ፈልግ

ሊቀ ጳጳስ ጋብሪኤል ጆርዳኖ ካቺያ ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጋር- የፋይል ፎቶ ሊቀ ጳጳስ ጋብሪኤል ጆርዳኖ ካቺያ ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጋር- የፋይል ፎቶ 

በተ.መ. ድርጅት የቅድስት መንበር ታዛቢ ከጦርነት ውጭ ያሉ ውጤታማ አማራጮችን መጠቀም ያስፈልጋል አሉ

ኒውዮርክ በሚገኘው በተባበሩት መንግስታት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ብጹእ አቡነ ጋብሪኤል ካቺያ ከቫቲካን መገናኛ ብዙሀን ጋር ባደረጉት ሰፊ ቃለ ምልልስ “ወታደራዊ መፍትሄዎች” እንደማይሰሩ እና ሌሎች መንገዶችም መታየት እንዳለባቸው ከገለጹ በኋላ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ አደጋዎች በሰው ልጅ ህልውና ላይ ተጨባጭ ስጋት እንደሚፈጥሩ አስጠንቅቀዋል።

 አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

“ወታደራዊ መፍትሄ” የሚባለው ነገር አይሰራም፣ በሺህዎች የሚቆጠሩ ህይወቶች ጠፍተዋል፣ ቤተሰቦች ወድመዋል፣ ቤት፣ ስራ እና መሠረተ ልማት ወድመዋል፣ ስለዚህም ሌላ መንገድ መታየት እንዳለበት…”

በተባበሩት መንግስታት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ ጋብሪኤሌ ካቺያ ከቫቲካን መገናኛ ብዙሀን ጋር ባደረጉት ሰፊ ቃለ ምልልስ ነበር ከላይ ያለውን የገለጹት።

በውይይቱ ወቅት ታዛቢው በተለይ በዩክሬን እና በመካከለኛው ምስራቅ ያሉትን ጦርነቶች ግምት ውስጥ በማስገባት የሰላም መንገዶች በማንሳት፥ በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ውስጥ እንኳን መረጋጋትን የሚያመጡ እና እስካሁን ጥቅም ላይ ያልዋሉ ሌሎች መንገዶች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

ሐዋርያው ጳጳስ ከዚህም በተጨማሪ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የጦር መሣሪያ ወጪዎች ላይ ያለውን አሳሳቢ እውነታ አብራርተዋል፥ እንደነዚህ ያሉት ኢንቨስትመንቶች በማህበራዊ-ኢኮኖሚያዊ ልማት እና ግጭት መከላከል ፕሮግራሞች ላይ ቢውሉ የተሻለ ለውጥ ይመጣ ነበር ብለዋል። እርስ በርስ መተማመንን እና ዲፕሎማሲያዊ መዋቅሮችን እና ትብብርን ወደነበረበት መመለስ አስፈላጊነት በማንሳት፥ “በአጠቃላይ ለሰው ልጅ ህልውና ስጋት” የሚሆኑ የኑክሌር ጦር መሳሪያዎች አደጋ ቤተክርስቲያን በጽኑ ያሳስባታል ብለዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሆነው ለአምስት ዓመታት ያገለገሉት ሊቀ ጳጳስ ካቺያ፣ ይህ ታላቁ ዓለም አቀፍ ድርጅት ለሰላም የበለጠ ውጤታማ ሚና እንዲጫወት አስፈላጊ ነው ብለው የሚያምኑትንም ገልጸዋል።

ጥያቄ፦ ክቡርነትዎ፣ አሁን ባለው አሳሳቢ የዓለማችን ሁኔታ ምክንያት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የሰላም ጥሪ ማቅረባቸውን ቀጥለዋል። በተሞክሮዎ መሰረት በተለይም በዩክሬን እና በመካከለኛው ምስራቅ ግጭቶች ውስጥ የሰላም መንገዶችን እንዴት ማግኘት ይቻላል?

