ፈልግ

ሊዝበን የሚገኘው የጄሮኒሞስ ገዳም ሊዝበን የሚገኘው የጄሮኒሞስ ገዳም  (Vatican Media)

የፖለቲካ እና የሃይማኖት መሪዎች በሊዝበን መሰብሰባቸው ተነገረ

የቫቲካን ዜና ወደ ፖርቱጋል ተጉዞ እንደዘገበው ታዋቂ የሃይማኖት እና የፖለቲካ መሪዎች ስለ ሰላም ግንባታ፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና የከተሞች አካታችነት ዙሪያ ለመወያየት የፖርቹጋል መዲና በሆነችው ሊዝበን ከተማ መሰብሰባቸው ተነግሯል።

 አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የቆስጠንጢንያ ፓትርያርክ እና የመካ ታላቁ መስጊድ ኢማምን ጨምሮ ከሞላ ጎደል ከሁሉም የዓለም ዋና ዋና ሃይማኖቶች የተወከሉ ተወካዮች በዚህ ሳምንት በተለያዩ አበይት አጀንዳዎች ለመወያየት ሊዝበን ከተማ ገብተዋል።

የአውሮፓ ህብረት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የአፍሪካ ህብረት ባለስልጣናት እንዲሁም የበርካታ የአውሮፓ ሀገራት የቀድሞ መሪዎችን ጨምሮ በርካታ ታዋቂ የፖለቲካ መሪዎች በስብሰባው ላይ እንደሚገኙም ተገልጿል።

ይህ ውህደት ሆን ተብሎ የተደረገ ሲሆን፥ ዝግጅቱን በገንዘብ የሚደግፈው የካይሲድ (KAICID) የውይይት ማዕከል “ትራክ 1.5 ዲፕሎማሲ” ተብሎ በተሰየመው የውይይት ሂደት እንደሚያምን እና ይህም “ትራክ 1” የሚባለው በመንግስታት መካከል የሚደረጉ ውይይቶችን ከ “ትራክ 2” መንግስታዊ ባልሆኑ አካላት መካከል የሚደረገውን ውይይት ጋር በማዋሃድ የሚከናወን የውይይት ዓይነት ነው።

ካይሲድ ‘KAICID’

ካይሲድ ተብሎ የሚታወቀው ተቋም በ2003 ዓ.ም. የተመሰረተ እና የንጉስ አብዱላህ ቢን አብዱላዚዝ ዓለም አቀፍ የሃይማኖቶች እና የባህላዊ ውይይት ማዕከል ሲሆን፥ ሳዑዲ አረቢያ፣ ስፔን እና ኦስትሪያ እንደ መስራች ሃገራት፣ ቅድስት መንበር ደግሞ እንደ መስራች ታዛቢ ሃገር ይታያሉ።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከሰላም ግንባታ እስከ የአየር ንብረት ለውጥ ባሉ ጉዳዮች ላይ የሃይማኖቶች ትብብርን ለማበረታታት ያለመ መደበኛ ጉባኤዎችን እያስተናገደ ይገኛል።

ይህ ሰሞኑን እየተካሄደ የሚገኘው ስብሰባ “የውይይት እምቅ ሃይል፡ በፍጥነት በሚለዋወጥ ዓለም ውስጥ ለሰላም ጥምረቶችን መገንባት” በሚል መሪ ቃል ከግንቦት 6-8 ቀን 2016 ዓ.ም. የሚካሄድ ነው።

ጉባኤውም ሦስት ዋና ዋና የውይይት ርእሶች ያሉት ሲሆን፥ እነዚህም 'የሰላም ግንባታ'፣ 'አካታች ከተሞች' እና 'የተቀደሰ ስነ ምህዳር' የተሰኙት ናቸው።

እነ ማን ተሳተፉ

በዚህ ጉባኤ የሁሉም አቢያተ ክርስቲያናት መሪዎች እና የመካ ኢማምን ጨምሮ ከሞላ ጎደል ከሁሉም የዓለም ሃይማኖቶች የተውጣጡ መሪዎች እንደሚገኙበትም ተገልጿል።

ከእነዚህም ውስጥ የፖላንድ ዋና ረቢ፣ የሲክ መሪዎች (የሲክ ሃይማኖት የተመሰረተው ከ500 ዓመታት በፊት (1469) በፑንጃብ፣ ሰሜን ህንድ ነው)፣ የቡድሂስት እና የሂንዱ ድርጅቶች ኃላፊዎች፣ በርካታ የካቶሊክ እና የፕሮቴስታንት መሪዎች እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውስጥ የባሃኢ ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዋና ተወካይ ይገኙበታል።

ከፖለቲካ ተጋባዦቹ መካከል ከተባበሩት መንግስታት የስነ ህዝብ ፈንድ ተወካይ ወ/ሮ ሞኒካ ፌሮ፣ ከአፍሪካ ህብረት ዶ/ር ሞኒክ ሳንዛባጋንዋ እና የአውሮፓ ህብረት የሃይማኖት ነፃነት ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ፍራንስ ቫን ዴሌ ይገኙበታል።

የጣሊያን፣ የፈረንሳይ እና የኦስትሪያ የቀድሞ መሪዎች የነበሩ ማትዮ ሬንዚ፣ ፍራንሷ ኦላንዴ እና ሄንዝ ፊሸር በስብሰባው ላይ ይገኛሉ።

የውይይት ‘እምቅ’ ኃይል

ካይሲድ በድረ-ገጹ እንደገለጸው የውይይት መድረኩ “የውይይትን የለውጥ እምቅ አቅም ለመጠቀም፣ ሰብአዊ መብቶችን በማሳደግ ውጤታማነቱን ለመፈተሽ፣ ማህበራዊ ትስስርን ለማጎልበት፣ እርቅን ለማስፋፋት እና የአካባቢ ትብብርን ለማመቻቸት” እንደተዘጋጀ ገልጿል።
 

15 May 2024, 15:43