ፈልግ

ፓትርያርክ በርተሌሜዎስ የካይሲድ ጉባኤ ላይ ንግግር ሲያደርጉ ፓትርያርክ በርተሌሜዎስ የካይሲድ ጉባኤ ላይ ንግግር ሲያደርጉ 

የቀድሞ ፕሬዚዳንቶችን እና የቆስጠንጢንያውን ፓትርያርክ ያሳተፈ የውይይት ጉባኤ በሊዝበን ተጀመረ

የመካ የታላቁ መስጊድ ኢማም እና የቆስጠንጥንያ ፓትርያርክ ከተለያዩ ሃይማኖቶች የተውጣጡ ተሳታፊዎች የተገኙበት በሊዝበን በተካሄደ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ንግግር ባደረጉበት ጉባኤ የቫቲካን ዜና ተገኝቶ ዘገባ አቅርቧል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በፖርቱጋል መዲና ሊዝበን የሃይማኖት እና የፖለቲካ መሪዎችን አንድ ላይ ያሰባሰበው ካይሲድ (KAICIID) የተባለው የውይይት ማዕከል የገንዘብ ድጋፍ አድርጎ የተዘጋጀው እና 'የለውጥ ውይይት' የተሰኘው ጉባኤ ግንቦት 7 ቀን 2016 ዓ.ም. ረቡዕ ዕለት በይፋ ተጀምሯል።

የቆስጠንጥንያ ፓትርያርክ፣ የመካ ታላቁ መስጊድ ኢማም እና ሶስት የቀድሞ የአውሮፓ ሃገራት መሪዎችን ጨምሮ እጅግ ልዩ ክህሎት ያላቸው ተናጋሪዎች በጉባኤው ላይ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፥ እያንዳንዳቸው ለአስር ደቂቃ ያህል አጫጭር ንግግር አድርገዋል።

የውይይት ኃይል

የካይሲድ ዋና ፀሃፊ የሆኑት ዶ/ር ዙሀየር አልሃርቲ ዝግጅቱን ሲያስተዋውቁ ካነሱት ነጥቦች ውስጥ፥ በተለይ ዛሬ ላይ በዓለማችን እየጨመረ ከመጣው የ“አለመተማመን” ሁኔታ አንፃር ውይይቶች አስፈላጊ መሆናቸውን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

የቀድሞ የኦስትሪያ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሄንዝ ፊሸር በመቀጠል ባደረጉት ንግግር ፈላስፋውን ካርል ፖፐርን በመጥቀስ “እኔ ትክክል ልሆን እችላለሁ፣ አንተም ልትሳሳት ትችላለህ ወይም እኔ ልሳሳት እችላለሁ፥ አንተም ትክክል ልትሆን ትችላለህ፥ ነገርግን አንድ ላይ ሆነን ወደ እውነት መቅረብ እንችላለን” ብለዋል።

ከዶክተር ሄንዝ በማስከተል ንግግር ያደረጉት የቆስጠንጥንያው ፓትርያርክ እና የምስራቅ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መሪ የሆኑት ቀዳማዊ በርተሌሜዎስ ሲሆኑ፥ የክርስቲያኑ ማህበረሰብ በተለየ ሁኔታ የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ በሃይማኖቶች መካከል ውይይት እንዲደረግ ለረዥም ጊዜያት በቁርጠኝነት እየሰራ እንደነበር ጠቅሰው፥ ይህ ትግል “መንፈሳዊ ግዴታው” መሆኑንም ጭምር ጠቁመዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የመካ የታላቁ መስጊድ ኢማም ሷሊህ ቢን አብዱላህ አል ሁመይድ ህብረተሰቡን ከ ‘አክራሪነት እና ከጥላቻ’ ለመታደግ “መከላከል” አስፈላጊ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተዋል።

በዚህ የመጀመሪያ ቀን መርሃ ግብር የመጨረሻው ተናጋሪ የነበሩት የሊዝበን ከንቲባ ካርሎስ ሞዳስ ሲሆኑ፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በቅርቡ የዓለም ወጣቶች ቀንን ለማክበር ወደ ከተማዋ ያደረጉትን ጉብኝት በማስታወስ፥ የዓለም ወጣቶች ቀን በተከበሩባቸው ስድስት ቀናት “በሊዝበን ውስጥ ያሉ ሁሉም ሰዎች በፈገግታ ተሞልተው ነበር” ፥ ይህ ደግሞ ሃይማኖት ሊያመጣው የሚችለው አዎንታዊ አስተዋፅዖን የሚያሳይ ግልጽ ማሳያ ነው ብለዋል።

የሴቶች ሚና

በማንኛውም ጊዜ በሃይማኖታዊ ውይይት ውስጥ የተካፈለ ማንኛውም ሰው በእንዲህ ያለ የውይይት ወቅት የወንዶች የበላይነት እንደሚታይበት ሊናገር ይችላል።

ይህንን ጉዳይ የሞዛምቢክ ፖለቲከኛ እና የሰብአዊ መብት ተሟጋች የሆኑት ወ/ሮ ግራቻ ማሼል በቀጥታ የተመለከቱት ርዕሰ ጉዳይ ሲሆን፥ “ተስማሚ እና ዘላቂ ሰላም ከፈለግን ሴቶች በድርድሩ ውስጥ መሳተፍ አለባቸው” ሲሉ ለተሰብሳቢዎቹ ተናግረዋል።

ይህ አካሄድ እንዴት ሊሠራ እንደሚችል በምሳሌ ያብራሩት ወ/ሮ ግራቻ፥ በ2002 ዓ.ም. የኬንያ አዲስ ሕገ መንግሥት ከመጽደቁ በፊት በተካሄደው ብሔራዊ ውይይት ላይ ተሳትፈው እንደነበር በማስታወስ፥ በሂደቱ ውስጥ ሴቶች በግልፅ ተሳታፊ ስለተደረጉ ብቻ ነው ህገ መንግስቱ በህዝብ የዕለት ተዕለት ህይወት ውስጥ የሴቶች ቁጥር ኮታ እንዲይዝ የተደረገው ብለዋል። በዚህም ምክንያት በ2007 ዓ.ም. በሀገሪቱ በተካሄደው ምርጫ ከፍተኛ የሴቶች ቁጥር ተመርጠዋል በማለት የሴቶችን ሚና በምሳሌ አመላክተዋል።

የመንፈሳዊነት መሠረታዊ ሚና

‘በዚህ የመጀመሪያው ረጅም ቀን ውስጥ ካደረግኩት በጣም አበረታች ውይይቶች ውስጥ ከዓለም አቀፍ የሃይማኖት እና የዘላቂ ልማት አጋርነት ተወክለው ከመጡት ከኩሽዋንት ሲንግ ጋር ያደረግነው ቆይታ የማይረሳ ነበር’ ብሏል የቫቲካን ዜና ጋዜጠኛ።

አቶ ኩሽዋንት “ሁሉም ነገር የሚጀምረው ከውስጥ ነው፥ ፖለቲካዊ መፍትሄዎች፣ መዋቅራዊ ውይይቶች እና ቴክኒካዊ ውይይቶች ያስፈልጋሉ፥ መጀመሪያ ግን ውስጣችንን መለወጥ አለብን” ካሉ በኋላ፥ ይህ መንፈሳዊ ተጋድሎ “በሕይወት ውስጥ የምናሳልፈው ከፍተኛው ጥበብ” ነው ማለታቸውን ዘግቧል።
 

16 May 2024, 14:40