መልስ፦ ከበርካታ ምክንያቶች እና ሀላፊነት ከሚሰማቸው ዋና ተዋኒያን የተለያየ እይታዎች ለሚነሱ እንደዚህ ያሉ ግጭቶች ማንም “አስማታዊ” መፍትሄ የለውም። ነገር ግን፣ በድፍረት እና በፀና እምነት መናገር የሚቻለው መፍትሄው ሰላም ብቻ ነው፥ የአመጽ እና የግጭት መንገዶች ይልቁንም ሞትን ማመንጨት፣ ኢፍትሃዊነትን ማስቀጠል እና ጥላቻን ማፍራት ነው ውጤታቸው። አንተ ባነሳሃቸው ግጭቶች ውስጥ “ወታደራዊ መፍትሄ” ተብሎ የሚጠራው አይሰራም፥ ነገር ግን ሌላ የወደፊት ሁኔታን መገመት አይቻልም። በነዚህ ጦርነቶች በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ በሺዎች የሚቆጠሩ ህይወት ጠፍቷል፣ ቤተሰብ ወድሟል፣ ቤት፣ ሥራ እና መሰረተ ልማት ወድሟል፥ ነገር ግን ውስብስብ በሆነ መንገድ ሌላ የሰላም አማራጭ መወሰድ እንዳለበት ግንዛቤን አምጥቷል። ወደ ጦርነት የሚያመሩ ምክንያቶች ብዙ እንደመሆናቸው መጠን፣ ወደ ሰላሙ መንገድ ሊመሩ የሚችሉ ምክንያቶችም ያን ያክል ብዙ ናቸው። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ የሰላም መንገዶችን መፈለግ ከሁሉም አካላት ቅን ቁርጠኝነትን፣ ግልጽ እና ገንቢ ውይይት እንደሚያስፈልግ፣ ከሁሉም በላይ መለያየትን ወደ ጎን በመተው ለጋራ ጥቅም በጋራ ለመስራት፣ ዕርቅና አብሮነትን የሚያጎለብት መሆኑን አስገንዝበዋል።

ጥያቄ፦ ሊቀ ጳጳስ ካቺያ በእርስዎ አስተያየት ፍጥነቱን ለማርገብ የሚረዱ እና እስካሁን ጥቅም ላይ ያልዋሉ መንገዶች አሉ? በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ውስጥም ቢሆን?

መልስ፦ የተባበሩት መንግስታት ቻርተር ስድስተኛው ምዕራፍ በአጠቃላይ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት “በድርድር፣ በመጠየቅ፣ በሽምግልና፣ በመግባባት፣ በግልግል ዳኝነት፣ በክልላዊ ኤጀንሲዎች ወይም በድርድሮች መሆን እንደሚገባ” የሚመለከት ሲሆን፥ ይህም አጠቃላይ የሰብአዊ እርምጃዎችን መጨመር ይቻላል። ስለዚህ ለተለያዩ ተነሳሽነቶች ሰፊ ቦታ አለ፣ ነገር ግን መሰረታዊ የሆኑ ተግዳሮቶች እና በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት ለመጠቀም ፈቃደኞች ያለመሆን አዝማሚያ ስላለ በተግባር ላይ ለማዋል አስቸጋሪ ይሆናሉ።

ጥያቄ፦ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ጦርነት በከፍተኛ ሁኔታ እየተካሄደ ይገኛል። እንዲሁም በመገናኛ ብዙኃን ያልተነገሩ ጦርነቶች አሉ፥ ለምሳሌ በማይናማር፣ ሱዳን፣ ሶሪያ፣ የመን፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ... በቅርቡ በወጣው ሪፖርት መሰረት ብዙ አገሮች ለጦር መሣሪያ የሚያደርጉትን በጀት እየጨመሩ ባሉበት በዚህ እጅግ ተለዋዋጭ ሁኔታ እርሶን ይበልጥ የሚያሳስበው ዬትኛው ነው?

