ፈልግ

በኒውዮርክ ከተካሄዱ የሰላም ድርድሮች መካከል አንዱ በኒውዮርክ ከተካሄዱ የሰላም ድርድሮች መካከል አንዱ  (UN Photo/Loey Felipe)

በዓለም ዙሪያ ግጭቶችን የሚፈቱ 39 የሰላም ሂደቶች በመካሄድ ላይ እንደሚገኙ ተገለጸ

በስፔን ባርሴሎና ከተማ የሚገኝ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ የትጥቅ ትግሎችን በሰላማዊ መንገድ ለማስቆም የሚፈልግ የባለ ብዙ አቅጣጫ ጥረቶችን ለመተንተን ባደረገው ጥናቱ፣ ቤተ ክርስቲያኑ በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ፣ በአሜሪካ እና በአውሮፓ ውስጥ ባሉ ስምንት የድርድር ሂደቶች ላይ ትብብር በማድረግ ላይ እንዳለች አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት እና የቦሎኛ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ማቴዮ ዙፒ በቅርቡ ወደ ዩክሬን በመጓዝ በኪዬቭ ከከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ጋር 48 ሰዓት የፈጀ ውይይት አድርገው መመለሳቸው ይታወሳል። ብጹዕ ካርዲናል ማቴዮ ዙፒ ወደ ዩክሬን የተጓዙት በር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ተልከው እንደነበር ይታወሳል። የተልዕኮዋቸው ዓላማ ሩሲያን እና ዩክሬንን ወደ ሰላም የሚመራ ውይይት ለማካሄድ፣ አማራጮችን ለመፈለግ እና ይህን ለማሳካት ከዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ከአቶ ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል። 

እነዚህ ጥረቶች ቅድስት መንበር ከግጭቱ መጀመሪያ ጀምሮ እያከናወነች ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች እና የሰብዓዊ ዕርዳታ ተግባራት አካል መሆናቸው ይታወቃል። በእርግጥ በአሁኑ ወቅት በዓለማችን ዙሪያ 39 የሰላም ጥረቶች በሂደት ላይ እንደሚገኙ ሲታወቅ በእነዚህ ጥረቶችም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሳተፋቸው ታውቋል። ውስብስብነት ያላቸው ተነሳሽነቶች ከግጭቱ ተሳታፊ ወገኖች በተጨማሪ ሦስተኛ ወገኖችን በመጋበዝ ወደ ተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ እና ዘላቂ መፍትሄዎችን ለማምጣት በጋራ እንደሚሠሩ ታውቋል።

የግጭቶቹ አጠቃላይ እይታ

የሰላም ድርድሩ ውጤት ካስገኛቸው አጋጣሚዎች አንዱ ባለፈው የጎርጎሮሳውያኑ ህዳር 2/2023 ዓ. ም.  የኢትዮጵያ መንግሥት በሰሜኑ የአገሪቱ ከፍል ከሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ የፖለቲካ ፓርቲ ጋር ዘላቂ ሰላምን ለመፍጠር ስምምነት ላይ መድረሱ ይታወሳል። ስምምነቱ ግጭቶችን በዘላቂነት ለማስቆም እና በሁለቱም ወገኖች የተፈረሙ ስምምነቶች ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የሥራ አፈፃጸም እቅድ ያለው መሆኑን ታውቋል። ወደዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ እና የሰላም ሂደቱን ወደ ፊት ለማስቀጠል የአፍሪካ ኅብረት ተወካዮች፣ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) እና የአሜሪካ ዲፕሎማቶች አስተዋፅኦ ማድረጋቸው ይታወሳል።

እነዚህ እና ሌሎች ዛሬ በዓለም ዙሪያ እየተከናወኑ ያሉ ዲፕሎማሲያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊ፣ ማኅበራዊ እና ሰብዓዊ ጥረቶች እንደ ጎርጎሮሳውያኑ 2022 ዓ. ም. የሰላም ድርድር ትንተና ሪፖርት ላይ በዝርዝር እንደተቀመጠ በስፔን ባርሴሎና በሚገኝ የግል ዩኒቨርሲቲ የሰላም ባህል ማዕከል በተዘጋጀ ሰነድ በማጠቃለያው ላይ ገልጿል። ሰነዱ የተከሰቱትን ግጭቶችን በአገር እና በአህጉር ደረጃ አቅርቧል። ሪፖርቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ በመካሄድ ላይ ከሚገኙ 39% ድርድሮች መካከል የትግራይን የሰላም ድርድር በአፍሪካ ውስጥ ከሚካሄዱ 15% የሰላም ድርድር ሂደቶች አንፃር ይተነትነዋል።

26% በሚደርሱ ግጭቶች መካከል አሥር የሰላም ድርድሮች በእስያ አህጉር ውስጥ በመካሄድ ላይ እንደሚገኙ፣ 15% የሚደርሱ የአውሮፓ ግጭቶች መካከል ስድስት የሰላም ድርድሮች በመካሄድ ላይ እንደሚገኙ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ እና በአሜሪካ ውስጥ ከተቀሰቀሱት 20% ግጭቶች በእያንዳንዳቸው ውስጥ አራት የሰላም ድርድሮች በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ ጥናቱ አመልክቶ፥ እንደ ጎርጎሮሳውያን በ2022 ዓ. ም. ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰላም ድርድር ሂደት የተካሄደው በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል የተከተውን  ግጭት በድርድር ለመፍታት መሆኑን ጥናቱ አረጋግጧል። የ39 ከመቶ የሰላም ሂደቶች ትንተና ፆታን ያካተተ ሲሆን፥ የሰላም ሂደቶች ጦርነቶቹ በወንዶች፣ በሴቶች እና በሕጻናት ላይ የሚያስከትሉትን የአደጋ መጠንን ግምት ውስጥ ያስገባ እንደሆነ ለማየት ተችሏል።

