመን የክብሩ ተካፋዮች እንድንሆን የደካሞች ኣፅናኝና የክርስቲያኖች ረዳት  የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጇ ይህንን ጸጋና በረከት ለእያንዳዳችን ታሰጠን።

  

 

22 April 2018, 10:43