መልስ፦ በጣም የሚያሳስበኝ የግጭቶች “መባባስ” ስጋት እና የሰው ልጅ ስቃይ ከቀን ወደ ቀን እየከፋ የመምጣቱ ጉዳይ ነው። ይህ የጦር መሳሪያ ባለቤትነት ውድድር በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማት ላይ ጥቅም ይውሉ የነበሩትን የገንዘብ ምንጮችን ያካትታል። በይበልጥ በመሠረታዊነት ይህ ሁሉ አካሄድ የሚያሳየው ደኅንነት የሚመነጨው በኃይልና በጦር መሣሪያ ይዞታ ነው የሚለውን አደገኛ ቅዠትን ያመላክታል። በሌላ በኩል ግን በጋራ መተማመንና ኃላፊነት ላይ የተመሠረተ ግንኙነት ውጤት ነው። ከዚህ አንጻር የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ለ “ወንድማማችነት” ወይም “ማህበራዊ ወዳጅነት” ያቀረቡት ጥሪ በእርግጠኝነት የሰላም ግቡን እንዲያሳካ ከተፈለገ፥ ከመሰረቱ “መለወጥ” ያስፈልጋል።

ጥያቄ፦ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ሀገራት ያሏቸው የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ከፍተኛ አደጋ ሊያስከትሉ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል። በእርስዎ እይታ የሰው ልጅ በዚህ የታሪክ ደረጃ እያጋጠመው ያለው አደጋ ምንድን ነው?

መልስ፦ ስለ ሰው ልጅ ክብርና ሰላም ለሚያስተምረው ዶግማዋ ታማኝ የሆነችው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን፣ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ አደገኛነት እንደሚያሳስባት በተለያየ ጊዜ ገልጻለች። እነዚህ የጦር መሳሪያዎች ሰፊ ውድመት ሊያስከትሉ፣ አካባቢን ሊያበላሹ ብሎም አሁኑ ባለው እና በሚመጣው ትውልድ ላይ ሊነገር የማይችል ስቃይ እንደሚያስከትሉ፥ በአጠቃላይ በሰው ልጅ ላይ የህልውና ስጋትን ያመጣሉ። ከዚህ አንፃር፣ በጥቅም ላይ ብቻ ሳይሆን አውዳሚ የጦር መሣሪያ ባለቤት መሆንም ከሥነ ምግባር አኳያ ተቀባይነት የሌለው፣ በመከላከያ ውስጥ ካለው ተመጣጣኝነት መርህ ጋር የሚቃረን በመሆኑ፣ የማይለይና የማይቀለበስ ጉዳት ስለሚያደርስ ግልጽ የሆነ ውግዘት ያስፈልገዋል። ሆኖም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ እንዳሉት ከኒውክሌር አደጋ በተጨማሪ ዛሬ በሰው ልጅ ላይ ዓለም አቀፍ አደጋ የሚፈጥሩ ሌሎች ሁለት እውነታዎች እንዳሉ፣ ማለትም የአየር ንብረት ለውጥ እና ከቁጥጥር ውጪ የሆነ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ወይም ‘አርቴፍሻል ኢንተለጀንስ’ እድገት መኖሩንም መጨመር እፈልጋለሁ። በእነዚህ በሦስቱ አስገራሚ ጉዳዮች፣ የቤተክርስቲያኑ ድምጽ በግልጽ እና አሳማኝ በሆነ መልኩ ይሰማል፥ የኒውክሌር ጉዳዮችን በተመለከተ፥ ቅድስት መንበር የኑክሌር ጦር መሣሪያዎች እንዳይስፋፋ የሚደነግገውን ስምምነትን ከማፅደቋ በተጨማሪ፣ የቅርብ ጊዜውን ታህሳስ 2013 ዓ.ም. ለፈራሚ ሀገራት ተፈፃሚ የሆነው ሙሉ ክልከላውን አጽድቃለች። የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ‘ኢንሳይክሊካል ላውዳቶ ሲ’ እና ታህሳስ ወር ላይ በዱባይ የተካሄደውን የፓርቲዎች ጉባኤን በማስመልከት በቅርቡ የወጣውን ሐዋርያዊ መግለጫ ‘ላውዳቴ ዲየምን’ ማስታወስ በቂ ነው። በመጨረሻም አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን በማስመልከት ቅዱስ አባታችን በዚህ ዓመት ታህሳስ 22 ቀን የሰላም ቀንን በማስመልከት በላኩት መልእክት ላይ በተለየ ሁኔታ አንስተዋል። አሁን ደግሞ በሚቀጥለው ወር በፑግሊያ በሚካሄደው የጂ7 ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ እና ሰው ሰራሽ አስተውሎት ስላለው የጎንዮሽ ጉዳት ወይም የስነምግባር ግድፈት ለማንሳት በዝግጅት ላይ ይገኛሉ።