ጥናቱን ካካሄዱት መካከል ወ/ሮ አና ቪሌላስ እንደተናገሩት፥ “እነዚህ መረጃዎች በጦርነት እና ተለዋዋጭ ሁኔታዎች መካከል ያለውን የኃይል እኩልነት እና ተፅእኖን እንድንመለከት ያስችሉናል” ብለው፥ “የሰላም ድርድር ሂደቶች በንድፍ፣ በአፈፃፀም፣ በአሳታፊነት፣ በውጤታማ ስምምነቶች በኋላ የሚደረጉ ስልቶችን እና ሌሎች ዘርፎችን በእኩል መጠን ትኩረት የማይሰጥ የትንታኔ ዓይነት ነው” በማለት አስረድተዋል።

ሰላምን ለመገንባት የተደረገ ጥናት

ለዚህ ሪፖት አስተዋፅዖን ያበረከቱት ስድስት ተመራማሪዎች፥ ጥናቱ በትምህርት ዘርፍ ብቻ የተገደበ ሳይሆን፣ ከዓላማው አንዱ መረጃና ትንተና በመስጠት ከተለያዩ ወገኖች የመጡ የግጭቱ ተዋናዮችን በሰላም ድርድር በማሳተፍ አገልግሎት ለመስጠት መሆኑን “የሰላም ባህል ትምህርት ቤት” ዳይሬክተር ወ/ሮ ጆርዲ ኡርጌል የሚመለከታቸውን አካላት፣ ሸምጋዮችን እና የሲቪል ማህበረሰብን በማካተት አስረድተዋል። ግጭት ውስጥ የሚገኙትን አካላት ለማቀራረብ ጥረት የሚያደርጉ ጅምሮች በሙሉ የሰላም ሂደት ተብለው ሊወሰዱ እንደማይችሉ የገለጹት ወ/ሮ ጆርዲ፣ ይልቁንም ግጭቶችን ለመፍታት እና ዋና መንስኤዎቻቸውን በሰላማዊ መንገድ ለመቀየር ያሰቡት ብቻ የሰላም ሂደቶች እንደሆኑ ባለሙያው ጠቁመዋል።

የሦስተኛ ወገኖች ሚና

የሰላሙ ሂደት እንዲፋጠን የሚረዳው የሦስተኛ ወገኖች ጣልቃ ገብነት ሲሆን፥ እነዚህ ወገኖች ከሁሉ በፊት ግጭት ውስጥ ባሉት ወገኖች ህጋዊ እውቅና ሊሰጣቸው እንደሚገባ፣ ተዋናዮቹ አብዛኛውን ጊዜ ዓለም አቀፍ ተቋማት ወይም አካላት ሲሆኑ ለውይይት የበኩላቸውን አስተዋፅዖ የሚያበረክቱ እና ከግጭቱ ነጻ ለመሆን የደኅንነት ዋስትና ሊሰጣቸው እንደሚገባ ሪፖርቱ ገልጾ በዚህ መሠረት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2022 ዓ. ም. ውስጥ 90% የውይይት ሂደቶች በሦስተኛ ወገኖች ንቁ ጥረት እንደተካሄዱ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቢያንስ አንድ ሦስተኛ አካልን ባካተቱ የድርድር ሂደቶች ላይ መሳተፉን ሪፖርቱ አስታውቋል።

ውይይትን በማቀላጠፍ ረገድ የቤተ ክርስቲያን አስተዋፅኦ

ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በካሜሩን፣ በሞዛምቢክ፣ በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ በኮንጎ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ፣ በደቡብ ሱዳን፣ በኮሎምቢያ እና በሄይቲ የሰላም ሂደቶች ላይ የተሳተፈች ሲሆን፥ አሁን በምታበረክተው አስተዋጽኦ ከሌሎች ጋር በመሆን በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል ያለውን ግጭት ለማስቆም እና ቀውሱን ለመፍታት የሰላም ድርድር መድረኮች በማመቻቸት ላይ እንደምትገኝ ሪፖርቱ ገልጿል።

የጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት እና የቦሎኛ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ማቴዮ ዙፒ ዩክሬን ውስጥ ከሃይማኖት መሪዎች ጋር ያደረጉት ውይይት ያሳየው ውጤት እና በሕዝብ ላይ የሚደርሰውን ስቃይ ለመቀነስ የሚደረግ ጥረት ቀጣይ እርምጃዎችን ለመገምገም ጠቃሚ እንደሚሆን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል አስታውቋል። እነዚህ የቤተ ክርስቲያን ተግባራት እና የተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የዓለም አቀፍ ኤጀንሲዎች እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥረቶች በሙሉ ሰላም በጦርነት ላይ ድል እስካለተቀዳጀ ድረስ ውጤታማ እንደማይሆኑ ሪፖርቱ ገልጿል።

 

20 June 2023, 17:35