ጥያቄ፦ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እንዳሉት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የተፈጠረው የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ መዋቅር መዳከም በብዙ የዓለም ክፍሎች እየታየ ያለው የጥላቻ እና የግጭት መንስኤ ሆኗል። በእርስዎ አስተያየት ይህ በጣም የተዳከመው የት አከባቢ ነው?

መልስ፦ ከባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ አንፃር በፓርቲዎች መካከል ጥልቅ እና ሰፊ የሆነ የመተማመን መሸርሸር አለ። በክልሎች መካከል የጋራ መተማመን ካለ ትብብርን፣ ግልጽ ውይይትን እና ግጭትን ለመፍታት ያስችላል። በአንፃሩ መተማመን ከሌለ ዓለም አቀፍ ግንኙነቶች በጥርጣሬ፣ በፉክክር እና በጥላቻ ሊገለጡ ስለሚችሉ የጋራ ተጠቃሚነትን እና ዘላቂ ሰላምን የሚያጎለብቱ ስምምነቶች እና መግባባት ላይ ለመድረስ አስቸጋሪ ያደርገዋል። ለአብነት ያህል፣ በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ የ ‘ቬቶ’ ወይም ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት እና በተለይም የመስቀለኛ ድምጽ አጠቃቀም እየጨመረ መምጣቱን ልብ ሊባል ይችላል። በአምስት ወራት ብቻ ለስድስት ጊዜ ያክል ጥቅም ላይ ውሏል፥ ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ፣ በ2009 ዓ.ም ብቻ ሙሉውን ዓመት ለሰባት ጊዜ ያክል ጥቅም ላይ መዋሉ ይታወሳል።

ጥያቄ፦ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ በመሆን ለአምስት ዓመታት አገልግለዋል። ይህ ታላቅ ዓለም አቀፍ ድርጅት ለሰላም የበለጠ ውጤታማ ሚና እንዲጫወት ምን መደረግ ያስፈልጋል ይላሉ?

መልስ፦ በመጀመሪያ ደረጃ ከተለያዩ አቅጣጫዎች በትክክል የተገለጹ ችግሮች እንዳሉ ሆነው፣ የዚህ ድርጅት ህልውና በራሱ ትልቅ ስኬትና ትልቅ ዕድል መሆኑን በድጋሚ ማረጋገጥ ያለብኝ ይመስለኛል። ለነገሩ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በቋሚነት እና በተረጋጋ ሁኔታ ለመገናኘት፣ ፊት ለፊት ለመወያየት እና ለመነጋገር ብቸኛው መሳሪያ ነው። እንደ ሁሉም ተቋማት ሁሉ ከዘመኑ ጋር ለመራመድ ቀጣይነት ያለው ማስተካከያ ማድረግ አስፈላጊ ሲሆን፥ ከዚህ አንፃር የስርአቱን ማሻሻያ ለማድረግ ያሰቡ የተለያዩ ሂደቶች አሉ። ከሁሉም በላይ ግን የተባበሩት መንግስታት ቻርተር መርሆዎች ሁሉንም ትክክለኛነታቸውን ወይንም ተገቢነታቸውን የሚጠብቁ ይመስለኛል፥ መተግበሪያዎቹ እና ዘዴዎቹም እንዲሁ አይጎድሉም። ምናልባት ዛሬ ወደ ሰላም የሚያደርሱ መንገዶችን ለማግኘት የዛሬ ሰማንያ ዓመታት ገደማ ለዚህ ድርጅት መፈጠር ያነሳሳውን መንፈስ እንደገና ማግኘቱ አስፈላጊ ይሆናል። በመጪው መስከረም እዚህ ኒውዮርክ ውስጥ በሚካሄደው የቀጣዩ “የወደፊቱ ጉባኤ” ድርሻ ይህ ይመስለኛል።
 

15 May 2024, 21:08